ከክውፍተኛ የትግራይ ኃይሎች አመራሮች በተጨማሪ የትግራይ ክልል ምስራቃዊ ፣ ደቡብ ምስራቃዊ ፣ የደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ እንዲሁም በራስ ተነሳሽነት መሰባሰባቸውን የገለፁ የመቐለ ከተማ ወጣቶች መግለጫ አውጥተዋል። ” ወታደራዊ መኮንኖች ከተልእኮ እና ከተሰጣቸው ህዝባዊ እና መንግስታዊ ስምሪት ባፈነገጠ መልኩ ወደ አንዱ ቡድን በማዳላት ያወጡት መግለጫ በአስቸኳይ እንዲያርሙት ” ሲሉ ጠይቀዋል። ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸው ደጋፊዎች ስላላቸው ሌላ ግጭት እንዳይነሳ ስጋቱ አይሏል።
አገር ሊያጠፋ የሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት በማንኛውም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሰው የትግራይ ኃይል አመራሮች ያወጡትን አንድ ወገን የደገፈ መግለጫ ሌሎች የትግራይ ኃይል አመራሮች አወገዙት። በትግራይ ሃይል አመራሮች ዘንዳ የተነሳው አለመግባባት አደጋ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል እየተገለጸ ነው።
ያካሄደው ጉባኤ በብሄራዊ የምርጫ ቦርድና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተካተቱ የድርጅቱ አባላት እውቅና ያልተሰጠውና በዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ትህነግ እውቅና እንደሚሰጡ ያስታወቁት የትግራይ ኃይል አመራሮችን በተቃራኒው ጊዚያዊ አስተዳደሩ በፅኑ ተቃውመውት ነበር መግለጫ ያወጡት።
ትናት የወጣውን መግለጫ ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ የትግራይ ሐይሎች ከፍተኛ አዛዦች “ከተልእኳቸው ውጭ ለአንድ ሕገወጥ ቡድን ወግነው ግዚያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ስርዓት አልባኝነት የማንገስ እና ሰራዊት የመበተን ግልፅ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል” ሲል ለትግራይ ህዝብና ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ አስታውቆ ነበር።
“ሕጋዊ ይሁን ሞራላዊ ቅቡልነት የሌለው ነው” ሲል የከፍተኛ አዛዦቹን ወገን የለየ አቋምና ውሳኔ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተቃወመ ማግስት ከከፍተኛ አዛዦቹ መካከል የተለየ አቋም የሚያራምዱ አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
” እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ውጤቱ ህዝብን እና አገር የሚያጠፋ አካሄድ በመሆኑ መቆም አለበት ” -ሲሉ የተለየ አቋም ያላቸው ከፍተኛ የትግራይ ኃይል አመራሮች አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ የበላይ የትግራይ ኃይል አመራር መኮንኖች ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ያወጡት መግለጫ ተቃውሞ እንደገጠመው የተገለጸውም ይህ ከሆነ በሁዋላ ነው።
የእነ ዶክተር ደብረጽዮንን ትህነግ ደግፈው አቶ ጌታቸው የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር ያወገዙት የትግራይ ኃይል አዛዦች መግለጫቸውን ባሰራጩበት ወቅት አቋሙ በሙሉ ድምጽ የተወሰነ መሆኑን አመልክተዋም ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ይፋ እንደሆነው ሌሎች የትግራይ ኃይል አዛዦች አካሄዱን መቃዋማቸው ይፋ ሆኗል።
የጊዚያዊ አስተዳደሩን መግለጫ ተከትሎ በአመራሮቹ ሰብሰባ ላይ የተሳተፉ የተለየ አቋም እንዳላቸው የገለጹ ከፍተኛ የትግራይ ኃይል አመራሮች ፥ ” የሰራዊት አመራር በመሆን የፓለቲካ ፓርቲ የሚመስል ሰራዊት ለመገንባት የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤቱ ህዝብን እና አገር የሚያጠፋ አካሄድ እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን ” ሲሉ በአደባባይ አስታውቀዋል።
የተለየ አቋም እንዳላቸው በመግለጫቸው ያሳወቁት ከፍተኛ አመራሮቹ ፤ ” አንድ የፓለቲካ ፓርቲ እና በዚህም በዚያም ያሉት ቡድኖችን የሚመለከት አጀንዳ ላይ መወያየት እና አቋም መያዝ ከሰራዊቱ ተልእኮ ውጪና ወታደራዊ ወንጀል በመሆኑ በጥብቅ እንቃወማለን ” ሲሉ አብራርተዋል።
” ስለሆነም ከሰራዊቱ ተልእኮ እና የስራ ስምሪት ውጪ ‘ ጠላት ነው ‘ በሚል ፍረጃ የጊዚያዊ አስተዳደሩን ፕሬዜዳንት ለመቀየር የሚደረግ የፓለቲካ እንቅስቃሴ ተቋማዊ አሰራር የሚጥስ በመሆኑ እንዲቆም በጥብቅ እንጠይቃለን ” ሲሉ አክለዋል።
የክልሉ ምስራቃዊ ፣ ደቡብ ምስራቃዊ ፣ የደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ እንዲሁም በራስ ተነሳሽነት መሰባሰባቸውን የገለፁ የመቐለ ከተማ ወጣቶች ባወጡት መግለጫ ፤ ” ወታደራዊ መኮንኖች ከተልእኮ እና ከተሰጣቸው ህዝባዊ እና መንግስታዊ ስምሪት ባፈነገጠ መልኩ ወደ አንዱ ቡድን በማዳላት ያወጡት መግለጫ በአስቸኳይ እንዲያርሙት ” ሲሉ ጠይቀዋል።
” አመራሮቹ ያወጡት ህገ-ወጥ መግለጫ ጅምር ሰላሙ የሚያጨልምና የሚያመክን በመሆኑ ፤ ለህግ እና ስርዓት ተገዢ ከሆኑ አመራር እና አባላት ጋር በመሆን እስከ መጨረሻ ብፅናት እንደምንታገላችሁ ልናሳውቃችሁ እንፈልጋለን ” ሲሉ የተቃወሙ መኮንኖች አስታውቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ የትላንቱን መግለጫ በመቃወም ለቪኦኤ በሰጡት አጭር ቃል ፥ ” የትግራይ ሰራዊት የቡድኖች መጫወቻ እንዲሆን የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ስህተት ነው ፤ ወታደራዊ መኮንኖቹ ፓለቲከኛ መሆን ካሰኛቸው ወታደራዊ ሃላፊነታቸው በመተው የፈለጉት ፓርቲ አባል መሆን ይችላሉ። ከዚህ ውጭ ያደረጉት ስህተት ግን በአስቸኳይ እንደሚያርሙት ተስፋ አደርጋለሁ ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ የወታደራዊ ኃይል አመራሮች የደብረጽዮን ትህነግ በወሰነው መሠረት ‘የተዳከመ’ ያሉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በሌላ እንዲዋቀር መወሰናቸውን አይዘነጋም።