የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት አፕሪል ወር ግድም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ድምጻቸውም ምስላቸው ለአንድ ወር ያህል ጠፍቶ ነበር። አስመራ በቅርብ የሚያውቋቸው ሳይቀሩ መረጃ አልባ በመሆናቸው ዜናው በተለይ በውጭ አገር ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ኢሳያስ ሰሞኑን ልክ የዛሬ አስራ ሶስት ዓመት እንደሆነው ሳይሆን በሌላ መልኩ መነጋገሪያ ሆነዋል። አጀንዳ የሆኑትም ” በቃቸው” በሚል ነው። በስም የሚታወቁ ተቃዋሚዎች ይሁኑ ሌላ አካል ኢሳያስ ላይ ኃይል የሚጠቀምበት ወቅት መድረሱን የሚናገሩም እየበዙ ነው።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የዛሬ አስራ ሶስት ዓመት ግድም ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ከህዝብ ዕይታ ተሰውረው መቆየታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ታመዋል በሚል በኤርትራዊያን ዘንድ በስፋት መነጋገሪያ ሆነው ቢቆዩም በስተመጨረሻ “በኤርትራ ቴሌቪዚን ቀርበው “ያስወሩብኝ ጠላቶቼ ናቸው። ጤነኛ ነኝ አለሁ ” በማለት ምንም እንዳልተፈጠረ አስታውቀው ዜናውን ውሃ አፍሰውበታል።
እሳቸው ጤነኛ መህናቸውንና ምንም የተፈጠረ ነገር እንደሌለ ቢናገሩም የመንግስታቸው ተቃዋሚ የሆኑ ድረ ገጾች ፕሬዘዳንቱ በጉበት በሽታ በጽኑ መታመማቸውን በስፋት ሲዘግቡ ነበር። አንዳንዶቹም በህይወት መኖራቸውን ሳይቀር የሚሞግት ዘገባ ያቀርቡ ነበር። በተለይም ‘አሴና” የተሰኘው ድረ ገጽ ምንጮችን ጠቅሶ የኢሳያስን መታመም ዘግቦ ኤርትራ ባሁኑ ወቅት በጥድፍያ በተቋቋመ ‘የአመራር ጉባዔ’ ስር እየተዳደረች ስለመሆኗም አመልክቷል። አሴና ባጭሩ የስውር ሽግግር መንግስት መቋቋሙን ነበር ያስታወቀው።
አማጺ በማደርራጀትና የሽብር ተልዕኮ በመስጠት የውክልና ስራ የሚሰሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ በርካታ በደል የፈጸሙና እየፈጸሙ ያሉ መሆናቸው ቢታወቅም ደፍሮ መቀመጫቸውን ለመነቅነቅ የሞከር መሪ ኢትዮጵያ አልገጠማትም።
መለስ ከጫፍ የደረሰ ድል ገልብጠው በኤርትራ ጉዳይ ሁለት ታሪካዊ ጥፋት ሰርተው አለፉ። ኃየለማሪያም ደሳለኝ በክፉም ሆነ በበጎ የሚጠቀስ ስራ አልሰሩም። አብይ አሕመድ በፍቅር ጀምረው ዓለምን ጉድ ቢያሰኙም መጨረሻው አላማረላቸውም።
ኢሳያስ “ኢትዮጵያ የጋራቸን” በሚል ወተቷን ማለብና የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ እንዳሻቸው መዘወር ነው ዓላማቸው። የጦርነቱ ወቅት መንግስት አቅም ስላላበጀ፣ በታጋሽነት አብሮ እንዳላየ ሆኖ ቢሰራም ከሻዕቢያ ተፈጥሮ አንጻር ሊቀጥል እንደማይችል በርካቶች ገምተው ነበር። የሆነው አልቀረም በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ “ለምን ገብቼ አልፈተፈትኩም” በሚል አኩርፈው የፍቅር ውላቸውን ቀደዱ።
አፍታም ሳይቆይ አብይ አሕመድ ፊታቸውን ከባህር በር አንጻር ወደ ሶማሊላንድ ሲያዞሩ የኢሳያስ አውሬነት ከረባት ለብሶ አደባባይ ወጣ። ኢትዮጵያን በገሃድ ረግመው ከግብጽና ሶማሌ ጎን ለመቆም መወሰናቸውን ጭራቸውን እየቆሉ በይፋ ተናገሩ። የቀጠሯቸው የዩቲዩብ ፍልፈሎችም ከአገራቸው ጥቅም ይልቅ ኢሳያስ በልጠውባቸው እሳቸውን አንግበው ኢትዮጵያና ጥቅሟ ላይ መዝመት ጀመሩ። አሁንም እየዘመቱ ናቸው። በዚህ መነሻ ነው ” ክፋት ከተፍለገ ከእርስዎ በላይ እናቅበታለን” በሚል በባህር ከታች ጉሮሮ ለመንከስ፣ በድንበር እሳቸውን የሚገነድስ አቅጣጫ መያዙ የተሰማው።
በዚሁ መነሻ ሲብላላ የኖረው ቁጭት አሁን ላይ ኤርትራ ላይ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ መረጃ በተመጋጋቢነት እየተሰማ ነው። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን “ኢትዮጵያ የጋራ” የሚለውን እሳቤ አስመልክቶ ሲሽኮረመም የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ አቋሙን ካሳወቀ በሁዋላ በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች “አለ ነገር” የሚያስብል የሆነውም ለዚሁ ነው።
አቶ ኢሳያስ ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀችበት ቀን ጀምሮ አገሪቷን በብቸኝነት ሲመሩ መቆየታቸው ብቻ ሳይሆን ምክትል እንኳን ስለሌላቸው ድምጻቸው ጠፍቶ በነበረበት ወቅት የኤርትራ መሪ ማን ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄም ይነሳ እንደ ነበር አሁንም ተመሳሳይ ስጋት እሳቸውን ከማስወገዱ ጋር ጎን ለጎን እየተነሳ ነው። በዛው ወቅት አሴና ፕሬዚዳንቱ ሞተዋል በሚል ጊዜያዊ የስልጣን ድልድል መከናወኑን ጠቅሶም ዘግቦ ነበር። ዛሬ ይህ አጀንዳ የሚያስጨንቃቸው ኢሳያስ ሲወገዱ ስለሚተካው መሪና ሽግግር ጎን ለጎን በጥልቀት ሊሰራበት እንደሚገባ እየገለጹ ነው።
“በኤርትራ ሰዓት ቆሟል” የሚለው ዘጋቢ ፊልም ብቻ ሳይሆን በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ኤርትራን ከደቡብ ኮሪያ ጋር እያመሳሰሉዋት ነው።፡ኢትዮጵያዊው ምሁር እንደሚሉት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ህዝቡ አሁንም ኢምፔሪያሊዝምን የሚዋጋ እንደሚመስለው ጠቁመው፣ እንዲህ ያለ የጨለማ አመለካከት በ21ኛው ክፍለዘመን ውስጥ መመለከት አስገራሚ እንደሚሆን ይገልጻሉ።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን “ኢትዮጵያ የጋራ” የሚለውን እሳቤ ልክ እንደ ደቡብ ኮሪያ ዓይነት ያረጀ እሳቤ መሆኑ ምሁሩ ያስታውቃሉ። ኤርትራን አስመልክቶ ሲሽኮረመም የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ አቋሙን ካሳወቀ በሁዋላ በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች “አለ ነገር” የሚያስብሉ ቢሆኑም ለመረጃ ዝግ የሆኑት ኤርትራዊያን በተለያዩ ስልቶች አስቀድመው መረጃ ሊያገኙ የሚችሉበት፣ በውጭ ካሉትም ጋር ውይይት የሚደረግበት አግባብ ሊኖር እንደሚገባ ይገልጽሉ።
በሴፕተምበት 2024 የአሜሪካ መንግስት ሻዕቢያን የሚቃወሙ ድርጅቶችን በገንዘብ መርዳት እንዳለበት የካሊፎርኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካይ እንደራሴ ብራድ ሸርማን ጠይቀው ነበር። ጥያቀው የቀረበው በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የስቴት ዲፓርትመንት (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር) መሥሪያ ቤት ኃላፊን ቃል በተቀበለበት ወቅት መሆኑ ጉዳይ ዝም ብሎ የሪፖርት ማድመቂያ እንዳልሆነ በወቅቱ አስተያየት መሰጥቱ አይዘነጋም።
“The U.S. must support the fight for a free Eritrea” ያሉት እንደራሴው ኤርትራዊ አሜርካውያን ወደ ኤርትራ የሚልኩት ገንዘብ የሚቆምበት መንገድ እንዲፈለግ በማሳሰብ የሻዕቢያን ዋና ገቢ ማምከን ግድ እንደሆነ አመልክተው ነበር።
የዚያው ሰሞን ኤርትራ ተቃራኒ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች እስር ቤት የሚወረወሩባት አገር ሆና መቀጠሏ እንደሚያሳስባት አሜሪካ ስታስታውቅ፣ አሜሪካ ኤርትራ ከ25 ዓመት በፊት ያረቀቀችውን ሕገ መንግሥቷን ተግባራዊ እንድታደርግ፣ ነጻ ምርጫ እንድታካሂድ እና ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጡ እንድትፈቅድ አሥመራ በሚገኘው ኢምባሲዋ በኩል ጠይቃ ነበር።
ኤርትራ ተቃራኒ ሃሳብ ያላቸው ዜጎች እስር ቤት የሚወረወሩባት አገር ሆና መቀጠሏ እንደሚያሳስባት ስትገልጽ እንደተለመደው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገ/መስቀል የአሜሪካ የምርጫ ሥርዓት በገንዘብ የሚዘወር እንደሆነ ገልጸው በትዊተር ገጻቸው ምላሽ ለመስጠት ሞክረዋል። ከሶስት አስርት ዓመት በላይ ያለ ህገመንግስት፣ ምርጫና ዴሞክራሲያዊ የፍትህ ተቋማት የምትንከላወስ አገር ተሽክመው የአሜሪካን ምርጫ የሚተቹት የኤርትራ ባለስልጣናት “እስከመቼ በዚህ ይቀጥላሉ” የሚለው ጉዳይ አሁን ላይ ጎልቶ እየወጣ ነው።
የሶሪያው አምባ ገነን አላሳድ ከስልጣን ሲወገዱ ቲቦር ናጌ በኤክስ ገጻቸው “አሁን የቀረው ኢሳያስ ነው” በማለት አሳባቸውን አጋርተው ነበር። ሰውየው የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሃፊ ወይም ሁለተኛ ሰው እንደመሆናቸው የሚሰጡት አስተያየት ተራ የግለሰብ እንዳልሆነ ይታመናል። በቀርቡም “Amb Tibor Nagy: ‘The #Eritrea|n people are prisoners of one of the largest prison or war camps in the world, and even the diaspora cannot criticize him.” ኤርትራ የዓለም ትልቁ እስር ቤት ወይም የጦር ካምፕ ናት። እንዲህ ያለች አገር ብትሆንም በውጭ ያሉት ዲያስፖራዎች ደፍረው እንደማይተቹ በአንድ ቃለ መጠይቃቸው አመልክተዋል። በዛው ንግግራቸው ይህ የሆነ ምን አልባትም ኤርትራ ለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ህይወት በመስጋት ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ምሁራንም በተመሳሳይ ይህንኑ እያሉ ነው።
ትህነግ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በውጭ አገር ተቃውሞ የሚያሰሙ ዜጎችን ፊልም በማንሳት በአገር ቤት የሚኖሩ ቤተሰቦችን የማስፈራራት፣ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በመመለስ ወዘተ የማሸማቀቅ ስራ ይሰራ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ምንም እንኳን በኤርትራ ለውጥ ቢያስፍልግም ጥንቃቄ እንደሚያሻው የሚገልጹ አሉ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ የሚተሳሰሩበት አግባቦች እጅግ ብዙ ናቸው። ምን አልባትም ዘርዝሮ ማስቀመጥ ይከብድ ይሆናል። ለዚህ ነው ፕሮርፌሰር ብሩክ ኃይሉ “ሻዕቢያንና የኤርትራን ሕዝብ ለይቶ ማየት ግድ ነው” ሲሉ ያሳሰቡት። እዛው ላይ መልሰው ደግሞ ” ኤርትራ የግል፣ ኢትዮጵያ የጋራ የሚለው እሳቤም ሻዕቢያም አርጅተዋል” ሲሉ የፖለቲካውን አተያያቸውን ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ጉዳይ “የመሽኮርመም ፖለቲካ የሚባለውን” ብሄራዊ ጥቅም የማያስጠብቅ አካሄድ በይፋ ቀይሮ ወደ ቀይ ባህር ፖለቲካ ከገባ ብሁዋላ “ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ስትራቴጂክ ጠላት ነው” የሚሉ ወገኖች ትክክል መሆናቸው እየታየ ነው። ሻዕቢያ ኢትዮጵያ የባህር በር ተነፍጋ እንደታነቀች መቀጠል አለባት የሚለው አቋሙ በርካታ ዜጎችን ” አበዙት ካልሆነ ይለይለት” የሚል ብሄራዊ ስሜት እይቀጣጠለ እንደሆነም መረጃዎች ይመሰክራሉ።
ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ድርሽ ማለት የለባትም በሚል ከግብጽ፣ ሶማሊያና ከውስን የአረብ ሊግ አገራት፣ እንዲሁም አገር ቤት ከፈለፈላቸው ተላላኪ ታጣቂዎች ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ዕረፍት የመንሳት መንገድ የሚከተለው ሻዕቢያ መወገድ እንዳለበት ኢትዮጵያዊያን በስፋት እየተናገሩ ነው። ታጣቂዎችን በውክልና እያሰለጠን ወደ ኢትዮጵያ አስታጥቆ የሚያሰርገው ሻዕቢያ በኮንትሮባንድ፣ በውጭ ምናዛሬ አጠባ፣ ለውጭ አገር ዜጎች ባልተፈቀደ ንግድ፣ እንዲሁም ሻዕቢያ በሚያደራጃቸው ነጋዴዎችና የንግድ አግባቦች ኤምባሲውን ጨምሮ ኢትዮጵያን በመመዝበር ላይ የተቸከለ አካሄድን የሚከተለው ሻዕቢያ እያለ ኢትዮጵያ ከቶውንም ሰላም ልታገኝ እንደማትችል አሁን ላይ ድምዳሜ የተያዘ ስለመሆኑ አመልካች ጉድዮች እየተስተዋሉ ነው። ለዚሁም አንዱ ማሳያ የመንግስት ሚዲያዎች ባልተለመደ መልኩ ሻዕቢያን በማንሳት በግልጽ መተቸትና ማስተቸት መጀመራቸው ነው።
“የኢሳያስ አመል፣ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ወዴት?” በሚል ርዕስ በNBC Ethiopia ማብራሪያ የሰጡት የፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ በርካታ የኤርትራ ምሁራን የአገራቸው ሁኔታ ለምን እንደማያሳስባቸው ወይም ዝምታን እንደመረጡ አይገባቸውም። ቀደም ሲል ኤርትራዊያን በንግድ ዘርፍ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ይንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰው ይህ ዛሬ እንደሌለና ኢትዮጵያዊያን ሊጠቀስ በማይችል ደረጃ ኤርትራዊያንን ጥለዋቸው እንደሄዱ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ አሳዛኝ መሆኑንም አመልክተዋል።፡
ለኤርትራ መንግስት ያደሩ ናቸው የሚባሉት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከመሳይ መኮንን ጋር ባደረጉት ውይይት ቢጤ ኢትዮጵያ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን እያሰለጠነች እንደሆነ ጠቅሰው ክስ አሰምተዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሻዕቢያን በዚህ ደረጃ ለመከላከልና በግልጽ ለኢትዮጵያዊያን ሻዕቢያን ወክለው ሲከራከሩ ያደመጡ “ሰውየው የሚታሙበት የባንዳነት ውርስ ጉዳይ እውነት መሆኑን አሳዩን” ሲሉ አስተያየት እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል።
መሳይ በፌስ ቡክና በዩቲይብ ገጽ አስተያየት መስጫ እየቆለፈ ባሰራጨው የራሱና የአቶ አንዳርጋቸው ውይይት ላይ እንደተመለከተው አቶ አንዳርጋቸው አማራ ክልል ላይ ባለው ፕሮጀክታቸው ደስተኛ አይደሉም። እንዲያውም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ታይቶባቸዋል። ለዚህም ይመስላል ስጋታቸውን ለኤርትራ ወገን ሆነው ያሰሙት።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች አየር ኃልን ጨምሮ አሁን ላይ ያለው ቁመናቸው በየዋሻውና ገዳማት ለሚሽሎኮለክ ቡድን ሳይሆን፣ ከዛ ላለፈ ተልዕኮ እንደሆነ ደጋግመው እየገጹ ነው። በተከታታይ በከፍተኛ መኮንኖቹ የሚሰጠውን ጥቆማ የሰሙ መንግስት በሻዕቢያ ላይ የቀድሞውን መንገድ እንደማይከተልና ከሰላም አማራጭ በተጨማሪ በሁሉም አግባብ ሊያስተናግደው በቂ ዝግጅት እንዳለው ይገልሳሉ። ይሁን እንጂ ከመንግስት ኃላፊዎች በቀጥታ ይህን አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም።
ፕሮፌሰር በቀረቡበት የውይይት መርድረክ ላይ አስተያየት ሰጪ ሆነው የታዩት ሌላ የወራቤ ዩኒቨርስቲ መምህርና የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን በማገባደድ ላይ የሚገኙት መሀመድ አወል በኤርትራ ለውጥ የማይቀር በመሆኑ ጥንቃቄ እነድሚያሻ ይናገራሉ። ተተኪው መዘጋጀት እንዳለበት ይመክራሉ። ኢሳያስን ሁለት ሶስተኛውን ህዝብ በደህነት አረንቋ የከቱት፣ አገሪቱን በ21 ክፍለዘመን ጨለማ ውስጥ የቀረቀሩ፣ አምራጭ ዜጋው አገር ጥሎ እንዲኮበልል ያደረጉ፣ ፍሱም አምባገነን መሆናቸውን አመልክተዋ ኢሳያስ አፉወርቂ ድንገት ቢወገዱ ለኢትዮጵያም ስጋት ስለሚሆን ከስንብታቸው ጋር የተተኪው ጉዳይ በጥልቀት ሊሰራበትና ኤርትራዊያን በስፋት እንዲመክሩበት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ዘዴ ያሉትንም ጠቁመዋል።
በውጭ ካሉ ኤርትራዊያን ጋ የጋራ ምክክር መደረግ እንዳለበት የጠቆሙት ምሁሩ ኢሳያስን የሚተካ መመቻቸት እንዳለበት ጠቁመዋል። ይፋ ያልሆን ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ኢሳያስን የሚተኩ የተቃዋሚ ኃይሎች ራሳቸውን እያዘጋጁ እንደሆነ ይገልጻሉ። ተከታታይ ስብሰባ በማድረግ የሽግግር ህገ መነግስት ማዘጋጀታቸውንም የሚጠቁሙ አሉ።
ኢሳያስም ይህን የተረዱ በመሆኑ አማራ ክልል ያለውን ጦርነት በዋናናት ቀድመው ማስጀመራቸውን የሚናገሩ አሉ። እነ አቶ አንዳርጋቸው የዚህ ኦፕሬሽን አካል የሆኑት በዚሁ ሳቢያ እንደሆነ እነዚሁ ክፍሎች በማስረጃ ይገልጻሉ። ይህንኑ ዘመቻ እንዲያግዙ የተመረጡ ሚዲያዎችም የአማራ ክልልን ረብሻና ጦርነት ከሚፈለገው በላይ የሚያጦዙት በተልዕኮ እንደሆነ ያብራራሉ። እማራ ክልል የተለኮሰው ጦርነት በሚፈለገው መጠን የሻዕቢያን ፍላጎት ባለማርካቱ ከትህነግ ጋር የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት መጀመሩ ከስጋት ለመዳን በሚል እንደሆነም እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
“ገፋ ሲደረግ ይወድቃል” የሚባለው የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም ጉዳይ ገልብጦ እዚህ ደረጃ መድረሱ ለኤርትራው መሪ ስጋት መሆኑ ቀድሞም የሚጠበቅ እንደሆነ አስተያየት የሚሰጡ “ኢሳያስ በስደትና በማሸማቀቅ ለገደሉት ህዝባቸው የሚያስቡ ከሆነ እጃቸውን ከኢትዮጵያ በማንሳት ለለውጥ ይስሩ”ሲሉ መክረዋል።
እንኳን አንድ አገር አልቃይዳ እንኳን ምክትል እንዳለው ጠቅሰው የሚናገሩ የኢትዮጵያ ህዝብና የኤርትራ ህዝብ የተያያዘበት ቁምነገርና የተጣመረበት መስተጋብር እንዲሁ እንደ ሌሎች ዓይነት ተራ ባለመሆኑ ፖለቲከኞች በሚወስኑት ውሳኔ ሁሉ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ እንዲከቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አስተያየት ሰጪዎች በተደጋጋሚ ይመክራሉ።
የራሳቸው ጉዳይ እያለ በየጊዜው የኢትዮጵያን ጉዳይ ሰዓታት ሰጥተው ለኤርትራ ህዝብ በትግርኛ የሚደሰኩሩት ኢሳያስ በበርካታ ጉዳዮች የተሳሰሩትን የሁለቱን አገር ህዝብ ለማቀራረብና በከብር ለማለፍ ከወዲሁ እንዲያስቡ የወራቤ ዩቨርስቲው መምህር መክረዋል።