በግድያው ከተጠረጠሩትና በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሶስት ተጠርጣሪዎች መካከል አንደኛው የቀድም የባለሃብቱ የጥበቃ ሰራተኛ ነው። ግድያውም የተፈጸመው ተቀነባብሮና ዝግጅት ተደርጎበት ሲሆን፣ የተያዙት ራሳቸውንና ማንነታቸውን ቀይረው በደቡብ ክልል ነው። ፖሊስ በምስል፣ በስምና በአድራሻ ይፋ ያደረገው ዜና ግድያውን የፖለቲካ አጀንዳ ላደረጉት ክፍሎች የሚያስደስት አይሆንም

በድንገት ደጃቸው በር ላይ የተገደሉትን የአክሰስ ኮም ኩባንያ ባለቤት እና የሸበል በረንታ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ቢረሳው ህይወታቸው ካለፈ ቅጽበት ጀመሮ በተደረገ የተቀናጀ ክትትል ባለሃብቱን ገድለዋል የተባሉ ሁለት ተጠረጣሪዎች መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ በስም የሚታወቁ ሚዲያዎች ግድያውን ለተቋቋሙበት ዓላማ አውለውት እንደነበር አይዘነጋም።
አቶ ቢረሳው ምናለ ታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም 1ሰዓት ከ30 ላይ ቤታቸው በር ላይ በጥይት ተመትተው እንደተገደሉ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው መሰረት ሚዲያ፣ ግድያው ሲፈጸም፣ ባለሀብቱ በሚኖሩበት ለሚ ኩራ፣ ወረዳ ዘጠኝ አትሌቶች መንደር ምንም ዓይነት የጥበቃ ኃይል እንዳልነበረና ሟች የብቸና ሰው መሆናቸውንም አመላክቶ ነበር።
ይህንኑ ዜና ተከትሎ ሟች የጎጃም ሰው በመሆናቸው የተጠቁ ተደርጎ ዜናው የፖለቲካ መገበያያ መሆኑም አይዘነጋም። በርካታ አስተያየት እየታከለበት ” አትነሳም ወይ” በሚል ቅስቀሳ የማህበራዊ ሚዲያ መቀሰቀሻ ግብዓት ሆኖ ነበር።
ፖሊስ እንዳለው አቶ ቢረሳው ምናለ ፈንታ ታሕሳስ 21 ቀን 2017 ዓም በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው እንዳለፈ ገዳዮችን ማደን ጀምሯል።
ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ በወንጀሉ ስፍራ ፈጥኖ በመድረስ የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት ለማወቅና በቁጥጥር ስር ለማዋል ቀን ከሌት ያልተቋረጠ እና እልህ አስጨራሽ ክትትል ሲያደርግ ማድረጉን ገልጾ መረጃ ቢሰጥም፣ የባለሃብቱን ግድያ ያሰራጩት ክፍሎች ግን ፖሊስን ጠቅሰው ይህ እስከተጻፈ ድረስ ምንም አላሉም።ከወንጀሉ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ምንነት ለመለየትም ከአዲስ አበባ ሐዋሳ እስከ ሞያሌ ጫፍ የደረሰ መረጃና ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባር መከናወኑን ፖሊስ ዘርዝሯል።
በፖሊሳዊ ጥበብ እና ስልት በተሰራው በዚህ ስራ ወንጀሉን በመፈፀም የተጠረጠረውን መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለውን ግለሰብ እና አብዩ አይተነው ፈንታ ጨምሮ ለወንጀሉ መፈፀም አካባቢውን በመቆጣጠር ተሳትፎ የነበረውን አቶ ወርቁ መለሰ ካሴ የተባሉትን ሦስቱንም ተጠርጣሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጌዴዎን ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ ላይ በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሪፖርት ያስረዳል።
ተጠርጣሪዎቹ ከወንጀሉ መፈፀም በፊት በተቀነባባረ ሴራ በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ግለሰብ በህገ-ወጥ መንገድ በታጠቀው ማካሮቭ ሽጉጥ የአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ የግል ጠባቂ ሆኖ ሲያገለግል እንደቆየ ተጠቁሟል።
ሁለቱ ግለሰቦች ከአቶ አብዩ አይተነው ፈንታ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት አንዱ የአካባቢውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ለወንጀል ፈፃሚው ሁኔታውን ሲያመቻች መኮንን ይዋል ይፍሩ የተባለው ደግሞ የግድያ ወንጀሉን መፈፀሙን ለፖሊስና ለፍርድ ቤት ከሰጡት የእምነት ቃል የተረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር በወንጀሉ ስፍራ የመርማሪዎችንና አቃቤ ህግ ቡድን እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት የወንጀሉን አፈፃፀም መልሶ ማቋቋም (Re-construct) በተግባር አሳይተዋል፡፡
በዕለቱም የወንጀሉ ፍሬ የሆነው ንብረትነቱ የአቶ አብዪ አይተነው ፈንታ የውግ ቁጥር የሌለው ማካሮቭ ሽጉጥ እና ለማምለጥ የሞከሩበት እንዲሁም ሽጉጡን የደበቁበት ላንድክሩዘር ተሽከርካሪ በኤግዚቢትነት ተይዟል ፡፡ ምንም እንኳን ተጠርጣሪዎቹ ማንነታቸውን በመቀየር ከወንጀሉ ተጠያቂነት ለማምለጥ በሐሰተኛ ስም ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ ለመጥፋት ቢያስቡም በተሰራው እረፍት አልባ ፖሊሳዊ ጥበብ በታከለበት የክትትልና የምርመራ ስራ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቅንጅት ሰርተዋል፡፡ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ የክትትል ስራ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ እና ትብብር ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋል ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ እንደማይቻል የሚያረጋግጥ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የህብረተሰቡን አቅም በመጠቀም ውጤት መገኘቱን አመላክቷል፡፡ በቀጣይም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረጉ የፍትህ ሂደቶች ውሳኔውን ተከታትሎ ለህዝብ እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
