ኢሳያስ በየትኛውም መንገድ ኤርትራ ምድር ላይ ጦርነት እንዲደረግ አይፈቅዱም። ኢትዮጵያ ላይ ታጣቂና አማጺ ሲያደራጁ እድሜያቸውን የፈጁትና አሁንም ይህንኑ እየሰሩ ያሉት በዚሁ ፍላጎታቸው ነው። ይህ ፍላጎታቸው የሚመነጨው ደግሞ ካላቸው ስጋት እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚሰማ ጉዳይ ነው። አሁን ላይ በሚወጡ መረጃዎች የጎጃም ፋኖዎችና የእነ ደብርረጽዮን ትህነግ ኃሎች ጦርነቱ አማራ ክልል ላይ እንዲሆን መስማማታቸውን ኢትዮሪቪው ሰምታለች። ለዚሁ ማረጋገጫ የፋኖ የህዝብ ግንኙነትን ጨምሮ በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ የፋኖ አካላት “በቅርቡ ኮንቪክሽናል ጦርነት እንጀምራለን” ሲሉ ተድምጠዋል። ከመንግስት በኩል በዲፕሎማሲው አግባብ ሩጫ ከመደረጉ በዘለለ ይህን አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም።
ሰሞኑን እንደሚሰማው ሻዕቢያ ኤርትራ እንደምትወረር፣ አሰብን ለመውሰድ ዝግጅት መጠናቀቁን በተለያዩ መድረኮችና በፌስቡክ ባሰማራቸው ፕሮፓጋንዲስቶቹ አማካይነት እየገለጸ ነው። ይህንኑ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አገራቸው ክተት እንደትል ባዘዙት መሰረት ህጻን ሽማግሌ ሳይል ሁሉም ጦር እንዲያነሳ ታዟል።
ከአንዱ የትህነግ ፍንካች ጋር ዳግም ፍቅር የመሰረተው ሻዕቢያ ምንም ያህል ክተት ቢያውጅም ጦርነት እንደማይከፍት በዱባይ የሚገኘው የኢትዮሪቪው ተባባሪና የቀድሞ የሻዕቢያ ሰላይ ይናገራል። አክሎም ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች አሁን ላይ ኤርትራ ውስጥ እየተከናወኑ መሆናቸውን ይጠቅሳል።
” አሁን ላይ በኤርትራ ያለው ስሜት ልክ በትግራይ እንደሆነው ዓይነት ነው” የሚለው ተባባሪያችን፣ በትግራይ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የትግራይ ህዝብ እንደተከበበ፣ ሊጠፋ እንደሆነ፣ ህልውናው አደጋ ላይ እንደወደቀ ተደርጎ በከፍተኛ ደረጃ ዲጂታል ወያኔ ይቀሰቅስ እንደነበር፣ በዚህም ቅሰቀሳ ሳቢያ የትግራይ ህዝብ “ጦርነቱ የህልውና ነው” በሚል ሙሉ ድጋፍ እንዲያደርግ ተገዶ እንደነበር ያስታውሳል። ሆኖም ግን የትግራይ ህዝብ ሁሉም ነገር ግልጽ የሆነለት ከጦርነቱ በሁዋላ መሆኑን ያስታውሳል።
በዚህ መነሻ ኤርትራ ልትወረር እንደሆነ፣ አሰብ ሊወሰድ እንደሆነ፣ የባድመና አካባቢው አወዛጋቢ ስፍራ ሊነጠቅ እንደሆነ በየመዋቅሩ ለኤርትራ ህዝብ እየተነገረው ያለው ጦርነቱን የኤርትራ ህዝብ ልክ እንደ ትግራይ ህዝብ የህልውና አድርጎ እንዲማገድ መሆኑን ያስረዳል። ይህንኑ ለማጠንከር በፌክ አካውንት በተከፈቱ የማህበራዊ ሚዲያዎች “አሰብ በቅርብ ቀን ወደ ባለቤቷ” በሚል ሆን ተብሎ መረጃ እንዲሰራጭ እየተደረገ መሆኑን ያክላል። ይህ የመጀመሪያው ሁነት ሲሆን፣
በሁለተኛ ደረጃ ህዝቡ ሻዕቢያን መጥላቱ ነው። በኤርትራ ህዝብ በሻዕቢያ መማረሩን ያስታወቀው ይኸው የቀድሞ ሰላይ፣ አሁን ባለው መረጃ ኤርትራ ህዝቡን ከማስተባበር በዘለለ ጦርነት ውስጥ እንደማይገባ በእርግጠኛነት ይግለጻል።
ላለፉት አራት አስርት ዓመታት የተከናወነውን አስመልክቶ “በኤርትራ ሰዓት ቆሟል” በሚል የደመደመው ዶክመንታሪ ፊልም እንደሚያስረዳው ኢንተርኔት የለም። ያለውም ፋይል ማላክ ያማያስችል የኢንተርኔት ካፌ ሲሆን ቁጥጥር አለበ። ኤለክትሪክ የለም። ቱሪስት የለም። ወጣቶች አይታዩም ብዙ ነገሩ የቆመባት ከተማ ናት።
