የስምንት ዓመቷን የስኳር ህመምተኛ ታዳጊ ለአንድ ሳምንት ያህል የሚያስፈልጋትን ኢንሱሊን የተባለውን መድኃኒት በመከልከል ህይወቷ እንዲያልፍ ምክንያት ሆነዋል የተባሉ 14 የአውስትራሊያ የሃይማኖት ቡድን አባላት ጥፋተኛ ተባሉ።
ኤልዛቤት ስትሩዝ በአውሮፓውያኑ 2022 በስኳር ህመም ተሰቃይታ በደሟ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ በማለቱ ምክንያት ሕይወቷ እንዲያልፍ ሆኗል።
ኤልዛቤት መድኃኒቱን የተከለከለችው የህክምና አገልግሎትን በሚቃወም ‘ቅዱሳን’ በመባል የሚታወቀው የዕምነት ቡድን ፈጣሪ ይፈውሳታል ተብሎ በመታመኑ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።
አባቷ ጄሰን ስትሩስ እና የቡድኑ መሪ ብሬንዳን ስቲቨንስ በነፍስ ግድያ ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበው የነበር ቢሆንም ጉዳያቸው ባልታቀደ የግድያ ወንጀል እንዲታይ ተደርጓል።
የኤልዛቤት እናት እና ወንድምን ጨምሮ ሌሎች 12 የዕምነት ቡድኑ አባላትም ባልታቀደ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል። ሁሉም ግን ትፋተኝነቱን አስተባብለዋል።
ዳኛው ማርቲን በርንስ ረቡዕ ዕለት ወደ 500 ገጽ የሚጠጋው የውሳኔ ሐሳብ በያዘ የያዘ በሰጡበት ወቅት ምንም እንኳን የኤልዛቤት ወላጆች እና “ሌሎች ተከሳሾችን ጨምሮ ሁሉም የቤተክርስቲያኑ አባላት” እንደሚያከብሯት ግልጽ ቢሆንም፣ ድርጊታቸው ለእሷ ሞት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
“ኤልዛቤት በሁሉም መንገድ በፍቅር እንክብካቤ ይደረግላት እንደነበር ጥርጣሬ ሊኖር አይገባም” ብለዋል።
“ነገር ግን በፈጣሪ የፈውስ ኃይል ላይ ባለ እምነት ምክንያት… በእርግጠኝነት ሕይወቷን የሚያቆየውን ነገር [መድኃኒት] ተነፍጋለች።”
‘ቅዱሳኑ’ የተባለው የዕምነት ቡድን በአውስትራሊያ ውስጥ ከተቋቋመ ከየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሲሆን፣ ከሦስት ቤተሰቦች የተውጣጡ ከሰላሳ በታች የሆኑ አባላት ብቻ አሉት።
ይህ የነፍስ ማጥፋት ክስ ጉዳይ በኩዊንስላንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት የጀመረው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ሲሆን፣ ለበርካታ ወራትም ዘልቋል።
ዐቃቤ ሕግ 60 ምስክሮችን በማሰማት በመጨረሻዎቹ ቀናት ከፍተኛ ስቃይ የደረሰባትን “አስተዋይ” ያላትን ሕጻንን ሁኔታ በማቅረብ ክሱን አጠናክሯል።
ዐቃቤ ሕግ ካሮላይን ማርኮ ሟቿ ታዳጊ “ብዙም የማትናገር፤ ወደ መጸዳጃ ቤት እንድትሄድ እርዳታ የሚያስፈልጋት እና ራሷን የማትችል መሆኗ ተገልጿል” ከማለት ባለፈ ከፍተኛ ድካም እና ራስን መሳት እንዳጋጠማት ተናግረዋል።
የዕምነት ቡድኑ ምዕመናንም ከብሪዝበን በስተ ምዕራብ 125 ኪሜ ርቀት ላይ ቱዉምባ በሚገኘው ቤቷ ፍራሽ ላይ ለተኛችው የኤልዛቤት ጤንነት ሲጸልዩ እና ሲዘምሩ ነበር።

የታዳጊዋን ሕይወት ለመታደግ ሐኪም ለመጥራት ስልክ ለመደወል ምንም ዓይነት ጥረት አልተደረገም። ሕይወቷ ካለፈ አስከ 36 ሰዓታት ድረስ ባለስልጣናት እንዲያውቁት አልተደረገም። ምክንያት የተባለው ደግሞ ትድናለች በሚል ቡድኑ ስላመነ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተነግሯል።
ዕድሜያቸው ከ22 እስከ 67 ዓመት የሆኑ 14 ተከሳሾች ችሎት ፊት ቀርበዋል ነበር። ሁሉም ጠበቃ እንዲቆምላቸውም ሆነ ቃል ለመስጠት እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።
አብዛኞቹ የተከሰሱት ኤልዛቤት ኢንሱሊን እንዳትወስድ አባቷን በመምከራቸው ወይም በመረዳታቸው ነው ተብሏል።
የ53 ዓመቱ ጄሰን ስትሩስ ከ49 ዓመቷ ባለቤቱ ኬሪ ስትሩስ ዘግይቶ እምነቱን መቀየሩን እና ከዚህ ቀደም ኤልዛቤት መድኃኒት እንድታገኝ ድጋፍ ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።
ከተጠመቀ በኋላ ሃሳቡን እንደቀየረ እና በመጨረሻም ውሳኔው የሴት ልጁን ሕይወት እንደሚያጠፋ ያውቅ ነበር ተብሏል።
ፍርድ ቤት ተራው ደርሶ በእንባ እየታጠበ የተናገረው ጄሰን ስትሩዝ፤ እሱ እና ኤልዛቤት “ኢንሱሊንን ለማቆም” አንድ ላይ ተስማምተው እንደነበር እና አሁንም ሴት ልጃቸው ከሞት እንደምትነሳ እንደሚያምን ተናግሯል።
“ኤልሳቤት ተኝታለች። እናም እንደገና አገኛታለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
