መንግስት ሙስናና ግልጽ ሌብነትን፣ በአንድ ጀንበር ባለሃብት የሆኑትን፣ በበእርሃን ፍጥነት የትላላቅ ንብረት ባለቤት የሆኑትን አስመልክቶ ዝምታ መምረጡ በእጅጉ ሲያስወቀሰው እንደነበር፣ አገሪቱን “ሙስና” እየተባለ በቁልምጫ ስም የሚጠራው ሌብነት እየፈተናት እንደሆነ በመሪዎች አንደበት በተለያዩ ጊዜያ ቢገለጽም ከወሬ በዘለለ ዋናዎቹን ሻርኮች የማይነካ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ዓመታት አልፈዋል።
ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ሌላ ኮሚሽን ሊቋቋምበት እንደሚገባ በመጠቆም ተስፋ የቆረጡ መንግስትን ሲያወግዙ ኖረዋል። ሌብነቱም ሌባውም መንግስት እንደሆነ በመጥቀስ በድፍረት የሚናገሩና፣ ሕዝብም ስም እየጠራ የሚጠቋቆምባቸው ንብረቶችና “ባለሃብቶች” ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም።
ከለውጡ በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ሙስና አትበሉ” በማለት ተግባሩን በትክክለኛ ስሙ “ሌብነት፣ ሌባ” ተብሎ መጠራት እንደሚገባው በመጥቀስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የሚመሩት ብሄራዊ ኮሚቴ ከፍተኛ ጥቆማዎች ደርሰውት እንደየአግባቡ እየተኬደባቸው እንደሆነ ሲጠቆም፣ ዋናው ችግር የህግ አለመኖር እንደሆነ በተጓዳኝ ተገልሶ ነበር።
የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የብሔራዊ የሙስና ወንጀል መረጃ ጥቆማ የዲጂታል አሰራር ሥርዓት መተግበሪያ ማስጀመሪያ መርሐግብር ይፋ ሲያደርጉ ተመስገን ጥሩነህ ቁርጥ አቋም መያዙን አስታውቀውም ነበር።
ይህ ሁሉ አልፎ ዛሬ በሕገ-ወጥ ድርጊት በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል። አዲስ የወጣውን ህግ ተከትሎ ማጭበርበር የፈጸሙ መያዛቸውንም አመልክቷል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በሰጠው መግለጫ የፋይናንስ ወንጀሎች በሀገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘርፈ ብዙ እና ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ህጎችን አውጥታ በመተግባር እንደምትገኝም አስገንዝቧል፡፡ መግለጫው ቃል በቃል ባይገልጸውም ቀደም ሲል እርምጃ ለመውሰድ አመቺ ያልሆነው የህግ ክፍተት ተደፍኗል። በተለይም በህገወጥ የተገኘ ሃብትን ህጋዊ የማድረግ አካሄድ በስፋት ሌቦች የተረባረቡበት በመሆኑ ንብረት የማስመለስ አዋጅ ሲጸድቅ ከፍተኛ ጫጫታ ተሰምቶ ነበር።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 እየተተገበረ መሆኑ አገልግሎቱ ዋቢ አግርጎ በመገለጫው አመልክቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በተለያዩ ህጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የህግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁን አስታውሷል፡፡
የንብረት ማስመለስ አዋጁም ሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የወጣው አዋጅ ዓላማ የፋይናንስ ወንጀሎች አትራፊ አለመሆናቸውን በማረጋገጥ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ሁሉን አቀፍ አደጋ መግታት ነው ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ለጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው ያስረዳው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግለሰቦች ህጎችን ለማደናገሪያነት በመጠቀም እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን አካላትን ስም በመጥቀስ በማጭበርበር እና በማስፈራራት ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸው ክትትል በማድረግ የተደረሰበት መሆኑን ገልጿል።
በዚህም በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ 3 ግለሰቦች ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እጅ ከፍንጅ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡ ሌሎችንም በቁጥጥር ስራ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
አገልግሎቱ ከራሱ ምንጮችና ከጥቆማ በሚደርሱት መረጃዎች መሰረት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብሏል።
በርካታ ጉዳዮችም በህግ ተይዘው ይገኛሉ ያለው አገልግሎቱ÷ የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የሚወስዳቸውን ርምጃዎች የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል።
ህብረተሰቡም ማጭበርበርን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ወንጀል በመፈጸም የሚገኝን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሲመለከት በ9796 ነፃ ስልክ ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