የቅርብ ጓደኞቹ እና ወዳጆቹ ሲጠሩት “ተፌ” እያሉ ነው። ተማሪዎቹ ተፈሪ ይሉታል። በቅርብም በሩቅም የሚያውቁት ትሁትነቱን ደጋግመው ይመሰክራሉ።
ለቃለ መጠይቅ በቀረበባቸው ፕሮግራሞች ላይ የሰውዬውን እርጋታ እና መስከን መታዘብ ይችላል። ሲያወራ ረጋ ብሎ ነው ከተመጠነ ቁጥብ ፈገግታ ጋር።
ይህ ሰው የሙዚቃ መምህሩ፣ ሚዩዚኮሎጂስቱ፣ ከበሮ መቺው እና ሙዚቀኛው ተፈሪ አሰፋ ነው።
ባለፈው ሳምንት አርብ፣ ጥር 16/2017 ዓ.ም. ከበሮ ተጨዋቹ እና የሙዚቃ ተመራማሪው ተፈሪ አሰፋ ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ተፈሪ ላለፉት 15 ዓመታት ለኢትዮጵያ ሀገረ ሰብ ሙዚቃ ማገር ነበር።
ተፈሪን የሚያውቁት የምት ሙዚቃ ሊቅ ይሉታል። የዕድሜውን ዕኩሌታ ያሳለፈው ከበሮ በመጫወት ነው።
ሙዚቀኛው እና አዋቂው ተፈሪ የመሠረተው ‘ነጋሪት ባንድ’ ዘወትር አርብ ምሽት ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ በሚገኘው የአፍሪካ ጃዝ መንደር ይጫወታል።
ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 16/ 2017 ግን ተፈሪ ከሚወደው ከበሮ ጀርባ ዳግም ላይቀመጥ፤ የሙዚቃ ወዳጆች የእጆቹን ምትሃት ለመመስከር ላይታደሉ ተፈሪ እስከ ወዲያኛው አሸልቧል።
በተፈሪ ህልፈት የሙዚቃ ወዳጆች፣ የጃዝ አድናቂዎች አዝነዋል። የቅርብ ወዳጆቹ ደግሞ ልባቸው ተሰብሯል።
ተፈሪ የሚያስተምርበት ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሆነው እዩኤል መንግሥቱ፤ “ተፈሪ ያለው ችሎታ ለሀገራችን ባህል እንደ ተፈሪ ጥናት ያደረገ ሰው የለም ስለዚህ በትምህርት በእውቀት ያዳበረው ችሎታ አለው።”
እዩኤል የተፈሪን የሙዚቃ አበርክቶ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ “ተፌን ሙዚቀኛ ብቻ አድርጎ ነው ሰው የሚያየው፤ ሙዚቀኛ ብቻ አይደለም። እርግጥ ትልቅ ሙዚቀኛ፣ የሙዚቃ መምህር እና ተመራማሪ ነው ግን ደግሞ ከዚያ ሁሉ በላይ የኢትዮጵያውያንን ባህል ማንነታችንን ተረድቶ እና ያለንን ጥልቅ የሆነ ሀብት ተገንዝቦ ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ዞሮ ለማስተላለፍ በጣም የተጋ ሰው ነው” ሲል ይገልጸዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በወጣው እና እዩኤል ፕሮዲውስ ባደረገው ‘የደጋ ሰው’ አልበም ላይ ተፈሪ ተሳትፏል። አልበሙ ላይ የተካተቱት 12ቱም ሙዚቃዎች ላይ ከበሮ እና ፐርከሽን የተጫወተው ተፈሪ ነው።
እዩኤል “አልበሙን አልበም ያደረገው እሱ ነው። ምክንያቱም እውነተኛ የሆነውን ሀገር በቀል የኢትዮጵያ ሙዚቃ አጨዋወት በደንብ ዘመናዊ አድርጎ ከመጫወት እና ከመረዳት አንጻር ያበረከተልን ነገር ቀላል አይደለም” ሲል የተፈሪን አስተዋጽኦ ይገልጻል።

ተፈሪ በአንድ ወቅት “ከበሮ ለእኔ እንደ ልብ ትርታ ነው” ብሎ ነበር። ተፈሪ ከአምስት ዓመቱ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ቀናቱ ድረስ ከበሮ ሲመታ ኑሯል፤ እንደ ልብ ምቱ ሁሉ።