የ63 ዓመቱ ስቲቨንስ የቡድኑን ድርጊት እምነትን መሠረት ያደረገ ነው በማለት ችሎቱን “ሃይማኖታዊ ችሎት” ሲል ገልጿል።
ቡድኑ “በእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ የማመን መብቱ አለው” በማለትም ክሱን ላለመቀበል የወሰኑት ሕግን በመጠቀም ጉዳዩን “የመከላከል ዓላማ ስለሌለው ነው” ብለዋል።
የኤልዛቤት እህት ጄይድ ስትሩዝ በበኩሏ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኗን አስውቃ ቅዱሳኑን ትታ በ16 ዓመቷ ከቤተሰቧ ቤት እንደሸሸች ተናግራለች።
እሷ እና ሌሎች ምስክሮች እንደገለጹት ከሆነ ጉባኤው ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥብቅ አመለካከቶች እንደያዘ ገልጸዋል።
ዋነኛ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች መወገድ እንዳለባቸው እና የገና እና የፋሲካ በዓል “የዕምነት የለሽ” እግዚአብሔርን ያልተቀበሉ ሰዎች በዓላት ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 የኤልዛቤት ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ ፍርድ ቤቱ ሰምቷል። በወቅቱ በስኳሩ ህመም ምክንያት እረሷን ስታ (ኮማ ውስጥ ገብታ) የነበረ ሲሆን፣ 15 ኪሎ ከመመዘኗም በላይ በእግር ለመራመድ ተቸግራ ነበር።
የስኳር በሽታ እንዳለባት እና በየቀኑ የኢንሱሊን መርፌ እንደሚያስፈልጋት ለቤተሰቦቿ ተነግሯቸዋል።
ሁለቱም ወላጆች በዚያ ክስተት ተከሰው የነበር ሲሆን፣ ጄሰን ስትሩስ በሚስቱ ላይ በመመስከሩ አነስተኛ ቅጣት ተላልፎበታል።
ለዓመታት የቅዱሳን አባል የነበረችው ሚስቱ ልጆቻቸውን በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ህክምና መውሰድ የለባቸውም ብላ ታምንም ነበር ብሏል። አባት ሴት ልጁ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሕይወቷ እንዲያልፍ በመተዉ መጸጸቱንም በግልጽ ተናግሯል።
ሚስቱ በእስር ላይ እያለች ለተወሰነ ጊዜ ኢንሱሊን እንዲሰጣት እንደረዳትም ፍርድ ቤቱ ሰምቷል። ይህን ማድረጉን እንዲያቆም ከሌሎች የሃይማኖት ቡድኑ አባላት ግፊት ገጥሞታል።
ዳኛ በርንስ ውሳኔውን ሲሰጡ ጄሰን ስትሩህስ እና ስቲቨንስ በታቀደ የነፍስ ግድያ ሊከሰሱ ያልቻሉበት ምክንያት ዐቃቢያነ ሕጎች ጥንዶቹ ኤልዛቤት ላይ ግድያ ለመፈጸም ወይም ከባድ የአካል ጉዳት ለማድረስ እንዳሰቡ ማረጋገጥ ባለመቻላቸው ነው።
በጋራ በመሆን ለሞቷ ምክንያት የሆነ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል 14ቱም ተከሳሾች ባልታቀደ የሰው ነፍስ የማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲሉ ዳኛው ብይን ሰጥተዋል።
ጄይድ ስትሩስ በፍርዱ ደስተኛ መሆኗን ብትገልጽም የአውስትራሊያ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት ማድረግ የሚገባውን ባለማድረጉ ምክንያት “እህቷን ማጣቷን” ገልጻለች።
እህቷ ከፍርድ ቤት ውጪ በሰጠችው መግለጫም “እሷን ለመጠበቅ ወይም በራሷ ቤት ውስጥ ከነበረው ሁኔታ ለመጠበቅ ቀደም ተብሎ አልተሠራም” ስትል ወቅሳለች።
ቡድኑ በሚቀጥለው ወር የቅጣት ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ይጠበቃል።
አዳዲስ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠኑት በርናርድ ዶኸርቲ እንዳሉት ከሆነ ቱዉምባ ለረጅም ጊዜ “ያሸበረቁ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እና ራሳቸውን የቻሉ አብያተ ክርስቲያናት ነበሯት” ብለዋል።
“ቅዱሳኑም በጥቂት ቤተሰቦች ዙሪያ ከተመሠረቱ ከእነዚህ ትናንሽ ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ሆኖ ይታያል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው፤ ሆኖም ግን ስለቅዱሳኑ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም” ብለዋል።
ቅዱሳን በብሪዝበን በሚገኘው የሪቫይቫል ሴንተርስ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ተሳትፈው እንደነበር ጄይድ ስትሩስ ተናግራለች። ስቲቨንስ ፓስተር መሆን ባለመቻሉ ተለያይተዋል ብላለች። ከዚያ በኋላ የራሳቸውን ደብር መሥርተው በሳምንት ብዙ ጊዜ በእሱ ቤት ጸሎት ያደርጉ ነበር ስትል ተናግራለች።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk