ወልድያ፡ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ንጉሥ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፣ እንደ ቅዱስ በቅድስና ከሰማየ ሰማያት ይወጣል። እንደ ንጉሥ ለሕዝቦቹ ፍርድን ይሰጣል፤ እንደ ቅዱስ በጸሎቱ ምህረትን ያሰጣል። እንደ ካህን ኪዳን ያደርሳል፣ አሀዱ ብሎ ይቀድሳል፤ ያወድሳል። እንደ ቅዱስ በቅድስና ይመላለሳል።
የቤተ መንግሥት ንጉሥ፣ የቤተ ክህነት ቅዱስ ነው። ንግሥናው ቅድስናውን አላስረሳውም። አድናቆት እና ሙገሳ አላስታበየውም። ከንግሥናው ሳይጎድል፣ ከቅድስናውም ዝቅ ሳይል በትህትና ኖረ እንጂ። ቃሉ ትደመጣለች። ምክሩ ትሰማለች። ሰላምታው ትናፈቃለች። አኗኗሩ ታስቀናለች።
እንደ አብርሃም በድንኳን ያድራል፤ ለጌታው ግን በአለት ላይ ቤት ይሠራል። እንደ አጣ ሰው ይራባል፤ የተራቡትን ግን ያጠግባል። እንደ ንጉሥ እጅ ንሱልኝ ከማለት ይልቅ በነጋ በጠባ ለአምላኩ እጅ ይነሳል። በምትጣፍጥ አንደበቱ የአምላኩን ስም እየጠራ ያወድሳል።
በጸሎት፣ በስግደት ይበረታል። በቅድስናው ጥበብ ተገለጠለችለት። አለት እጅ ሰጠችለት። ምድርን ሰማይ አደረጋት። ሰማይንም በምድር ሠራት። ቅድስቲቱን ሥፍራ ለዓለም ሁሉ ገለጣት። የምሥጢር ማኅተም አተመባት። የማይጠፋ ቃል ኪዳን አኖረባት። ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ።
መጽሐፍ እንዲህ ይላል የአማኞች ንጽሕናም ከስጋው አራቀም። የመላእክት ትጋት ሀብት ከእርሱ ጋር ትኖራለች። የሁሉም የአምላክ ወዳጆች በረከትም በመሐል ራሱ አለች።
የበዛች የበጎ ሥራው ድካም ከእነርሱ ጋር አስተካክለዋለችና። ጻድቅ ነው። ሰውነቱ በጭምትነት በትር የተቀጣ ነውና። ሰማዕትም ነው፤ የበደለው ሳይኖር በግፍ ከሀገር ወደ ሀገር ሲሰደድ እና ሲቀጣ ኖሯልና።
ታላላቆቹም መረቁት፤ እርሱ ከፍ አድርጓቸዋልና። ሽማግሌዎችም መረቁት፤ እርሱ በእርጅናቸው ደግፏቸዋልና። ሕጻናትም መረቁት፤ እርሱ አሳድጓቸዋልና። ድሆችም መረቁት፤ እርሱ አረጋግቶ አሳድጓቸዋል። ድህነታቸውን እስኪረሱ ድረስ ለቅሷቸውን አስጥሏልና።
ባልቴቶችም መረቁት፤ እርሱ ከሀዘናቸው አረጋግቶ ችግራቸውን አስወግዷልና። ባለጸጎችም መረቁት፤ እርሱ አክብሯቸዋልና። የተጋፋቸውም ነገር የለምና። የእርሱን ከመስጠት በስተቀር ከእነርሱ የወሰደባቸው የለምና።
ችግረኞችም መረቁት፤ እርሱ ለአሰቡት ሁሉ እየረዳ መጠጊያ ኾኗቸዋልና። የታረዙትም መረቁት እርቃናቸውን ሸፍኗልና። የተራቡም መረቁት እርሱ መግቧቸዋልና። የተጠሙትም መረቁት፤ እርሱ በጣፈጠ ባማረ መጠጡ አርክቷቸዋልና።
ባሕታውያንም መረቁት እርሱ ረዳት እና መጋቢ ሁሉንም በሁሉ ኾኖላቸዋልና ተብሎ ተጽፏል።
ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ለንግሥናውም ለቅድስናውም የተመቻቸ እና የተገባ ነው።
የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዲያቆን ተካ ውቤ ቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያን ያስዋበ፣ ንጉሥም፣ ካህንም፣ ቅዱስም ኾኖ ኢትዮጵያን የመራ ታላቅ ነው ይላሉ። በአካለ ነፍስ ወደ ሰማይ ያረገ በሰማይ የተመለከታቸውን በምድር የሠራ፣ ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙበትን ያነጸ ቅዱስ ነው።
መላእክት የሚመሩት፣ የሚያግዙት፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የሚገለጥበት ንጉሥም ቅዱስም ነው ይላሉ። ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያን በአራት አሥተዳደር ከፍሎ ያሥተዳደረ፣ ትሁት፣ ደግ እና ቅን ነበር ነው የሚሉት። የአሥተዳደር ሥርዓቱ ጥበብ የተመላበት። በፍቅር የሚመራ ነውም ይላሉ።