ሚያዚያ 15/1964 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተወለደው ተፈሪ ነፍሱ ወደ ሙዚቃ በለተይም ወደ ከበሮ ያጋደለችው ገና በለጋ ዕድሜው ነው።
“የምት መሳሪያ ውስጤ ነበር” የሚለው ተፈሪ፤ ያገኘውን ነገር እየመታ ይጫወት እንደነበር ያስታውሳል። ብላቴናው ተፈሪ እጆቹን ያፍታታው ጠረጴዛ፣ የቤት ግድግዳ፣ ሶፋ፣ በመምታት ነበር። ጣሳ እና ብረት ድስትን ጨምሮ የቤት ውስጥ ዕቃዎችም አይቀሩትም።
በየዓመቱ ሐምሌ ወር ተፈሪ የሙዚቃ ችሎታውን የሚያሳይበት ጊዜ ነው። ሐምሌ የአባቱን አቶ አሰፋ ፀጋዬ ልደት ለማክበር ለዘመድ አዝማድ የሙዚቃ ድግስ ይዘጋጃል። እህቶቹ ይዘፍናሉ፣ እስክስታ ይወርዳሉ እሱ የሙዚቃ ድግሱን በከበሮ ያጅባል።
ለከበሮ ያለውን ፍቅር የታዘቡት እናቱ ባህላዊ ከበሮ ገዝተው ሰጡት። ከዚህ በኋላ ተፈሪ ውሎ እና አዳሩ እዚህ ከበሮ ላይ ሆነ። ወንድሞቹ ኳስ ሲያንቀረቅቡ እሱ ከበሮ ይመታል።
ተፈሪ የሙዚቃ ጉዞ ፈር መያዝ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነው። ተፈሪ ትምህርቱን የተከታተለበት ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት፤ ጆቫኒ ሪኮ፣ ሄኖክ ተመስገን እና ግሩም መዝሙርን የመሳሰሉ ሙዚቀኞች አፍርቷል። በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት በቢኒያም ፀጋዬ ስር ሙዚቃን ተምሯል።
የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለ የኢትዮ ጃዝ አባት የሚባሉት ከዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ተገናኘ። ከዚያ በኋላ ተፈሪ እና ጃዝ ተወዳጁ።
በደርግ መንግሥት የመጀመሪያ ዓመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አባቱ አቶ አሰፋ ፀጋዬ በትምህርት የሚያምኑ ሰው ናቸው። ራሳቸው ሁለት ዲግሪ እና ሦስት ዲፕሎማ ነበራቸው።
“ሙዚቃም ከሆነ በትምህርት መደገፍ አለበት” ብለው የሚያምኑት አቶ አሰፋ፣ ልጃቸው ሙዚቃ እንዲማር ገፋፉት።
በአፍላነት ዕድሜው የተዋወቃቸው ጋሽ ሙላቱ ደግሞ ፖላንድ አገር የሚገኝ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ጠቆሙት።
በ1980ዎቹ አጋማሽ ተፈሪ ወደ ፖላንድ አቀና። ተፈሪ ፖላንድ አገር በሚገኘው Karol Szymanowski Academy of Music በምት የሙዚቃ መሳሪያዎች በዲግሪ ደረጃ አጥንቷል። ትምህርቱን እዚያው በመቀጠል በተለያዩ የአፍሪካ የምት መሳሪያዎች ላይ ማስተርሱን ሠርቷል።

ጉዞ ወደ ላስታ
ተፈሪ ከሙዚቃ አካዳሚው ከተመረቀ በኋላ፣ ቤተሰቦቹ ወደሚገኙበት አሜሪካ አገር አቅንቷል። በአገረ አሜሪካ እንደ ጥላሁን ገሰሰ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ማህሙድ አህመድ እና አስቴር አወቀን ከመሳሳሉ ከአንጋፋ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ጋር ሙዚቃ ተጫውቷል።
“ላስታ ሳውንድ” ተፈሪ ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በመሆን ያቋቋመው የመጀመሪያ ባንድ ነው። ባንዱን የመሠረተው ከተማሪ ቤት ጓደኛው ኪሩቤል አሰፋ እና ፀጋዬ ሥላሴ ጋር ነው።
