(ኢትዮሪቪው)ሚካኤል ሽመልስ ጌታሁን የተባለ ተከሳሽ የእንጀራ ልጁ የሆነችውን ሟች አዶናዊት ይሄይስ ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ በወላጅ እናትዋ ፊት በመግደሉ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡
ተከሳሹ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው 15 ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ ለማንም እንዳትናገሪ፣ ከተናገርሽ እናትሽና አባትሽን እገላለሁ፣ እንዲሁም የግብረ ስጋ ግንኙነት ስንፈፅም በሞባይል ቪድዮ ቀርጨዋለሁ፣ በሚድያና በቴሌግራም እለቀዋለሁ በማለት ድርጊቱን እንዳትቃወም የስነ ልቦና ጫና በማሳደር ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወትዋ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል እየደጋጋመ ሲፈጽም እንደነበር ታውቋል፡፡
ሟች አዶናዊት ይሄይስ ከተከሳሽ ሁለት ጊዜ ስታረግዝም መጀመሪያ የነበረው እርግዝና ቤተሰብ እንዳያውቅበት የሟች ስም ኤፍራታ አለማየሁ በሚልና የሟች ዕድሜም 19 ዓመት እንደሆነ በማስመሰል ሐሰተኛ ስም እና ዕድሜ በማስመዝገብ ያረገዘችውን ፅንስ እንድታስወርድ በማስገደድ እርግዝናውን እንድታስወርድ ማድረጉ ተነግሯል፡፡
መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሳሽ በሟች ላይ በፈፀመው የግብረስጋ በደል ወንጀል ምክንያት ፖሊሶች ሊያዙት ወደ ቤቱ መምጣታቸውን ሲያይ በመስኮት ወጥቶ ከፖሊስ እጅ አምልጦ ከሄደ በኋላ ሊይዙት የመጡትን ፖሊሶች መሄዳቸውን ሲያረጋግጥ ተመልሶ ወደ ሟች ቤት በመምጣት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ወላጅ እናትዋ ፊት በቢላ ደጋግሞ በመውጋት ሟች ሕይወትዋ እንዲያልፍ ማድረጉም ተነግሯል፡፡
ሟች ሕይወትዋ ሲያልፍም ለሁለተኛ ጊዜ ከተከሳሽ እርጉዝ የነበረች በመሆኑ ምክንያት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ከተጣራበት በኋላ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዓቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት 1ኛ/ ክስ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ህግ አንቀጽ 539(1)(ሀ) እንዲሁም 2ኛ/ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 627/1/እና 628/ሀ/ መሰረት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሰው ግድያና ውንብድና ችሎት ክስ አቅርቦ ቆይቷል፡፡
ጉዳዩን ሲያይ የነበረው ችሎትም የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ ከሰማ በኋላ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃውን አቅርቦ ካሰማ በኋላ ተከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ማስረጃ ሊከላከል ባለመቻሉ የጥፋተኛነት ፍርድ ተሰጥቶበታል፡፡
ተከሳሽ የጥፋተኛነት ፍርድ ከተሰጠው በኋላም ለቅጣት ማቅለያነት በሚል በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ የጀዌ ቦኒ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የተለያዩ 8 የምስጋና ወረቀቶች እንዲሁም ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ወረዳ አዲስ ሰላም እገጣ ማርያም ቤተክርስቲያን አንድ የምስጋና ምስክር ወረቀት አቅርቦ ነበረ፡፡
ነገር ግን ተከሳሽ ያቀረባቸው የምስጋና ምስክር ወረቀቶች ሐሰተኛ ለመሆናቸው በዓቃቤ ሕግ በኩል በማጣራትና ይህንኑ ለችሎቱ በማስረዳት ለቅጣት ማቅለያነት በሚል ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ውድቅ እንዲሆኑ በመደረጋቸው፣ ተከሳሽ በታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን ችሎቱን የተከታተለው የጋዜጣ ፕላስ ዘገባ ያስረዳል።