አምላክ የሚመሠገንባቸውን፣ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ የምትታይባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ያነጸ። አምሣለ ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ የሠራ ታላቅ ነው። ፍቅርን እንጂ ጠብን የማይወድ፣ ሀገሩን የሚያስከብር ነው ይሉታል።
የእርሱ የእጅ ሥራዎች ቅድስናውን የሚመሰክሩለት፤ ታላቅነቱን የሚገልጡለት፤ የጥበብ ቀንዲልነቱን የሚያሳዩለት፤ ኢትዮጵያን ያንቆጠቆጠ፣ በክብር ዙፋን ላይ ያስቀመጠ ነው ይላሉ።
ቅዱስ ላሊበላ ኀያላን የሚያከብሩት፣ በሩቅ ያሉት እና አሳዳጅ የበዛባቸው ይታደገናል፤ ጠላቶቻችን በኀይሉ ድል ይነሳልናል ብለው የሚጠብቁት ታላቅ ነው ይሉታል። የእርሱ ኀይልም መንፈስ ቅዱስ ናት። ከእጁ የሚሰጠው እስከሚያጣ ድረስ ለደሀዎች የሚሰጥ ሩህሩህ ነው።
ቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያ በዓለሙ ፊት ጎብኚዎች እንዲበዙላት፤ አድናቂዎቿ እንዲበረክቱላት፣ አብያተ ክርስቲያናትን የሠራ፤ የኢትዮጵያውያንን የቀደመ ጥበብ ያሳየ ድንቅ አባት ነው። የኢትዮጵያን ታላቅነት በአለት ላይ ያሰረጸ ነውም ይሉታል። የእርሱ የእጅ ሥራዎች የማንነት መገለጫዎች ናቸው።
የእርሱ ከተማ የቀደመችዋ ሮሃ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ መብራት ናት። ሮሃ ማለት የጸዳ፣ ንጹሕ፣ ቅድስና ያለበት ቦታ ነው ይላሉ። በደብረ ሮሃም ሰው እና መላእክት ይገናኛሉ።
በደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ በዓለም ላይ የማይስማሙ ንግሥና እና ቅድስና የተስማሙለት ቅዱስ ነው ይላሉ።
የዚህ ዓለም የመጨረሻ አክሊል የንግሥና አክሊል ነው፤ የዚህኛው የዓለም የመጨረሻ የደስታ አክሊል የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርስ ቅድስና ነው።
ላሊበላም የዚህኛውም የዚያኛው የደስታ አክሊል የተስማሙለት ነው ይላሉ። ጦር ሳያነሳ ሀገር እና ሕዝብ ይገብርለታል። እንደ ንጉሥነቱ ፍትሕ ይሰጣል፤ እንደ ካህንነቱ እግዚአብሔር ይፍታህ ብሎ ከሐጥያት ይፈታል ብለዋል።
እርሱ ማዕከላዊ መንግሥት አለው። ወደ ሰማይ ለእግዚአብሔር፣ ወደ ምድርም ለሰው የቀረበ መንግሥትን ይዟልና። በዘመኑ ሰዎች ያላለቀሱበት፤ ደሀዎች ያልተበደሉበት ነው ይላሉ። መንግሥትነትን በሕዝብ ዘንድ ያስወደደ፣ ሀገርን ሰላም ያደረገ፣ ሕጻናትን ያሳደገ፤ ኀይሉ ክህነቱ የኾነ፤ ክህነቱ ለንግሥናው አብነት የኮነችው ጻድቅ ነው ይሉታል ሊቁ።
ሀገርን አንድ ያደረገ፣ ለኢትዮጵያ ጌጧን የሰጣት፣ ሰማይን በምድር ያበጃትም ነው ይላሉ ሊቁ። በሰማይ ሀገር አለን እንላለን፤ የሰማይ ሀገራችን ደግሞ ላሊበላ ቀርጾ አስቀምጦ ያሳየናል።
ሰማይና ምድርን አንድ አድርጎ ሰጥቶናል። የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አምሳያቸው በምድር የለም። በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ያለ ምክንያት እና ያለ ምልክት የተሠራ የለም። ሁሉም ሃይማኖትን ይናገራል እንጂ ነው የሚሉት።
ላሊበላ በጨለማ ውስጥ የሚያበራ እንቁ ነው። ቅዱስ ላሊበላ ሰባት ጊዜ የነጠረ የወርቅ ጽዋ ነው። ቅዱስ ላሊበላ የጥፋት ትል ጥርስ ያልነካው ስንዴ ነው ተብሎ ተጽፏል።
በምድር ንጉሥ፣ በሰማይ ቅዱስ ነውና እንደተመሠገነ ይኖራል፤ በትውልዶች ሁሉ ይዘከራል።
አሚኮ
TIPS
Growing relations between Israel and Ethiopia: between military deals, intelligence influence, and an eye on Egypt
The Wars We Still Can Stop
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security