በኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድ የሚፈልገው ልማትና ብልጽግና መሆኑን የብልጽግና ፕሬዚዳንት ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውንን ዘርዝረው የግጭቶቹ ሁሉ ጠንሳሾችና ጨማቂዎች ትላንትና ፖለቲካ ሲያንቦራጭቁ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።
15.7 ሚሊዮን የሚሆኑ አባላት እንዳሉት ያስታውቁትን ብልጽግናን የሚመሩት አብይ አህመድ ፓርቲው በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ እያደረገ ባለው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከመጀመሩ በፊት ህጻናት ያዘጋጁትን የስዕል አውደ ርዕይ ተመልክተዋል። በመክፈቻ ንግግራቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ “ግጭት በቃን፣ እንሰልጥን፣ እንነጋገር” ሲሉ የፓርቲያቸውንና የራሳቸውን ፍላጎት ገልሰዋል። አብይ በዚሁ ንግግራቸው “በ60ዎቹ የታጠቃችሁትን ክላሽ አውርዱ” ሲሉ “የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያንቦራጭቃሉና ግጭት ጠንሳሽ ” ላሉዋቸው ጥሪ አቅርበዋል። ወቅቱ የድርድር እና የውይይት በመሆኑ ይህንኑ አግባብ በመምረጥ የወደፊቱን ትውልድ ዕጣ ፈንታ ከማበላሸት መቆጠብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ብልጽግና በሰላም፣ በድርድር፣ በውይይትና በሃሳብ ለሚደረግ የፖለቲካ ትግል፤ ግማሽ መንገድ የመሄድ ልምምድ ባለፈው አሳይቷል። አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም “ፖለቲካን በቅጡ አልተለማመዱም” ሲሉ የቀደሙትን ፖለቲከኞች ወርፈዋቸዋል። “አባቶቻችን ሀገርኛ ሀሳብ አላፈለቁም። በተዋሱት ሃሳብ ሲጨቃጨቁ፣ ሲጋደሉ የኖሩ ስለሆነ፤ አሁንም ያንን ማስቀጠል ይፈልጋሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።
የፓርቲውን ያለፉት ዓመታት ጉዞ “የመነሳት ዘመን” ሲሉ የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ከጥልቅ እንቅልፍ፣ ከብዙ ዕዳ፤ መንቃት፣ መነሳት፣ የጀመርንበት ምዕራፍ ነበር” ሲሉ ጊዜውን ገልጸውታል። “የመጀመሪያው የመነሳት ምዕራፍ አብቅቶ፤ አሁን በዚህ ጉባኤ የሚጸድቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የማንሰራራት ዘመን ነው” ሲሉም አክለዋል።
አብይ በዛሬው ንግግራቸው “የማንሰራራት ዘመን፤ የቁልቁለት ጉዞ፣ የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበት ማለት ነው” ብለዋል። ከገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ባሉት ወራት፤ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች “የሚመረቁበት” እንደሆነም አስታውቀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ፓርቲው ቃል ከገባቸው ጉዳዮች መካከል “በኢትዮጵያ ቶርቸር ይቁም” የሚለው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል። አክለውም ብልጽግና ፓርቲ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት” በተጓዘበት “የመጀመሪያ ምዕራፍ” ካሳካቸው ጉዳዮች መካከል ላለፉት ስድስት ዓመታት፤ አንድም ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ torture አለመደረጉ ነው። ” ብታምኑም ባታምኑም” ሲሉ የገለጹትን የቶርቸር ዜና ” በዚህ ተግብራችን እንኮራለን” ሲሉ ገልጸውታል። ባለፉት ጊዚያት በኢትዮጵያ ቶርቸር መደረግና በማይታወቁ እስር ቤቶች መሰቃየት የተለመደ ሲሆን፣ በርካቶች በላቸውን ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወሳል። ከማዕከላዊ እስር ቤትና ከሶማሌ ክልል ማጎሪያ የወጡ ዜናዎች ለስምስማትም የሚከብዱ መሆናቸው አይዘነጋም።
“ብልፅግና አልቆ መገንባትን አስቀድሞ የሚያስብ ፓርቲ ነው”- የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ብልፅግና ፓርቲ ሊያፈርስ የሚፈልገውን ብቻ ማፍረስ ሳይሆን አልቆ መገንባትንም አስቀድሞ የሚያስብ ፓርቲ ነው ሲሉ የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ብልፅግና ሊያፈርስ የሚፈልገው በርካታ ኋላቀር አሰራሮች እና ልምምዶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ ቢያውቅም አልቆ መገንባትን አስቀድሞ የሚያስብ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም ነው “ፒያሳን ማፍረስ ሳይሆን አልቆ መገንባት የብልፅግና መለያው የሆነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ 60 ዓመታትን ያልተሻገረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ ዓመታት የነበረን የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንፈልገውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት የነበረበት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርቲ ፖለቲካ ስንጀመር ብልፅግናን እስከፈጠርንበት ድረስ ያሉ ድካሞች ውድቀቶች ልንሻገራቸው ያልቻልናቸው አንድ ፓርቲ ለውጥ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ለውጥ መሪ መሆኑን አለመገንዘባችን ነው” ብለዋል፡፡
ለውጥ መፍጠር ብቻውን ለውጥ ለመመራት የሚያስችል ብቃት እስካልፈጠረ ድረስ የተሟላ የፓርቲ ህልውና አይኖረውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለውጥ መፍጠር ማለት ስላለው ችግር ድካም ውድቀት አብዝቶ መናገር ሳይሆን መፍትሄም ማፍለቅ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሃምሳ እና ስልሳ አመታት የነበረን የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፤ ልናፈርስ ልንንድ የፈለግነውን በብዙ ማስረጃ መክሰስ እንጂ ልንገነባ የምናስበውን ልናመጣ የምንመኘውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት ነበረብን” ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያ ብልጽግና ጉዞ አይቀሬ ነው” – የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፓርቲው ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ብልጽግና ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ የመጀመሪያው ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአንድ ፓርቲ ዋና እስኳሉ ሃሳብ እንደሆነ በጉባኤው ላይ የተናገሩት የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሃሳብ ያለው ፓርቲ ለውጥ መፍጠርም መምራትም ይችላል ብለዋል።
በዘመቻ የጀመርናቸው ስራዎች ባህል መሆን አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ እንዲሁ ባህል ልናደርገው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ጉባኤ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባኤ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ብቻ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ብልፅግና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ልምምድ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል የሆነ እሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ መሆኑንም አመልክተዋል።
ብልፅግና ለኢትዮጵያ ፍቱን መድሀኒቱ መደመር ነው ብሎ ሲመጣ ላለፉት ስድስት አመታት ብልፅግናን መክሰስ እንጂ ማንም አማራጭ ሃሳብ ይዞ አለመምጣቱ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
ይህም ሆኖ በተቀዱ ሃሳቦች ላለፉት በርካታ አመታት የገጠሙንን ችግሮች ስለምናውቅ የኢትዮጵያን ተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ ሀገር በቀል ሃሳብ ቢያቀርቡ ብልፅግና ለመማር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ሃሳብ የነጠፈበት አካባቢ ማፍረስ ቢቀልም መልሶ መገንባት ግን መከራ ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ ቢፈጠር ለመማር ዝግጁ ነን ብለዋል።
ሙሉ ንግግራቸውን ለማግኘት:- https://youtu.be/vSRbh9kqsXI?si=sp3prpyP3gmcQgiz
ዜናው ከኢቲቪ፣ ኢንሳይደርና ከዩቲኡብ ንግግራቸው የተወሰደ ነው