በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር የሚተኮሱ ሃብታሞችን ማየት የተለመደ ነው። ይህ ምንጩ ግልጽ ያልሆነ ሃብት ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ሕዝብ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ፣ በድብቅ ሲያማ እንደነበር ይታወሳል። በተለይም ተቃዋሚዎች ሌብነትን የሚሸከም መንግስት እንደሆነ በመግለጽ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ኖረዋል።
ምንጩ የማይታወቅ ንብረትን አስመልክቶ አዲስ ሲወጣ በዋናነት የተቀመጠው ቀደም ሲል የነበሩ ህጎች ለአፈጻጸም ችግር በመሆናቸውና ወንጁእለኞች በህገወጥ ያፈሩትን ንብረት ቢፈርድባቸው እንኳን ሊያጡ የሚችሉበት አግባብ አለመኖሩ ነበር።
አስር ዓመት ወደሁዋላ ተመልሶ እንዲሰራ ፓርላማ ፈቃድ የሰጥው ግፍ ህጋዊ ባለንብረቶችን፣ በህጋዊ አግባብ ንብረት ያፈሩና ገቢያቸው፣ የሚከፍሉት ግብርና ወዘተ የሚጣታመውን የማይነካ መሆኑ በግልጽ ቢነገርም፣ ህጉ ወደ ተጋር ሲመነዘር ልክ ቀደም ሲል ህጉ ሲወጣ እንደሆነው ጫጫታ ማስነሳቱ በርካቶችን አስገርሟል።
በደቦ ህጉን “መንግስት ሊዘርፍ ነው” የሚል ታቤላ በመለጠፍ የሚቃወሙትን ወገኖች ለመገሰጽም ሆነ ለመከራከር አስቸጋሪ መሆኑን የሚናገሩ የህግ አዋቂዎች፣ አፈጻጸሙ ላይ ጥንቃቄ ማድረጉ ላይ ሊተኮርበት እንደሚገባ ከማሳሰብ የዘለለ አሁን ላይ ብዙም አስተያየት መስጠት አግባብ እንዳልሆነ ይናገራሉ። የሚቃወሙትም አካላትና ሚዲያዎች አንድና ሁለት መስመር ጽፈው በቁንጽል ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ማዕበል ለማስነሳት ከሚሞክሩ በአመክንዮ የተቃውሟቸውን ጭብጥ ሊያስረዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017ን አስመልክቶ የተሰጠውን ጋዜኛዊ መግለጫ የሚኒስቴሩ ማህበራዊ ገጽ ላይ በዚህ መልኩ ታትሟል። ከስር ያንብቡ።
የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጥር 1ቀን 2017 ዓ.ም የፀደቀዉን የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017ን አስመልክቶ ለመንግስት እና የግል የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በዛሬዉ እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 በጥር 1 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን ተከትሎ የአዋጁን ዓላማ፣ መሠረታዊ ይዘቶች፣ እንዲሁም ቀጣይ አተገባበር በተመለከተ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ለማጥራት መግለጫ መስጠት ማሰፈለጉን የገለፁት ክብርት ሚኒስትሯ፣ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በወንጀል የተገኘ ሃብት ማስመለስን በተመለከተ ራሱን የቻለና ወጥ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ያልነበረ በመሆኑ በሕግ ማስከበር ሂደት በጣም ክፍተት ፈጥሯል።
የወንጀል ሕጉን ጨምሮ በተለያዩ አዋጆች የሃብት ማስመለስ ሥነ-ሥርዓትን በሚመለከት የተካተቱ ድንጋጌዎች በራሳቸው የተሟሉ ካለመሆናቸው ባለፈ አንዱን ከሌላው ጋር እያስማሙ ለመተግበር አስቸጋሪ የሚያደርጓቸው ድንጋጌዎችን የያዙ እና ተፈጻሚነታቸውም ውስን የሆኑ ወንጀሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተቀረጹ በመሆኑ በርካታ በማህበረሰቡ ላይ ጉዳትን በሚያደርሱ ወንጀሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻልም። በዚህም ወንጀል ፈፃሚዎች ከወንጀል ድርጊት ያገኙትን ንብረቶች በማስመለስ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የሕግ እና አሰራር ክፈተቶች እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ አክለውም ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ እስካሁን ባሉን ሕጎች ተጠያቂ የሚሆኑት የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች ሲሆኑ ሌሎች ሰዎችን የማይመለከት በመሆኑ ሰፊ በሚባል ደረጃ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት የማፍራት ሁኔታ ተስተውሏል።
የዚህ ሕግ አለመኖር ሌሎች የመንግስትና ሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞች በቀላሉ በሕገ-ወጥ መልኩ ያፈሩትን ንብረት በእነዚህ ሰዎች ስም ለማፍራት እና ለመደበቅ እንዲችሉ ትልቅ አስተዋጽዖ አድርጓል ብለዋል።
በሌላ በኩል አዋጁ የዜጎችን የንብረት መብት ተገቢ ጥበቃ ለማረጋገጥ ብዙ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ፣ በቅን ልቦና ንብረትን የያዙ ሰዎች በቅን ልቦና የያዙት ንብረት እንዳይወረስ ተገቢውን ጥበቃ ሰጥቷል።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በሚመለከት ለማስረዳት የሚቀርበው የማስረጃ አይነት እንደየ አግባቡ የተለያየ ሊሆን ይችላል። የንብረቱን አመጣጥ የማስረዳት ሸክም ያለበት ሰው በማንኛውም ያስረዱልኛል በሚላቸው የማስረጃ አይነቶች ሊያስረዳ የሚችል ሲሆን የማስረጃው አጥጋቢነት ደግሞ በፍርድ ቤት የሚመዘን ይሆናል።
በመሆኑም የንብረት ማስመለስ ሕግ መውጣት ዜጎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን የእኩል ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እና የግለሰቦችን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ንብረት የማፍራት ባህልን በማሳደግ ጠንካራ የሆነ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋዕፆ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
የዚህ ሕግ አተገባበር በሰዎች የንብረት መብት ላይ ያልተገባ ተጽዕኖን እንዳይፈጥር እና የሕግ አስፈጻሚ አካላት ባልተገባ አሰራር የዜጎችን መብት እንዳይጥሱ በሚያስችል መልኩ እንዲተገበር አዋጁ የአደረጃጀት እና የአሰራር መፍትሔዎችን አካቷል ያሉት ክብርት ሚኒስተሯ፣ አዋጁ የሚተገበረው በፍትሕ ሚኒስቴር በተማከለ አደረጃጀት ለዚህ ሥራ ዓላማ በሚደራጅ የሥራ ክፍል በመሆኑ ግልጽ የአሠራር ሂደትና የተጠያቂነት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተገልፆል።
ምንጩ ያልታወቀ ንብረትን በተመለከተ በቅድመ ክስ ሂደት ማንኛውም ሰው ጉዳዩን እንዲያስረዳ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እና አቤቱታዎች የፍርድ ቤቶች የሥነ ሥርዓት ሕጎችንና መርሆዎችን ተከትለው ጥብቅ የሆነ ማጣራት የሚደረግባቸው ሲሆን አቤቱታ የሚቀርብባቸውም ሰዎች በሕጉ መሰረት ያላቸውን ማስረጃዎች የማቅረብ እና በፍርድ ቤት ዘንድ ቀርበው የመደመጥ መብታቸው እንዲከበርላቸው ይደረጋል።
ለሥራ ክፍሉ የሚቀርቡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን የሚመለከቱ ጥቆማዎችም ሆነ ጥርጣሬዎች ጥብቅ በሆነ አሰራር የሚጣሩ እና በቂ ምክንያት መኖሩ የሚታመንባቸው ጉዳዮች ብቻ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱበት የአሰራር ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናልም ተብሏል።
በአጠቃላይ የንብረት ማስመለስ ሕግ በኢትዮጵያ ሰዎች ከወንጀል ድርጊት የሚያፈሩትን ሀብት እና ምንጩ ሳይታወቅ የሚያገኙትን ንብረት በመቆጣጠር እና ሲገኝም ለማሕበረሰቡ ተመላሽ እንዲሆን በማድረግ ወንጀል አትራፊ ሥራ እንዳይሆን ማድረግን እና በአጠቃላይ ደግሞ ማህበራዊ ፍትሕን ማስፈንን አላማው አድርጎ የጸደቀ እና ይህንን ዓላማ በሚያሳካ አግባብ ጥብቅ የሆነ የአፈጻጸም ሥርዓትን የሚከተል የሕግ ማዕቀፍ ነው ሲሉ ክብርት ሚኒስተሯ አብራርተዋል።