አዲስ አበባን ከዓመታት በሁውላ የሚመለከቱ ያለምንም ማጋነን ቀድሞ የሚረዱት መታደሷን፣ እየታደሰች መሆኑን፣ ገና እድሳቷ እንደሚቀጥል፣ ተወደደም ተጠላም ጅምሩ ሌላ አማራጭ የሌለው እንደሆነ ነው፡፡ ወደ ውስጧ ዘልቀው ወሬ መቃረም ሲጀመሩ፣ መቀማመስና መጎራረስ ሲጀመሩ ደግሞ መለክያው በውል ሊታወቅ በማይችል ስካር ውስጥ መሆኗን ይረዳሉ፡፡
የናጠጡ፣ ለመናጠጥ የተቃረቡ፣ ህግ የሚያከብሩ፣ ህግ የሚደረማምሱ፣ ከልካይ የሌላቸው፣ የሚከለከሉ፣ ዋጋ የሚሰቅሉ፣ ህዝብን ያለ አንዳች ምክንያት የሚገፉ፣ ስግብግቦጭ ለጋሶች፣ የሚያማርሩ፣ የተማረሩ፣ ሚዛን የሳቱ፣ ሚዛን የተደፋባቸው ወዘተ ዓይነቶች አዲስ አበባን ሞልተዋታል። ይህዝብ ብዛቱ የጎርፍ ያህል ነው። በሄዱበት ሁሉ ትርምስ ነው። ክልሎች ውስውጥ ህዝብ የተረፈ አይመስልም። አስመራና መቀለም ወጣቶች ስለመኖራቸው፣ ደቡብ አካባቢ ታዳጊዎች …. ብቻ ምን አለፋችሁ አዲስ አበባ ሞልታ ፈሳለች።
የዚህ ድርገጽ ባለቤት ያየውን እንዳለ በራሱ ግርምት አጅቦ ያካፍላል፡፡ አይቶ፣ ጠይቆና አጣርቶ መዘገብን የመሰለ የህሊና ፈውስ እንደሌለ ጻሃፊው መረዳቱን ሳያዩ “በውስጥ አዋቂ ነገረኝ” ታቤላ ለሚያንቦጫርቁ የማሰቢያ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው መጠቆም ይወዳል። በአንድ ካፌ ኤሊያስ መሰረትን የጻፈውን አንስተው ሲወያዩና ሙድ ይዘው ሲተርቡ ከነበሩ ሶስት ሰዎች ከቀዳሁት ልጀምር።
ውሾች ተገደሉ የሚል ዜና ከውስጥ አዋቂ እንደደረሰው ጠቅሶ ” ዓለም ዓቀፍ ጋዜጠኛ ” ኤሊያስ መሰረት መጻፉን ያዩት ተረበኞች “ኝ ምን ሆኖ ነው? ምን ተከልክሎ ነው?” እያሉ ይጠያየቃሉ። ኤሊያ ባለቤት አልባ ውሾች የሚርመሰመስባትን አዲስ አበባን ከበሽተኛና ተልከስካሽ ውሾች ማጽዳት የሚያስወግዝ ተግባር አድርጎ አቀረቧል፡፡ ቀጥሎ ዜናው በሚስጢር የተነገረው እንደሆነ ይገልጻ። ቀጥሎ መርዙ ዘመኑ ያለፈበት እንደሆነ በሚስጢር መስማቱን ያስከትላል። አክሎ አሞራዎችን ያዋልዳል። አሞራዎቹን የሞቱትን ውሾች እንዲበሉ ያደርጋል። ከዛ አየር ላይ ያንሳፍፋቸዋል። ከዛ ከዛው ከአየር ላይ እንዲጸዳዱ ያደርጋቸዋል። ከዛም ለድርሰቱ እንዲያመች አሞራዎቹን ውሃ ላይ እንዲጸዳዱ ያደርጋቸዋል። ድርሰቱን ተአማኒ ለማድረግ ባለሙያ በምናቡ ሳለ፡፡ በምናቡ የተሳሉት ባለሙያ ራሱ ኤሊያስ ውሃ ላይ እንዲጸዳዱ ያደረጋቸው በራሪ አሞራዎች ውሃውን በመርዙ ስለበከሉት ሰዎች በመርዙእንደሚያልቁ መተንበያቸውን አስነብቦ ብልጽናን አውግዞ ዜናውን እንደዘጋ ሰዎቹ ያወራሉ። ተረቡ ለጉድ ነው። ይስቃሉ።
