ሰሞኑን በአፋር ክልል የደረሰውን ርዕደ መሬት ለመመልከት ከሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት የተሰማራው ቡድን በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።
ከምክር ቤቱ የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት እንዲሁም ከውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳየች ቋሚ ኮሚቴዎች የተውጣጣ ቡድን በአፋር ክልል ርዕደ መሬት የጠፈናቀሉ ዜጎችን ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ ምልከታ አድርጓል፡፡
በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም በዕቅድ ተይዞ የተሟላ መረጃ በማሰባሰብ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ሞጋ አባቡልጉ አስገንዝበዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ በማዋቀር የተጎዱ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁሉም ዜጋ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለው የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የምክር ቤት አባሉ የተከበሩ አቶ ሞጋ አመላክተዋል፡፡
ተፈናቃዮች የሚሰፍሩበት ቦታ ከርዕደ መሬት የስጋት ቀጠና ነፃ መሆኑን በጥናት የተረጋገጠ መሆን እንዳለበት የቡድኑ አባላት አስገንዝበዋል፡፡
ከጤና አኳያም ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስፈላጊውን የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ የተከበሩ ወ/ሮ ነቢያት ጥላሁን አሳስበዋል፡፡
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መሰረታዊ የሆኑ መድኃኒቶችን በወቅቱ ማቅረብ እንደሚገባ የተከበሩ ወ/ሮ ነቢያት ጥላሁን አክለው ጠቁመዋል፡፡
የህክምና መገልገያ ግብአቶች የሚከሰተውን በሽታ መሰረት ባደረገ መልኩ አቅርቦት ሊኖር ይገባል ሲሉ የተከበሩ ወ/ሮ ነቢያት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሰብአዊ እርዳታ የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ እና የመድኃኒት አቅርቦት በቀጣይነት ሊቀርብ እንደሚገባ የቡድኑ አባላት አሳስበዋል፡፡
ለዜጎች የሚደረገው የሰብአዊ እርዳታ ፍትሃዊነትን በጠበቀ እና ከቅሬታ ነጻ መሆን እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በአፋር ክልል የፈንታሌ ወረዳ ተመራጫ የተከበሩ ወይዘሪት ፋጡማ አሊ ጠቁሟል፡፡
የተከበሩ ወይዞሪት ፋጡማ አሊ አያይዘውም በቀጣይ ምክር ቤቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አሰፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአፋር ክልል የጋቢረሱ ዞን ሶስት ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ አሊ በተፈናቃዮች ዘንድ እየተነሱ ያሉ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተዋቀረው ኮሚቴ የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በርዕደ መሬቱ አደጋ የተጎዱ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፤ የጤና፣ የግብርና ማሳዎች እና የትምህርት ተቋማት መበኖራቸው የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በየዘርፋቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ እንዲያደርጉ ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አያይዘውም፤ በክልሉ በርዕደ መሬቱ የተፈናቀሉ ከ54 ሺህ በላይ ዜጎችን ለማገዝ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዜና ፓርላማ