ቀደም ሲል በተለያዩ ሪፖርቶች ሻዕቢያ የአማራ ክልል ታጣቂዎችን እንደሚያሰለጥንና በውክልና እንደሚያስታጥቅ ይፋ ይደረገው የደህንነት ሰራተኛ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጦርነቱ በኤርትራ ምድር እንዳይሆን አጥበቀው እንደሚሰሩ አመልክቷል። በተመሳሳይ ቀደም ሲል ያነጋገርናቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኦፌኮ አመራር፣ በተመሳሳይ ኤርትራ ጦርነቱ ኤርትራ ምድር ሳይደርስ በትግራይ ዳግም እንዲጀመር ፍላጎት እንዳላቸው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ለመድረስ ውይይት ማድረጋቸንና ለጊዜው አማራ ክልልን ዋንኛ የጦርነት ቀጠና ላማድረግ ማቀዳቸውን ገልጸው ነበር።
ጦርነቱ በአማራ ክልል ብቻ እንዲሆን የትግራይ ሓይሎች በቅጽበት ወደ አማራ ክልል ዘልቀው እንዲገቡና ከአማራ ክልል ታጣቂዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ሻዕቢያ ያወጣውን ዕቅድ የነ ዶከተር ደብረጽዮን ቡድን መቀበሉን መርጃዎች እየጠቀሱ በርካቶች ቢግለጹም፣ ያልተጠበቀ ተግዳሮት እንደገጠማቸው ተሰምቷል።
የአንደኛው ትህነግ ወገን የሚያስተባብራቸው ኃይሎች፣ ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ጦርነቱን መቃወሙ፣ ትህነግን በጦርነቱ ወቅት ሲደግፉ የነበሩ ሚዲያዎችና የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከሻዕቢያ ጋር የተደረሰውን ስምምነት መቃወማቸው፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የተቀናቃኝ ደርጅቶችም በገሃድ አካሄዱን መንቀፋቸው ትግራይ ላይ ሻኧቢያ አመቺ ሁኔታ እንዳይገጥመው፣ ይልቁኑም አስፈሪ እንደሆነበት እየተሰማ ነው። ከሁሉም በላይ በትግራይ ኃይሎች ውስጥ ሻዕቢያን መበቀል የሚፈልጉ ወገኖች መኖራቸው ሌላው ሻዕያን ያሰጋ ጉዳይ ሆኗል።
ከሁሉም በላይ ከወልቃይት አቅጣጫ የሚሰማው ዜናና ዝግጅት ለትህነግም ሆነ ለሻዕቢያ ሌላ ራስ ምታት እንደሆነም ይሰማል። ቀደም ባሉ ሪፖርቶች እንደተመለከተው በጎጃም የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ኃይል ወልቃይትን አስመልክቶ የመሰጠረው ጉዳይ እንዳለ ታውቋል። ይህ መረጃ በርካታ የፋኖ አደረጃጀቶችን በተለይም ከጎንደር አቅጣጫ ቁማናቸውን ያስቀየረና ወልቃይት ላይ የብረት አጥር እንዲሰራ ምክኛት እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎችና አክቲቪስቶች በስፋት መረጃ እያሰራጩ ነው።
ከላይ እንደተገለጸው ትግራይን የጦርነት አውድማ ለማድረግና ስጋቱን ለማስወገድ እየሰራ ያለው ሻዕቢያ አሁን ላይ በክተት ኃይሉን እያጠናከረ ቢሆንም ከጎጃም አካባቢ ፋኖዎች ዘንዳ በቅርቡ ” ኮንቬክሽናል ጦርነት እንጀምራለን” የሚለው ተደጋጋሚ መግለጫ እነ ደብረጽዮንና እነ ዘመነ ካሴ አማራና የትግራይ ክልልን የጦርነት መነሻ ለማድረግ ሻዕቢያ የሰጣቸውን መመሪያ ስለመቀበላቸው ነው።
ምንም እንኳን ከጀርባ ግብጽንና ሳኡዲን፣ እንዲሁም የየመን አማጺዎችንና የሶማሌውን መሪ ሃሰን ሼክን የያዘው የኢሳያስ መንግስት አሁን ባለው ኃይል ወያኔንና የጎጃም ፋኖን በማነሳሳት የፕሮክሲ ጦርነት ከመክፈት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው የዱባዩ ነዋሪና የቀድሞው ሰላይ ይናገራል።እሱ እንደሚለው ሻዕቢያ በማናቸውም መስፈርቶች ኢትዮጵያ ምድር ላይ ወረራ የመፈሸም አቅም የለውም።
አንድን አገር ለመወረር ከሚወረረው አገር ሰራዊት ቢያንስ አራት እጥፍ ሊኖር እንደሚገባ ጠቅሶ ሻዕቢያ ይህን ያኽል ኃይል እንደሌለው በማሳየት ሻዕቢያ ወረራ መፈጸም እንደማይችል ተባባሪያችን ይናገራል። በሌላ በኩል ወረራ የሚሰነዘርበት አካል ወረራ ከሚፈጽመበት ኃይል አንድ ሶስተኛ ያህል ካለው መከላከል ይችላል። ይህን መስፈር በማንሳት ኤርትራ ከመከላከል ይልቅ ሌላውን አማራጭ ለመከተል አታስብም። ካሰበችም አይሆንም። በዚህ ምክኛት ነው ወያኔንና ፋኖን በውክልና ለማዋጋት ደፋ ቀና እየተባለ ያለው ሲል አስተያየቱን ያሰፋል።
ወያኔ መከላከያን ሲያጠቃ በኃይል አሰላለፍ አምስት እጥፍ የበላይነት ይዞ እንደነበር የትግራይ ኃይሎችን መግለጫ ዋቢ አድርጎ የሚናገረው የሻዕቢያው ሰላይ፣ ያም ሆኖ አለመሳካቱን በማንሳት ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የገነባቸው ኃይልና የታጠቀችው መሳሪያ በፍጹም ከሻዕብያና ወያኔ ጋር ስለማይነጻጸር ሻዕቢያ በራሱ ውጊያ ውስጥ ይገባል የሚል እምነት እንደሌለው በግል ካሉት መረጃዎች በመነሳት ድምዳሜውን ያስቀምጣል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት ከገባ ውጊያው የሚሆነው በከባድ መሳሪያና በዓየር በመሆኑ ወያኔዎቹም ሆነ ሻዕቢያ ያንን ለመቋቋም ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባ፣ ምንም ዝግጅት ቢያደርጉ ሊቋቋሙ እንደማይችሉ፣ ይህም ወያኔ ደብረ ብርሃን በደረሰበት ወቅት በቂ ልምድ በመኖሩ ችግርን በውይይት መፍታቱ ይሻላል የሚል እምነት እንዳለውም አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ የባህር በር የማግኘቷ ጉዳይ ያለቀለት በመሆኑ፣ ሃሰን ሼክም ቢሆኑ እንደቀድሞው ኢትዮጵያ ላይ እንዳይዛበቱ በራሳቸው የጎሳ ሰዎች ከንግድ ጥቅማቸው በመነሳት ስለተነገራቸው፣ ኢትዮጵያ አሰብን ልትወስድ ነው የሚባለውና ይህንኑ በማራገብ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተከፍሏቸው የሚያሰራጩ ለሻዕቢያ ቅስቀሳ አመቺ መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች እዚህ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሰጥቶ መቀበል ሂሳብ አሰብን ለመጠቀም መጠየቃቸው እየታወቀ፣ ንግግራቸውን በማጣመመ ሻዕቢያ የኤርትራን ህዝብ ለህልውና ጦርነት እንዲዘጋጁና ጥላቻቸውን በመተው በአንድነት እንዲነሱ እየተጠቀመበት በመሆኑ ሚዲያዎች ይህን ጉዳይ ማጥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የግብጽ የስለላ ተቋም ሃላፊ ጀነራል ጀማል አባስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብደላቲ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል። በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ከዚህም ባሻገር ለአስርት አመታት ግንኙነታቸው የሻከረውን የኤርትራ መንግስት እና ህወሓት በማቀራረቡ ረገድ ካይሮ ድርሻ እንዲኖራት ጥያቄ ማቅረቧን ዘናሽናል መዘገቡ አይዘነጋም። ይህ ግብጽ በሁሉም አገባብ እጇ ስለመኖሩ ነው።
የኤርትራ መንግስት ክተት ስለማወጁ ቢቢሲ ትግርኛው የአስመራ ነዋሪዎችን አነጋግሮ የዘገበውን ከስር ያንብቡ
የኤርትራ መንግሥት የቀድሞ የሠራዊት አባላት ወደ የክፍሎቻቸው ለዳግም ሥልጠና እንዲመለሱ እና ሌሎችም ከአገር ለመውጣት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እንዳጠበቀ በኤርትራ ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የሚገኙ የአገሪቱ ዜጎች ለቢቢሲ አረጋገጡ።
በዚህ መመሪያ መሠረት ከ60 ዓመት በታች የሚገኙ በኤርትራ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ ዜጎች ተመዝግብው ወደ ማሠልጠኛ እንዲገቡ፤ እንዲሁም ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ደግሞ ተገቢውን ፈቃድ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡ ያዛል።
ቢቢሲ ትግርኛ ያነጋገራቸው የአሥመራ ከተማ ነዋሪዎች ይህ የኤርትራ መንግሥት ትዕዛዝ በይፋ የተገለጸ አለመሆኑን ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚያስረዱት ይህ ትዕዛዝ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ያወቁት ከአገር ለመውጣት እና የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ቀበሌዎች በሄዱበት ወቅት በኃላፊዎች በተደረገላቸው ገለጻ ነው።
ለራሷ እና ለቤተሰቧ ደኅንነት ስትል ስሟን ያልገለጸች አንዲት በአውሮፓ ውስጥ ነዋሪ የሆነች ኤርትራዊት፤ እናት እና አባቷ ሊጠይቋት ወደምትኖርበት ሀገር ለመጓዝ የመውጫ ቪዛ ጠይቀው እናቷ ሲፈቀድላቸው የቀድሞ የኤርትራ ሠራዊት አባል የሆኑት አባቷ ቪዛ መከልከላቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግራለች።
ይህ በአካባቢ መስተዳደሮች በኩል ተግባራዊ እየሆነ ያለው የኤርትራ መንግሥት ትዕዛዝ ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም የሚመለከት በመሆኑ በነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃትን እንዳስከተለ ቢቢሲ ያናገራቸው የአገሪቱ ዜጎች ገልጸዋል።
በዋና ከተማዋ አሥመራ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች “ወቅታዊ ሁኔታን” ለማብራራት በሚል ከነዋሪዎች ጋር በተጠሩ ስብሰባዎች ላይ “ሴቶችም ጭምር” ወደ ወታደራዊ ሥልጠና ሊገቡ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ መረጃዎችን እየተሰጡ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ጠቁመዋል።
በዚህ ወታደራዊ የክተት ጥሪ ያገቡ እና ልጆች ያሏቸው ሴቶች ሳይቀሩ ወደ ነበሩባቸው የጦር ክፍሎች እንዲመለሱ የታዘዙ ሲሆን፣ በኤርትራ ከሚካሄደው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ኮብልለው ተደብቀው የሚገኙ አባላትም ያለቅጣት ወደ ክፍላቸው እንዲመለሱ እንደተወሰነ ተገልጿል።
እንዲሁም ከባድ ወንጀል ከፈጸሙት በስተቀር በተለያዩ ምክንያቶች እና ጥፋቶች በእስር ቤት የሚገኙ የሠራዊቱ አባላትም ተለቅቀው፤ በጥሪው መሠረት ወደነበሩባቸው የጦር ክፍሎች እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን በኤርትራ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ አመልክተዋል።
የኤርትራ መንግሥት ለዞን አስተዳደሮች ባስተላላፈው እና በቀበሌዎች አማካኝነት ተግባራዊ እየሆነ ያለው ይህ የክተት እና የሥልጠና ጥሪ፤ የሠራዊት አባላት ወደ ከክፍላቸው እንዲመለሱ የሚያዝ ሲሆን፣ በተለያዩ መስኮች ላይ የተሰማሩ ሌሎች የአገሪቱ ዜጎች ደግሞ ከአገር ሲወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ያዛል።
ቀደም ሲልም ኤርትራውያን ከአገር ለመውጣት ማሟላት የሚገቧቸው ነገሮች ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት እና የመንግሥት ፈቃድ የማግኘት ግዴታ የነበረባቸው ሲሆን፣ አሁን ግን የበለጠ መጥበቁን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከ70 ዓመት በታች የሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም ከ60 ዓመት በታች ሆነው ከሠራዊቱ የተሰናበቱ የቀድሞ አባላት ከአገር ለመውጣት በሚፈልጉበት ጊዜ በቅድሚያ ከአገሪቱ ሕዝባዊ ሠራዊት ጽህፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ በተላለፈው መመሪያ መሰረት ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች እንዲሁም በየትኛውም ዕድሜ ሆነው ያልወለዱ ከአገር እንዳይወጡ ተከልክለዋል።
ኤርትራ ውስጥ በርካታ ሴቶች ከኢትዮጵያ፣ ቱርክ እና አረብ ኤምሬትስ አነስተኛ ሸቀጦችን በማምጣት እና ሀገር ውስጥ በመሸጥ ስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። የሀገሪቱ መንግስት የተላለፈው አዲሱ ክልከላ ሴቶችን ማካተቱ፤ በዚህ አይነቱ አነስተኛ የንግድ ሥራ ቤተሰባቸውን በሚያስተዳድሩ ሴቶች ላይ ስጋት መፍጠሩን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ይህ መመሪያ መጥበቁን እና ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በመደበኝነት ወደተለያዩ አገራት በመጓዝ ይነግዱ የነበሩ ሴቶች፤ የአውሮፕላን ትኬት ከቆረጡ በኋላ ከአገር መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
የኤርትራ መንግሥት ለቀድሞ የሠራዊት አባላቱ ወደ ጦሩ እንዲመለሱ ዳግም ጥሪ ያወጣው እና ሌሎች ደግሞ ከአገር እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጉ የተሰማው ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ግንኙነት መቀዛቀዙ እየተነገረ ባለበት በወቅት ነው።
በዚህ ሳምንት የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ አልጀዚራ ድረ ገጽ ላይ በጻፉት አስተያየት ኤርትራ ሌላ ዙር ግጭት በቀጣናው ልትከፍት ትችላለች በሚል ከስሰው ነበር። ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ፅሁፍ ምላሽ የሰጡት የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ይህንን ክስ በማስተባበል በተቃራኒው የቀጠናው ችግሮች ምንጭ ኢትዮጵያ ናት በማለት ወቅሰዋል።
በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk