ማሳሰቢያ! …ስለዚህ ዱቄት አውቃለሁ የሚል ማንም ሰው እዚህ ፖስት ስር የንጥረነገሩን ስምና ተያያዠ መረጃዎች ቢጽፍ ወንጀል እያስተማረ መሆኑን ፣ ለዚህም ተጠያቂ እንደሚሆን አስቀድሞ ይወቀው፡፡
ይህ ጽሁፍ ረዘም ቢልም በጣም ይጠቅማችኋል፡፡
#Ethiopia | ነገርየው በተለምዶ “አፍዝ አደንግዝ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው በእጃቸው ያለ ወርቅ ይሁን ሞባይል፣ ብር ይሁን መን ሳይቀራቸው ያለ የሌለ ንብረታቸውንና ያም ሳይበቃ በባንክ ያለ ገንዘባቸውን በኤቲኤም አውጥተው ለሌቦች ያስረክቡና ጥቂት ቆይተው ሲነቁ ራሳቸውን ያልጠበቁበት ስፍራ ላይ ያገኙታል፡፡ ፖሊስ ጋር ሄደው ያመለክታሉ፡፡ ወይም ቲክቶክና ዩቲቱብ ላይ መጥተው “እንዲህ እንዲህ ሆኖ ይህ ወንጀል ተፈጸመብኝ” ይላሉ፡፡ ወንጀል የተፈጸመባቸው መሆኑ ባያጠራጥርም ‘ገና ሲነካኝ ፈዘዝኩ ፣ደነዘዝኩ፣ ከዚያ በኋላ የሆነውን አላስታውስም’ የሚሉትን ነገር ግን ብዙም ሰው አያምናቸውም፡፡
እኔም አንድ ወቅት የገዛ እህቴ እና እናቴ በተለያየ ጊዜ የዚህ ወንጀል ሰለባ ሲሆኑ ያሉትን ማመን ቸግሮኝ ነበር፡፡ እናቴ ‘የልጄ ማስታወሻ’ የምትለውን የወርቅ ቀለበትና ቦርሳዋ ውስጥ የነበረ ገንዘቧን ፣ እህቴ ደግሞ ሞባይልና ባንክ የነበረ ብሯን በተለያየ ጊዜ ለሌቦች አስረክበው ‘ያደረግነውን ሁሉ አናውቅም ነበር፣ ስንነቃ ራሳችንን ያልጠበቅነው ቦታ አገኘነው’ ብለው የነገሩኝን ታሪክ በሙሉ ልቤ ለመቀበል ተቸግሬ ነበር፡፡
በቅርብ እስከማውቀው ድረስ ፖሊስም በርካታ ይህንን መሰል አቤቱታዎች የቀረቡለት ቢሆንም በዚህ መንገድ የተፈጸመንና ፈጻሚውን ለማወቅ የሚያስቸግርን ወንጀል ለማጣራት አዳጋች ይሆንበታል፡፡ ማስረጃና ማረጋገጫ ስለማያገኝም አንዳንዴ ‘በዚህ ሁኔታ የሚፈጸም ወንጀል አለ’ ብሎ ለመቀበል ይቸገራል፡፡ ወንጀሉን “ማታለልና ማጭበርበር” በሚለው ርዕስ ላይ ብቻ መዝግቦ ያልፈዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ወንጀለኞቹ አይያዙም፡፡ተጎጂዎችም ሁሌም ስጉ ሆነው ይቀራሉ፡፡ አንዳንዶች ስለማይተማመኑ ተዘረፍን ባሉት ንብረት ሳቢያ ከትዳር አጋራቸውና ከቤተሰባቸው ተጣልተው ቀርተዋል፡፡ በዚህ መሃል ሌሎች ዜጎች በተራ በተራ የወንጀል ሰለባ እየሆኑ ይመጣሉ፡፡ በቀላል አማርኛ ከተማችን ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ይኸው ነው፡፡
እውን ግን “አፍዝ አደንግዝ” አለ?
ዛሬ የምነግራችሁ ብዙዎች “ሃሳብ የፈጠረው ቅዠት” ስለሚሉትና መኖሩን ስለማይቀበሉት (መሪጌታ ነን ባይ ሃሳዊዎችን ጥንቆላ ተዉትና) በተለምዶ ‘አፍዝ አደንግዝ’ ተብሎ ስለሚጠራው ንጥረ ነገር ነው፡፡ ‘አፍዝ አደንግዝን’ ብዙዎች ለወንጀል ተግባር መገልገያነት እያዋሉት መሆኑን ከበርካታ አቤቱታዎች ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ ይህንን ነገር ስጽፍ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ገብቼ መረጃውን አንዳንድ ዋልጌዎች ለመጥፎ ተግባር እንዳይጠቀሙበትና ለጥፋት እንዳያውሉት እየተጠነቀቅኩ በመሆኑ ፣ እየሸፋፈንኩ ባለፍኳቸው ነገሮች ቅር እንዳትሰኙ፡፡ ለጥንቃቄ የሚሆናችሁን ብቻ እነግራችኋለሁ፡፡ The devil is in the detail እንዲል ፈረንጅ ዝርዝሩ የሚያስከትለው ውጤት በጣም አደገኛ ነውና እለፉት፡፡
ነገርየው ዱቄት ነው፡፡ የሚገኘው ከአንድ ተክል ነው፡፡ ይህ ተክል በሃገራችን በበርካታ አካባቢዎች ፣ በከተማችንም ብዙ ቦታ በተለይ ወንዝ ዳር አካባቢ በቅሎ ይገኛል፡፡ በልጅነታችን እቃቃ ስንጫወትበት ስላደግን ፣ እናቶቻችንም ለአንዳንድ የቆዳ ችግሮች እንደመድሃኒት ስለሚጠቀሙበት እኔ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ አሁንም ብዙ ሰፈሮች ውስጥ አየዋለሁ፡፡
ሳይንስ “የምድራችን እጅግ አስፈሪው ተክል” ብሎ ይጠራዋል፡፡ በብዙ ሃገራት “የዲያቢሎስ ትንፋሽ” የሚል ስም ተሰጥቶታል፡፡ እግዚአብሄር ጠብቆን እንጂ በልጅነታችን ፍሬውንና አበባውን እየተጫወትንበት አድገን ምንም ሳንሆን መትረፋችን ተዐምር ነው፡፡ (ስሙ ይቅር)
ከዚህ ተክል የሚመረትና በዱቄት መልክ የሚዘጋጅ ‘xxxx’ የሚባል ንጥረነገር አለ፡፡ ይህ xxxx ንጥረነገር በጣም በጥቂት ግራም ጆሮ ግንድ አካባቢ ቆዳ ላይ እንዲቀባ ተደርጎ ይዘጋጅና በትራንስፖርት ሲጓዙ ለሚያጥወለውላቸውና ለሚያስመልሳቸው ሰዎች በየፋርማሲው ይሸጣል፡፡ ከፍ ላለ ህመም ማስታገሻነት ደግሞ በሚቀባ እና በሚዋጥ መልኩም ይዘጋጃል፡፡ ከቀዶ ጥገና በኋላ የሚከሰት ማቅለሽለሽና ማስታወክን ለማስወገድም ይሰጣል፡፡ አደገኛ ማደንዘም ይሰራበታል፡፡ በሌላ በኩልም በማይድን በሽታ ተይዘው መሞት ለሚፈልጉ ሰዎች እንደየሃገሩ ህግ በሃኪም ለሚታገዝ የሞት ውሳኔ ማስፈጸሚያ መጠኑ ከፍ ተደርጎ ይዘጋጅና ይሰጣል፡፡ (አወሳሰዱ አሁንም ይቆየን)
በአጠቃላይ ይህ ዱቄት በቆዳ በመስረግ፣ በትንፋሽ በመሳብ እና በመጠጥና በምግብ ውስጥ በመግባት የሰውን ልጅ የማሰብ፣ የማሰላሰል እና የማመዛዘን አቅም ያሳጣል፡፡ዋናው አላማ ማደንዘዝና ምንም ነገር እንዳይሰማን ማድረግ ነው፡፡
የሃገራቱ ስም ይቅርና በአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ እና የአውሮፓ ሃገራት በፋርማሲ ውስጥ ያለሃኪም ትዕዛዝ ይሸጣል፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ይገኛል ማለት ነው፡፡ እስካሁን ብዙዎች ቢወተውቱም በዓለምአቀፍ ደረጃ ቁጥጥር ከማይደረግባቸው ድራጎች ተርታ እስካሁን አልወጣም፡፡ አሁን ዋናው ነገር “ይህንን ዱቄት ወንጀለኞች እንዴት ይጠቀሙበታል?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እሱን እንየው፡፡
ይህንን ንጥረነገር በመጠቀም በተለያዩ ሃገራት ወንጀል ይፈጸማል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ልክ እንደኛ ሃገር ሁሉ አሜሪካ ጭምር እንዲህ ያለ ወንጀል ተፈጽሞ ተበዳይ አቤቱታ ሲያቀርብ ፖሊሶች “የከተማ ተረት ተረት ” ብለው ይቀልዱበት ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ልክ እንደኔ እናትና እህት ተበዳዮች ወይ ሰው አያምናቸው፣ ወይ ንብረታቸው አይመለስላቸው ወይ ወንጀለኛው አይያዝላቸው ከሁሉ ያጡ ሆነው ስለሚቀሩ ፖሊስ ጋር መሄድም ለሰው ማውራትም ያቆማሉ፡፡
ሌላው ጥልቅ መረጃ ይቅርብንና እናንተ ብቻ ከዚህ በታች ከምዘረዝራቸው ሰዎች ራሳችሁን ጠብቁ!!
(1ኛ) በሆነ አጋጣሚ ካገኛችሁትና ያለምንም ምክንያት ከቀረባችሁ ዘናጭ ‘ጀንትል ማን’ ነኝ ባይ ሰው ቢዝነስ ካርድ አትቀበሉ፡፡ ይህንን አንብቡልኝ ብለው ብጣሽ ወረቀት ከሚሰጧችሁ አዛውንት መሳይ ወይም የገጠር ሰው መሳይ ሰዎች ወረቀቱን አትቀበሉ፡፡ “ሎተሪ ደርሶኛል እዩልኝ” ብለው ሎተሪውን ከሚያቀርቡላችሁ ሰዎችም እንዲሁ ሎተሪውን እንዳትቀበሉ፡፡ ምክንያቱም ይህ ዱቄት የተነሰነሰበት ማንኛውንም ወረቀት በእጃችሁ በነካችሁ በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ በትንሹ ለ4 ሰዓት በሚቆይ ‘መነሁለል’ ውስጥ ትገባላችሁ፡፡ ነጻ ፍቃዳችሁን መቆጣጠር አትችሉም፡፡ የሚጠይቋችሁን ቀርቶ ያልተጠየቃችሁትን ሁሉ ታደርጋላችሁ፡፡ የወሰዷችሁ ቦታ ሁሉ ትሄዳላችሁ፡፡ በዚህ የተነሳ በእጅ ላለ ንብረት መወሰድ ወይም ቤት ድረስ በመሄድ ለከባድና ውድ ንብረቶች መዘረፍ፣ ለባንክ አካውንት መመዝበር፣ ሲከፋም ለመደፈርና ለአካል ብልቶች ዘረፋ ወንጀሎች ትጋለጣላችሁ፡፡ (እኛ ሃገር እስካሁን የተመዘገበው ሞባይል፣ወርቅና የባንክ ገንዘብ ስርቆት ነው )
(2ኛ) ከጸጉራችሁ ላይ ቆሻሻ ነገር ለማንሳት በሚል ሰበብ መሃረብ ወይም ሌላ ነገር ይዘው እጃቸውን ወደፊታችሁ ከሚያቀርቡ ሰዎች ፣ ወይም ፎቶግራፍ ወይም ስዕል መሳይ ነገር በእጃቸው ይዘው ወደፊታችሁ በማስጠጋት ከሚያሳዩዋችሁ ሰዎች ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ምክንያቱም የያዙት ነገር ላይ ያለውን ዱቄት በትንፋሻቸው ፊታችሁ ላይ ‘እፍፍ’ ሲሉት እናንተ ወደውስጥ ትስቡትና በቅጽበት ከላይ በተገለጸው መልክ ፈዝዛችሁና ደንግዛችሁ ራሳችሁን ትስታላችሁ፡፡ ያኔ የፈለጉትን ነገር እሺ ብላችሁ መፈጸም፣ አለያም ወደፈለጉት ቦታ መነዳት እጣችሁ ይሆናል፡፡
(3ኛ) በየትኛውም መመገቢያ ስፍራ እና መጠጥ ቤት የምትጠጡትን በብርጭቆም ይሁን በጠርሙስ ያለ መጠጥ ክፍት ጥላችሁ አትሂዱ፡፡ የተከፈተ መጠጥ ከሚያቀርብላችሁ ወየም ከሚጋብዛችሁ እንግዳ ሰው ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ይህ ዱቄት የተነሰነሰበት ፈሳሽ መጠጣት በተለይ ዶዙ ከፍ ያለ ከሆነ እስከሞት ሊያደርሳችሁ ይችላል፡፡ አለያም ለረጅም ሰዓት(እስከ24 ሰዓት) አፍዝዞ ስለሚያስተኛ እናንተ የምትነቁት ሁሉ ነገር ካለቀና ከደቀቀ በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተለይ አዘውትራችሁ ናይት ክለብ የምትወጡ ሰዎች በጣም ተጠንቀቁ፡፡ ብቻችሁን መኪና ከያዛችሁ የሚከተላችሁ ይኖራል፡፡ በአነድ መኪና ሆናችሁ ብትወጡ ይመረጣልሸ፡ ምክንያቱም የመኪናችሁ በር እጀታ በዚህ ዱቄት ከተነካ በሩን ስትከፍቱ ንጥረነገሩ በቆዳችሁ ይገባና ወዲያው ወንጀለኞቹ ከናንተ ጋር ተሳፍረው እናንተ እየነዳችሁ የትም ይዘዋችሁ ሊሄዱ ወይም ወደራሳችሁ ቤት ወይም ሱቅ ራሳችሁ እየነዳችሁ ወስዳችኋቸው የፈለጉትን ዘርፈው ለመሰወር ያስችላቸዋል፡፡
እዚህ ሃገር ብዙ ጊዜ ወንጀሉ የሚፈጸመው አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ መሆኑን ከአቤቱታዎች ተገንዝቤያለሁ፡፡ እህቴ ቦሌ መድሃኔአለም ተሳልማ ስትመለስ ነጠላ እንደለበሰች ነው ሁሉ ነገሯን አጥታ ራሷን መስቀል ፍላወር ያገኘቸው፡፡ እናቴም ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ስትመለስ ነበር በታክሲ ወስደው የዘረፏት፡፡ ቅድም አንዲት ወጣት ቲክቶክ ላይ ከኪዳነምህረት ስመለስ ሚሊኒየም አካባቢ አግኝተውኝ 28ሺህ በር ከባንክ አስወጥተው ዘረፉኝ ስትል ሰምቻታለሁ፡፡ ብዙ ጉዳት ደረሰብን የሚሉ ሰዎች ከመንፈሳዊ ሰፍራ ሲመለሱ በነዚህ ሰይጣኖች እየተጠመዱ ነው መሰለኝ ፡፡
ቀናችንን ለእግዚአብሄር ሰጥተን መውጣት ዋናው ነገር ነው፡፡ ያም ሆኖ የራስን ጥንቃቄ ማድረግ ደግሞ አምላክን “ምን በደልኩህ” ብሎ ከመሟገት ያድነናል፡፡ እናንተም ማንነታቸውን ስለማታስታውሷቸው፣ ፖሊስም ዳናውን ማግኘት ስለሚቸግረው ወንጀል ፈጻሚዎችን መያዝ አስቸጋሪ ነው፡፡ “ጥንቃቄ ይጠብቃል፣ ማስተዋልም ይጋርዳል” እንዲል ቅዱስ መጽሃፉ! በነገር ሁሉ እየተጠነቀቅን ፣ በጉዟችንም እያስተዋልን ይሁን ፡፡
ቸር ዋሉ!!
ማሳሰቢያ! …ስለዚህ ዱቄት አውቃለሁ የሚል ማንም ሰው እዚህ ፖስት ስር የንጥረነገሩን ስምና ተያያዠ መረጃዎች ቢጽፍ ወንጀል እያስተማረ መሆኑን ፣ ለዚህም ተጠያቂ እንደሚሆን አስቀድሞ ይወቀው፡፡
መላኩ ብርሃኑ