ይህን ከሰማሁ በሁዋላ ወዲያውኑ “የሚገደሉ ውሾች ምን ደረጋሉ” ብዬ አግባብ ያለውን ተቋም ዝም ብዬ እንደ ተራ ነርዋሪ ጠየኩ። እንኳን አሞራ ጅብ እንኳን አመድ ዝቆ እንደማያገኛቸው አስረዱኝ። በጉዳዩ ዙሪያ ከአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር አወጋሁ። ባለቤት አልባ ውሾች ያጠቋቸውን አነጋገርኩ። ምን ልበላችሁ የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ ጤና ቢሮው በዚህ አግባብ መዘግየቱና ህግ አውጥቶ ባለቤት አልባ ውሾችን አለማስወገዱ ያስመሰኘው ካልሆነ በቀር አያስተቸውም። አድራሻ የሌለው ውሻ ነክሷቸው መርፌ የተጠቀጠቁትን ቤቱ ይቁጠራቸው …. ጠንባራዎቹ የመንግስት ሚዲያዎች ህዝብ ጠይቀው፣ ተዟዙረው የመስራት ባህልና ፍላጎቱ ስለሌላቸው እንጂ የተርከስካሽ ውሾች ጉዳይ አሳሳቢ ነው።
ከአንድ የአዲስ አበባ ውብ ህንጻ ስር አረፍ ብያለሁ። ሁለት ደላላ ቢጤዎች ደጋግመው ስልክ እየደወሉ ውል ያስራሉ። “በሊትር” የሚለው ቃል ቀልቤን ስለሳበው በራሴ ጉዳይ የተጠመድኩ መስዬ አደመጥኳቸው። ጨዋታው የነዳጅ ግብይት ነው። በዚህ ስራ የተሰማሩ ወረበሎች ለሚያሰማሩዋቸው አሽከርካሪዎችን መረጃ ያቀባብላሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው አንዳንድ በቤት መኪና ታርጋ ስም የሚነግዱ፣ የራይድ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ በታንከራቸው እየሞሉ ከአዲስ አበባ ውጭና አዲስ አበባ ጠርዝ አካባቢ በተዘጋጁላቸው ግቢዎች ውስጥ እየገቡ ይሸጣሉ። ስራው አዋጪ ስለሆነ ነዳጅ ካለበት እየሞሉ ነዳጅ ሲነግዱ ይውላሉ። ነዳጅ የሚነግዱትን ጨምሮ ” ነዳጅ ጠፋ” እያሉ የመኪና ሰልፎችን ፎቶ እያነሱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ይቀባበሉት ዘንዳ ያከፋፍላሉ። እንዲህ ያሉ ከስውነት ደረጃ የወረዱ ሌቦች አዲስ አበባ ውስጥ ተሰግስገው በህዝብ ስቃይ ገንዘብ ያመርታሉ.።
እርስ በርሱ የሚጓተት ተጻራሪ መንፈስ ስጋ ለብሶ አዲስ አበባ ላይ ይገማሸራል። ይህን መንፈስ ለማየት መንፈስ መሆን አያስፈልግም፡፡ አዲስ አበባን በርጋታ ላያትና ላደመጣት ብዙ ራሷ ታሳብቃለች። ከየትኛውም ፕሮፓጋንዳ ባለፈ መልኩ አዲስ አበባ ራሷ ትተርካለች። ወደ ሌሎች ሳንጠነቁል አዲስ አበባን ሊያድሱ የተነሱና አዲስ አበባን በሚያድሱ ውስጥ ባሉ የአንድ መንፈስ ሃይሎች መካከል ሳይቀር መጓተት ለጉድ ነው፡፡
በዚ የኢትዮሪቪው አዘጋጅ እይታ ነው አዲስ አበባ ውስጥ በብዙ መልኩ፣ በበጎና በክፉ የተሳከሩ ጉዳዮች እልፍ ናቸው። ስምንት ፍሬ ባለ አንድ ሊትር ውሃ 104 ብር የገዛ ነጋዴ፣ አንዱን ፍሬ ብቻ 75 ብር ይሸጣል። ቀላል ሱቅ ሳይቀር ትርፉ የሚሰላው ከሶስት መቶ ፐርሰንት በላይ ነው። ገዢውም አይጥይቅም፣ ተቆጣጣሪም የለም፣ ህሊና የሚባለው ውብ የሰው ልጆች ሚዛን ተንኮታክቷል። የሚያሳዝነው ደረሰኝ የሚጠይቅ ዜጋ አለ ማለት አይቻልም። ይህ ሁሉ ሲሆን የመንግስት ሚዲያ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የማህበራዊ ሚዲያ ፖስትና ጽህፈት ቤታቸው የሚያዘጋጀውን ፊልም እየተቀባበሉ ከማተምና ከማውራት ሌላ ወግ የላቸውም። የግል የሚባሉትም በጅምላ መንግስትን ከማማትና ከመዘልዘል ውጭ እንዲህ ያለውን ጉዳ መንካት አይፍለጉም።
ቦሌ መድሃኒያልም ኢድና ሞል ጀርባ ሃርመኒ ሆቴል ቦዘና ሽሮ ከ300 ብር ባነሰ ይሸጣል። እዛው ግድም እስከ 650 ብር ለአንድ ሽሮ የሚጠይቁ አሉ። ስድስት የዶሮ ክንፍ ከአንድ ማንኪያ ሩዝ ጋር 850 ብር የሚጠይቁ የሱቅ በደረቴ ይዘት ያላቸው ምግብ ቤቶችም አሉ። እዛው ሰፈር አንድ ሲኒ ቡና፣ ማኪያቶ፣ ወይም ሻይ ከመቶ ብር በላይ ነው። እነዚህን ሰብሰብ አድርጎ ማነጋገርና የዋጋ ተመን ስሌታቸው ምንን መነሻ ያደረገ እንደሆነ የሚጠይቅ ሚዲያ አገሪቱ የላትም። ተቆጣጣሪ የለም።
ይህን ማስታወሻ ከማዘጋጀቴ በፊት በተለያዩ ህገወጥ ጉዳዮች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር፣ ጥቆማ በመስጠት ውጤቱን ስጠብቅ ምንም የለም። በዚህና በተለያዩ መረጃዎች አዲስ አበባ በርካታ ጉዳዮች ተሳክረዋል ከሚል ድምዳሜ ደረሰኩ። ነገሩ ብዙ ነው ለሚረባውም፣ ለማይረባውም በሺህ ብር ክፍያ መጠየቅ ተራ ነገር ነው። አንድ ሲኒ ጁስ ከአራት እስከ ስምንት መቶ ብር ይጠየቅበታል። አስቡት አንድ ፓፓዬ አራት ስኒ ቢሆን ዋጋው ከሁለት ሺህ ይልቃል ማለት ነው። ይህ ስሌት በምንም መልኩ ፍትሃዊ አይደለም። ከዋጋ ስያሜ አመክኞ ውጭም ነው። ይህ መሳከር ካልሆነ በቀር፣ ይህ ህሊና ቢስነት ካልተባለ በቀር፣ ይህ የአደባባይ ዘረፋ ካልተባለ በቀር ምንም ዓይነት ስም አይሰጠውም። የሚዲያ፣ የተቆጣጣሪ ያለህ የሚል ዜና እያዜሙ መኖር ……
አዲስ አበባ በከፊል እየተሞሸረሽች ነው፡፡ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሚሰሙትና በውል አገር ውስጥ ያለው ለየቅል መሆኑን ለመረዳት ሰዓታት በቂ ናቸው፡፡ ሊገለጽ የማይችል መመንደግ አለ፡፡ የዛን ያህል ደግሞ ኑሮ የደፈቃቸው አሉ፡፡ ስግብግብ ነጋዴዎች፣ ችጋራም ሃብታሞች፣ አይን ያወጡ ቸርቻሪዎች፣ ህሊናቸው የታወረ ወዘተ አዲስ አበባን ሞልተዋታል።
ለሰው መመላለሻ በተሰሩ መንገዶች ላይ በሁለት ረድፍ ሞልቶ መኪና ማቆም ገሃድ ነው። ሰዎች መረማመጃ አጥተው ከምኪና ጋር ይጋፋሉ። በርንዳቸው ላይ የሚቸረችሩ ሆቴሎችና ህንጻዎች የመኪና ማቆሚያቸውን ንግድ ቤት በማድረጋቸው ከዋና መንገዶች ውጪ ባሉ የእግረኛ መንገዶች ላይ በነግጻነት መራመድ አይቻልም። ይዚህ ማስታወሻ ባለቤት በምስል አስደግፎ ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ቢያደርስም ወፍ የለም። ነገሩ የኮሚሽን ክፍያ ይኑረው ሌላ በቀጣይ እንዘልቅበታለን። እዚህ ላይ መካድ በማይቻል ደረጃ ውብ ሆነው የተሰሩ መንገዶች ጽዳት፣ ስፋት፣ ውበት ያረካል። ቢሰራ መለወጥ እንደሚቻል የሚያረጋግጡ ድንቅ ደንቅ ስራዎች እዛም እዚህም አሉ።
ለዛሬ ሁሉንም መንካት ባይቻልም ፈርሳ እየተሰራች ያለቸውን ፒያሳን ከአናቷ ለማየት አደዋ ሙዚየም ግባሁ። እንደገባኝ ከሆነ በአድዋ ሙዚየም ወደፊት ብዙ ቅርሶችን ለማሰባሰብ የታሰበ ይመስላል። ከምንም በላይ ግባታው ታሪኩን በሚመጥን ደረጃ መሰራቱና የአጤ ሚኒሊክን የጥሪ ነጋሪት መጎሰሜ አስደስቶኛል።
ጉብኝቴን ጨርሼ ሰገነቱ ላይ ስወጣ ኮንትራት ከተሰጠው ከካፌ በአንድ ዳር ላይ እንደ ቅርጫ ሰንጋ ተንጠልጥሎ ይበለታል። በላቾቹ ብዙ ናቸው። የሚበለተው ስጋ ብዙ ነው። ስጋ እየተሽነሸነ ወደ ኩሽና ይጋዛል። አስተናጋጄን ቀስ ብዬ ስጠይቅ፣ በበነጋው ከአራት ሺህ በላይ እንግዶች እንደሚኖሩና ከአስር በላይ ሰንጋ መዘጋጀቱን አስረዳኝ። ያን በመስለ ምንጣፍ፣ ያን በመሰለ ሙዚያም አናት ላይ ይህ መደረጉ ሌላ መሳከር ሆኖ ተሰማኝ። ምነው ሌላ ቦታ አዘጋጅተው ቢያመጡት አልኩ። እያዘንኩ ሂሳቤን ከፍዬ / መስተንግዶው ስፍራውን አይመጥነም ስወጣ በስተግራዬ ሌላ ቴራስ አየሁና ደረጃውን ወጣሁ።
ውብ ሰገነት ነው። አትክልቶች አሸብርቀውታል። እዛ ላይ እየተጋበዙ አዲስ አበባን ቁልቁል መኮምኮም ደስ ያሰኛል። ግን ቆሾሿል። ጃንጥላዎቹ የሚያጥፋቸው ባለመኖሩ ንፋስ ገነጣጥሏቸዋል። ከልብ ያሳዝናል። ያስደሰተኝ ኝ ከላይ ሲያዩዋት የፈረሰች የምትመስለው ፒያሳ ዳግም ከስር መሰረቷ እየተሞሸረች መሆኑ ነው። ሰራተኛ ሰፈር፣ እሪ በከንቱ ያከማቹት ድሪቶ የለም። ውብ ሆነዋል። “ባቅላባ የበላንበት፣ ቺክ የጠበስነበት ” ምናምን እያሉ ሲያላችኑ የነበሩ የዘመን ጉዶች የህሊናና የአፍ ወለምታ ቅሌት ከሚባለው ሙሉ ክብራቸው ጋር ወራዳዎች ስለመሆናቸው ፒያስ ራሷ ህያው ምስክር ናት። እስከ አራት ኪሎ ደረቷ በደንብ ተሰንጥቆ ለሰው ልጆች ምቹ መሆኗን ሳይ ሰገነቱ ላይ ያየሁትን ቆሻሻ ረሳሁት። አዳንች አቤቤ ሌት ከቀን የሚሰሩት አፍንጫቸው ስራ ያለውን ትልቁን የአድዋ ሙዚየም የሚጠብቅና የሚንከባከብ ሳያዘጋጁ መሆኑ ሊገመገመሙ የግባል ብዬ ማሽሟጠጤን የምታውቋቸው ንግሯቸው።
አደዋ ሙዚያምን ልሰናበት ስል ልቤን የሞላ፣ ህሊናዬን ያራሰ ጉዳይ ገጠመኝ። ስድስት ተማሪዎች አምስት ሴቶች፣ አንድ ወንድ መጥተው ሰላም አሉኝ። እንግሊዘኛ ቋንቋን ልክ እንደተወልጅ ይናገራሉ። ስርዓታቸውን ከአንደበታቸው የሚፈሰው ሁሉ ነበስን ያርሳል። ፌስ ቡክ እንደሌላቸውና አሁን ላይ በስማ በለው ስለሚረጨው የዘር ጣጣ ምንም እንደማያውቁ አስረዱኝ።
ብዙ አስገራሚ ውይይቶችን አደረግን በመጨረሻ ” ይህቺ አገር የናንት ናት የተበላሸው ትውልድ እየከሰመ ነው” አልኳቸው። የተበላሸው ትውልድ የዘር ፖለቲካ እየተጋተ ያደገውና፣ በዛው መንገድ አድጎ የአገሪቱን ቢሮክራሲ ይዞ አገሪቱን የሚገዘግዘው ነው። በነተበት የትምህርት ፖሊሲ እየኮረጀና መመረቂያ ጽሁፍ እየገዛ፣ በጉቦ ዲግሪ የተሸከመ የኢትዮጵያ አበሳ ነው። የተበላሸው ትውልድ እነ ጃዋርንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ትርምስ የሚያመርቱለትን ሳይጣራ እየተጋተ ኢትዮጵያን ያዘለው ነው። አሁን ላይ ከዛም ከዚህም በቀደመው መንፈስ ኢትዮጵያንና ህዝቧን እየጎተቱ ያሉቱ እየከሰሙ ለመሆናቸው ማሳያዎቹ እንዲህ ያሉት ናቸውና ተስፋዬ መለምለሙን ነገርኳቸው። አቀፉኝና ፎቶ ተነሳን። እነሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ትንታግ ታዳጊዎች ኢትዮጵያ እያፈራች መሆኗን በተለያዩ ጉብኝቶቼ አይቻለሁ። ሁሉም ጅምር የስለጠነ እሳቤና ለሰላም በተዘጋጀ ልብ ቢታገዝ የሚል ምኞት አሳደረብኝ። ኢትዮጵያ ታሳዝናለች፣ ታስቀናለች፣ ተፋ ታሲዛለች። በቀጣይ ያየሁትን እጻፋለሁ።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk