ሁኔታው በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ሰዓት ሊፈጠር ይችላል፤ በተለይ የስምጥ ሸለቆን ታከው የሚገኙ ከተሞች፤ ይህ መረጃ አስፈላጊ በመሆኑ ለሌሎችም ያካፍሉ፤ ያዳርሱ፡፡
==የመሬት ውስጣዊ አወቃቀር==

መሬት ሙሉ በሙሉ በጠጣር ቁስ የተሞላች አይደለችም፡፡ መሬት የተዋቀረችው ከሦሥት ዋና ዋና ንብርብር ንጣፎች ነው፡፡ እነርሱም፡- ቅርፊተ አካል(Crust)፣ የምድር ማዕከል ንጣፍ(Mantle) እና ውስጠ እምብርት(Core) ናቸው፡፡ (አወቃቀሩ በስዕላቂ መግለጫ ውስጥ ይገኛል ተመልከቱት፡፡)
• ቅርፊተ አካል(Crust)፡- ይህ ስስ የሆነ የመሬት የላይኛው ንጣፍ ነው፡፡ እኛ የምንንቀሳቀስበትን የመሬት ወለል ይወክላል፡፡
• የቀለጠ አለት(Mantle)፡- ይህ በመሬት ቅርፊተ አካል እና በመሬት ውስጠ እምብረት መከካከል ቀልጦ የሚዋልል የቀለጠ አለት ነው፡፡
• ውስጠ እምብርት(Core)፡- ይህ የመሬት ውስጠ እምብርት ክፍል ሲሆን ስሪቱም ብረት ነው፡፡
==የመሬት ውስጠ እምብርት ምን ያክል ሞቃት ነው?==
የዚህን ጥያቄ መልስ ማንኛውም ተመራማሪ በእርግጠኝነት ይህን ያክል ነው ብሎ አይናገርም፤ ነገር ግን የውስጡ ክፍሎች በጣም ሞቃት እንደሆኑ የሚመሰክሩ ማስረጃዎች በመሬት ገፅታዎች ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ሁኔታም በእሳተ ገሞራዎች ፍንዳታ እና ቀልጠው በሚፈሱ አለቶች መልክ ማየት ይቻላል፡፡
==መሬት መንቀጥቀጥ==

የመሬት ዉጫዊው ክፍል በተለያዩ ቅርፊት መሰል አካላት(plates) የተሸፈነ ነዉ፡፡ የነዚህ ቅርፊት መሰል አካላት ዉፍረት በአማካይ ከ(20-60) ኪ.ሜትር ወደ መሬት ስር ይዘልቃል፡፡ እነዚህ ቅርፊት መሰል አካላት በመካከላቸዉ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የኃይል መጠራቀም ይፈጥራል፡፡ የኃይል መጠራቀሙም እየጨመረ ይሄድና የአለቱ አካል ሊሸከመዉ ከሚችለዉ አቅም በላይ ሲሆን ይደረመሳል፡፡ ይህ በከፍተኛ ጫና ታፍኖ የነበረ ኃይል በድንገት ሲያፈነግጥ የሚወጣዉ ከፍተኛ ኃይል በመሬት የላይኛዉ ቅርፊት አካል ላይ በሞገድ መልክ በፍጥነት ይሰራጫል፡፡ የዚህን ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተፈጠረ ወይም ተከሰተ እንላለን፡፡ የነዚህ ቅርፊት መሰል አካላት እንቅስቃሴ ሁኔታ እና መጠን እንደየአካባቢዉ ይለያያል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ ጥናት ሴስሞሎጂ (Seismology) ይባላል፡፡ ቃሉም የግሪክ (Seismos) ሲሆን ትርጉሙም መንቀጥቀጥ ማለት ነዉ፡፡
እነዚህ ቅርፊት አካሎች(Plates) አንዱ ከሌላዉ የሚለይበት እጅግ በጣም ረዥም የሆነ ስንጥቅ ይገኛል፡፡ ይህ ስንጥቅ የተለያዩ መዛነፎችን ይፈጥራል፡፡ ይህ አጠቃላይ ስንጥቅም የዝንፈት መስመር(fault line) ይባላል፡፡ በዝንፈት መስመር የሚለያዩ ቅርፊተ አካሎች(Plates) እጅግ ግዙፍ እንደመሆናቸዉ መጠን አንደኛዉ በሌላኛዉ ላይ ተፅዕኖ ማድረሳቸው የማይቀር ነዉ፡፡ በመሆኑም እነኚህ የተለያዩ ቅርፊተ አካሎች እርስ በርሳቸዉ በተቃራኒ አቅጣጫ አንዱ ከሌላኛዉ ሊሸሽ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ ቅርፊተ አካሎቹ እርስ በርሳቸዉ ተደጋግፈዉ የሚኖሩበትን መንገድ ስለሚያመክን በከፍተኛ ጫና ምክንያት አለቶቹ ተያይዘዉ እንዲደረመሱ ሲያደረግ ታምቆ የቆየዉ ኃይል በማፈንገጥ የሚለቀዉ ኃይል ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ማዕከላዊ ቦታ የሚነሳዉ ከፍተኛ ሞገድ በሁሉም አቅጣጫ በመሰራጨት እረጃጅም ስንጥቅ መስመሮችን እየሠራ በመቀጠል የላይኛዉን የመሬት ንጣፍ ገፅታ ያመሰቃቅላል፡፡
ከተፈጥሮአዊ ምክንያቶች በተለየ ሁኔታ የሰዉ ልጅ አንዳንድ እቅስቃሴዎችም የመሬት መንቀጥቀጥ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የተለያዩ መርዛማ ዝቃጮችን ለማስወገድ ተብለዉ የሚቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች፣ ዉሃ ለማከማቸት ተብለዉ የሚቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች፣ በመሬት ዉስጥ ለዉስጥ ለኒዩክለር ጦር መሳሪያ ሙከራዎች የሚቆፈሩ መተላለፊያዎች፤ ሰዉ ሰራሽ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የእነዚህ ድርጊቶች መስፋፋት ከተፈጥሮአዊዉ የመሬት መንቀጥቀጥ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተፅእኖ በመፍጠር የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያስከትል ይችላል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያስከትለዉ ዉድመት አደጋዉ የደረሰበት አካባቢ ያለዉ የመሬት አቀማመጥ፣ መንቀጥቀጡ የሚቆይበት ጊዜ እና መንቀጥቀጡ የሸፈነዉ ክልል ይወስነዋል፡፡ ህንፃዎች የተሠሩበት የንድፍ ዓይነት እና ለግንባታ ጥቅም ላይ የዋለዉ የቁስ ዓይነትም የአደጋዉን አስከፊነት ሊጨምርም ሆነ ሊቀንስ ይችላል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ ማስተዋል ከምንችለዉ በጣም ዝቅተኛ የንዝረት መጠን አንስቶ እስከ ብዙ ሺህ ኪ.ሜትሮች የሚደርስ የሞገድ ነዉጥ ሊፈጥር የሚችል ነዉ፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ በመሬት ላይኛዉ ቅርፊተ አካል ላይ የሚገኙትን ህንፃዎች ፣ድልድዮች እና ግድቦች እንዲፈርሱ በማድረግ በአጭር ጊዜ ዉስጥ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ከባህር ወይም ከዉቂያኖስ ከፍተኛ የሆነ የዉሃ ሞገድ ሱናሚ(Tsunami) በማስነሳት እና ወደ የብስ በማምጣት ለመገመት የሚያዳግት ጥፋትን ያደርሳል፡፡ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተተክለዉ የሚገኙ መሳሪያዎችም የመሬት መንቀጥቀጦችን ከተለያዩ ቦታዎች ላይ በየቀኑ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ዉስጥ አደጋ የመፍጠር አቅም ያላቸዉ በጣም ጥቂቶች ናቸዉ፡፡
ባለፉት 500 ዓመታት በዓለማችን ላይ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸዉን በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት አጥተዋል፡፡ የብዙ አገራት የመሠረተ ልማት አዉታሮች እና ንብረቶች እንዳልነበር ሆነዉ አልፈዋል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥን ቀድሞ መተንበይ በጣም አዳጋች ቢሆንም በቂ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ፡-ለምሳሌ ስለ አደጋዉ ትምህርት በመስጠት፣ የአደጋ ጊዜ እቅዶችን በማዉጣት እና በማሰልጠን ፣ጠንካራ እና ተጣጣፊ(ከሁኔታዉ ጋር የሚስማማ) ንድፍ ለህንፃዎችም ሆነ ለሌሎች መሠረተ ልማቶች በመጠቀም ሊደርስ የሚችለዉን አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል፡፡
==ዝርግ ንጣፎች እንዴት ይንቀሳቀሳሉ?==

ዝርግ ንጣፎች የጎንዮሽ በተቃራኒ አቅጣጫ ሊፋጩ ወይም በተቃራኒ አቅጣጫ ተቀራርበው ሊገፋፉ ወይም በተቃራኒ አቅጣጫ ሊራራቁ ወይም በተቃራኒ አቅጣጫ በቁመታቸው ሊፋጩ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እነኝህ ንጣፎች የሚገናኙበት ቦታ መረጋጋት የተሳነው እና ብዙ ክንውኖች ያሉበት ቦታ ነው፡፡ ለምሳሌ በስዕል እንደምትመለከቱት ሁለት የተለያዩ ዝርግ ንጣፎች በተቃራኒ አቅጣጫ ቢራራቁ በሁለቱ ዝርግ ንጣፎች ታፍኖ የነበረው የቀለጠ አለት በከፍተኛ ኃይል መገንፈሉ የማይቀር ነው፡፡ ያም ካልሆነ ደግሞ በሁለቱ ዝርግ ንጣፎች በተቃራኒ አቅጣጫ መራራቅ ምክንያት(የአብዛኞቹ ስምጥ ሸለቆዎች የተፈጠሩበት መንገድ) የሚፈጠረው የአለቶች መናድ ከፍተኛ ንዝረቶች በመፍጠር መሬትን ማንቀጥቀጡ የማይቀር ነው፡፡(ስዕላዊ መግለጫዎችን ይመልከቱ)
በዝንፈት መስመር(የቅርፊተ አካሎች መዋሰኛ) ላይ በእንቅስቃሴዎቹ ምክንያት የሚፈጠረው ከፍተኛ ጫና የሚፈጥረው የኃይል መጠራቀም አለቱ መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ ሲሆን የሚከሰተው የአለቶች መሰባበር እና መደርመስ በሁሉም አቅጣጫ ሞገዱ በመሰራጨት እና ከፍተኛ ንዝረት በመፍጠር የመሬት መንቀጥቀጥን ያስከትላል፣ የመሬት ገፅታም ምስቅልቅሉ ይወጣል፡፡
==የመሬት መንቀጥቀጥ ልኬት==

የመሬት መንቀጥቀጥ ልኬት የሬክተር ስኬልን(Recter scale) በመጠቀም ይከናወናል፡፡ ዘዴው የሚጠቀመው የሂሳብ ቀመሮችን በመሆኑ በጣም ልከኛ ነው፡፡ ትልቅ ቁጥር ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያመለክተው ትልቅ ጥፋትን ነው፡፡ በስዕል ውስጥ ያለውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡፡
አንድ የሬክተር ስኬል ቁጥር ከቀዳሚው ቁጥር በአስር እጥፍ ኃያል ነው፡፡ ይህንን የመሬት መንቀጥቀጥ የሚለካው መሳሪያ ሳይስሞግራፍ(Seismograph) ይባላል፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የሚወሰዱትን የሬክተር ስኬል(Recter scale) መረጃዎች በንፅፅር በማየት የመሬት መንቀጥቀጡ ከየት አካባቢ እንደጀመረ ለመለየት ይረዳል፡፡
በክፍል ሁለት የመሬት መንቀጥቀጥ በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ምን ይመስላል? ሁኔታው ያሰጋናል ወይ? የሚለውን እንመለከታለን፡፡ ወደፊት በክፍል ሦሥት ደግሞ ሁኔታው ሲፈጠር ምን አይነት ፈጣን እንርምጃ እንውሰድ የሚለውን እናያለን፡፡

(ክፍል አንድ – እ እ አ 2016 ላይ የተፖሰተ ነው)