የብዙ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ጆሮ የሳበው የላስታ ሳውንድ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ባንድን ያካተተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሳሪያዎች ከተለያዩ የሙዚቃ ዓይነቶች ጋር ያዋህዳል።
የ”ላስታ ሳውንድ” በተለይ “ጥቁር ሴት” የሚለው ሙዚቃቸው በጣም ተወዳጅ ሆኖ ነበር።።
የባንዱን አባላት ሕይወት የተከተለ “Journey to Lasta” የተሰኘ ፊልምም ተሠርቷል። ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያሸነፈው ፊልሙ በሙዚቀኞቹ ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው። ተፈሪ አሰፋ፣ ኪሩቤል አሰፋ እና ፀጋዬ ሥላሴ ተሳትፈውበታል። ሙዚቀኞቹ የሚያልፉበት ትግል የፊልሙ ዋና ማጠንጠኛ ነው።
ተፈሪ በፊልሙ ላይ በቀን ከሦስት ሰዓት በላይ ልምምድ ሲያደርግ ይታያል። “ምንም አቋራጭ መንገድ የለም” የሚለው ተፈሪ ጠንክሮ በመሥራት ያምናል።
ተፈሪ ከላስታ ሳውንድ ቀጥሎ የተፈሪ ማረፊያ የሆነው ወዳሴ ባንድ ነው።
ውዳሴ በተፈሪ አሰፋ፣ ጆርጋ መስፍን እና ፋሲል ውሂብ የተመሠረተ የኢትዮ ጃዝ ባንድ ነው። በአትላንታ የተመሠረተው ውዳሴ ‘ሰላም’ የተሰኘ አልበም አውጥቷል።
አልበሙ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ቀጥታ የተቀዳ የጃዝ አልበም ነበር። ‘እንደ አባ ገሪማ’፣ ‘እቴሜቴ’ እና ‘ድለቃ’ የተሰኙት እንዲሁም በአልበሙ ውስጥ የተካተቱት ሙዚቃዎች ይበልጥ ታዋቂ ናቸው።
ባንዱ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ታዳሚዎች የመድረክ ሥራዎችን አሳይቷል። ለሁለት ዓመታት የቆየው ውዳሴ በአሜሪካ የተለያዩ መድረኮች ላይ ሙዚቃዎችን አቅርቧል።
የባንዱ መሥራቾች ተፈሪ፣ ጆርጋ እና ፋሲል ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም ለስምንት ወራት በአገር ቤት አንድ ላይ ተጫውተዋል።
ተፈሪ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለሱ “ትልቁን አስተዋጽዖ” ያደረገው ውዳሴ ባንድ እንደሆነ ተናግሮ ነበር።
ከ14 ዓመታት በፊት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ወደ ኢትዮጵያ ሙዚቃ በጥልቀት የመግባት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፤ ነገር ግን [ከአገር ቤት] መራቄ ይህን እንዳላደርግ ስለከለከለኝ ወደዚህ እንድመለስ አነሳሳኝ” ብሎ ነበር።

ውዳሴ ዘ-ነጋሪት
ተፈሪ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ሦስተኛውን ባንዱን ‘ነጋሪት’ን አቋቁሟል። ነጋሪት በውዳሴ ባንድ መሠረት ላይ የተገነባ የጃዝ ባንድ ነው።
ራሱ ተፈሪም በአንድ ውቅት “ውዳሴ ነው ለነጋሪት ባንድ መሠረቱ ብዬ አምናለሁ” ብሎ ነበር።
ተፈሪ ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ባንድ ከማቋቋም ሌላ ያደረገው ዋና ነገር ኢትዮጵያዊ ሙዚቃዎችን ማዳመጥ እና ማጥናት ነበር። በተለይ የብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ።
ተፈሪ ይህን ያደረገው በሩቁ በካሴት አይደለም። በአካል ወደ አካባቢዎቹ በመሄድ ሙዚቃዎችን አድምጧል፣ ታዝቧል፣ ቀድቷል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር በነበረው ቆይታ “ዋናው ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ‘ሪትሞችን’ (ምቶችን) ለማጥናት ነው” ያለው ተፈሪ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ብሔረሰቦች መካከል የግማሽ ያህሉን [የሙዚቃ ምት] በቪዲዮ እና በድምጽ ሰብስቤያለሁ” ብሎ ነበር።
ይህ ተሞክሮ ተፈሪ ‘ነጋሪት ባንድ’ን እንዲያቋቁም አድርጎታል። ነጋሪት ባንድ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ቅርሶቻቸው ላይ ያነጣጠረ የኤትኖሙዚኮሎጂ (የሙዚቃ ጥናት)፣ የአንትሮፖሎጂ ጥናት እና ትንተና ጥረቶችን የሚያካሂድበት መድረክ ነው።
የባንዱ ራዕይ “ሀገር በቀል ጃዝ” ቅጂዎችን ማዘጋጀት እና ማተም ሲሆን፣ ይህም በፍጥነት እየጠፉ ያሉ የዓለማችን ነባር (indigenous) ማኅበረሰቦችን ያልተበረዙ ምቶችን ለባንዱ የጃዝ ዝግጅቶች እንደ ዋና መሠረት ማካተት ነው።
ተፈሪ ወደ ሀገር ከተመለሰ አንድ ዓመት በኋላ ነጋሪት ባንድን መሠረተ። የባንዱን ስያሜ የመረጠው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ በአንድ ወቅት ተናግሯል።
የመጀመሪያው ምክንያት የባንዱ ስያሜ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጽ እንዲሆን ከመሻት የመጣ ነው።
ነጋሪት ኢትዮጵያዊ ነው። ለዓመታት “ምታ ነጋሪት፤ ክተት ሠራዊት” እየተባለ ጦር ታውጆበታል፣ እየተጎሰመ አዋጅ ተነግሮበታል።
ሁለተኛው ምክንያት ከተፈሪ የከበሮ ተጨዋችነት ጋር የተያያዘ ነው። ነጋሪት እንደ ከበሮ ሁሉ ሙዚቃ ለማጀብ አይሁን እንጂ የምት መሳሪያ ነው።
ነጋሪት ለጦርነት እና ለደቦ ሥራ ኢትዮጵያውያንን ሲያሰባሰብ ቆይቷል። ተፈሪ ደግሞ በነጋሪት ባንድ የኢትዮጵያውያንን ሙዚቃ አሰባስቦ ኅብረ ዝማሬ ፈጥሯል።
ባንዱ እንደሚጎሰመው ነጋሪት የአካባቢያዊ ርቀቶች እና የባህል ልዩነቶች ሳይገድቡት ልዩ የሆነ የሙዚቃ ውህድ ለዓለም ተመልካቾች ለማምጣት እና አዲስ የ”INDIGENOUS JAZZ” (ቀደምት ጃዝ) ዘይቤ ለመፍጠር እንደሚፈልግ በባንዱ ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።
ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ኦሪጅንስ’ የተሰኘ አልበም ለአድማጮች አድርሷል። አልበሙ ከአራት እስከ ዘጠኝ ደቂቃ እርዝማኔ ያላቸው 12 ሙዚቃዎችን ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ሰብስቦ ያሳተመው ፈረንሳያዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ስለ ‘ኦሪጅንስ’ አልበም በጻፈው መጣጥፍ “ተፈሪ ልዩ የሆነ ሀብት እያለው ብዙም ትኩረት ባላገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ሙዚቃዊ ጥናት አካሄዷል” ሲል ያሞካሸዋል።
‘ኦሪጅንስ’ ውስጥ የተካተቱት ሙዚቃዎች ብዙዎቹ የተቀዱት ቦታው ላይ ነው። ራሱ ተፈሪ በአካል ሂዶ ነው የቀዳቸው። ከጌዲዮ እስከ ኮንሶ፣ ከየም እስከ ጋሞ፤ ከአገው እስከ ትግራይ ቱባ የሆኑ የአካባቢዎቹ ሙዚቃዎች ተካትተዋል።

የአልበሙ የመጀመሪያ ሙዚቃ የሆነው ‘እማሆይ’ ለዕውቋ ኢትዮጵያዊት ሙዚቀኛ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ መታሰቢያ የተሠራ ነው። ሙዚቃው ከራሳቸው የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የፒያኖ ጨዋታ የተካተተበት ነው።
ቀሪዎቹ ሙዚቃዎች የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ናቸው። እነዚህ ብሔሮች በአልበሙ ላይ እንደ አንድ ዋና ድምጻዊ ከፊት እንዲገቡ ተደርገዋል።
የአልበሙ ሁለተኛ ሙዚቃ “አርባ ምንጭ” የጋሞ እና የወላይታ ምቶች እንዲሁም ድምጾች ለጆሮ ሳይጎረብጡ እንከን የለሽ ውህደት የፈጠሩበት ነው። አንጋፋው የወላይትኛ ሙዚቀኛ ቶካቶ መና የተሳተፉበት አርባ ምንጭ በጋሞ ድምጾች ተጀምሮ ወደ ወላይታ ድምጾች ይሸጋገራል።
ነጋሪት ባንድ የ”ላሊበላ’ (አባ ውዴን) እንጉርጉሮ ከዋሽንት ጋር አዋህዶ በአልበሙ አካትቶታል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተለመደው ባህላዊ ዋሽንት እና ትራምፔት ከኮንሶ ባህላዊ ድምጾች ጋር ተዋህደው በአልበሙ ውስጥ የተካተተውን “ካፋ ጫፎ” ወልደዋል።
የጋሞ እንስቶች ከሴት ጓደኞቻቸው ጋር ከሚጠራሩባቸው ስሞች አንዱ ‘ሳቦ’ ነው። ሞክሼዬ እንደማለት ነው። ሳቦ ሴት ልጆች ከሌሎች የሰፈራቸው ሴት ልጆች ጋር በየዓመቱ ለሚደረገው የሙዚቃ እና ዳንስ ውድድር እንዲቀላቀሏቸው የዘፈኑት ዘፈን ነው።
አንዲት የሰፈር ልጅ ካልተቀላቀለቻቸው ደጃፏ ላይ ያሉ ሴት ልጆች “ሳቦ” እያሉ ይሳለቁባትል።
‘ጉዋይላ’ ሌላኛው ‘ኦሪጅንስ’ አልበም ላይ የተካተተ ሙዚቃ ነው። ጉዋይላ በእምቢልታ እና በከበሮ ታጅቦ በትግራይ የሚደረግ ጭፈራ ማለት ነው። ነጋሪት ባንድ እምቢልታን በዋሽንት እና በኪቦርድ ተክቶታል።
አልበሙ ከሙዚቃዎች ስብስብ ባለፈ እንደ አንትሮፖሎጂ (የባህል እና ማኅበረሰብ) ጥናት ሊቆጠር ይችላል።
ኦሪጅንስ ውስጥ የተካተቱት ሙዚቃዎች የእያንዳንዱን ብሔረሰብ የሰርክ ተግባር ማሳየት ይችላሉ። የኮንሶ አርሶ አደሮች የሚያንጎራጉሩት ‘ካፋ ጫፎ’፤ የጌዴኦ ሴቶች እንሰት ሲቆርጡ የሚያዜሙት ‘ቴዳኦ’ ለዚህ ማሳያ ናቸው።
ኦሪጅንስ አልበም ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎችን አግኝቷል። የእንግሊዙ ‘ሶንግ ላይን’ ጋዜጣ ‘የ2024 ጥር እና የካቲት Top of the world track’ ዝርዝር ውስጥ አርባ ምንጭ የሚለውን ሙዚቃ አካትቶታል።
በአውሮፓ የዓለም ሙዚቃ ሰንጠረዥም ላይ አልበሙ ተካትቷል።
ቢቢሲ – የጽሁፉ ባለቤትና ብቸኛ ተመስጋኝ ነው። ቢቢሲ ጊዜው ወስዶ ለሰነደው ታሪክ ምስጋና አርበናል
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk