– አሜሪካ ያወጣችውን ወጭ ዩክሬን ከማዕድኗ እንድትከፍላት የድርድር ጥያቄ አቀረበች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላወጣነው ወጭ ዩክሬን ከውድ ማዕድኗ እድታካፍለን ማለታቸውን ተከትሉ የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል::
አሁን ደግሞ የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ባለስልጣን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪን ከአሜሪካ ጋር በማዕድን ውል ዙሪያ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቀዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
አማካሪው ማይክ ዋልትስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ” ወደ ጠረጴዛው በመመለስ መመካከር ያስፈልገናል ወደ ጠረጴዛው አለመምጣት እኛ ያቀረብነውን ይህንን እድል ለመጠቀም ፈቃደኛ አለመሆን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል::
አማካሪው “ለዩክሬናውያን በእውነት የማይታመን እና ታሪካዊ እድል አቅርበናል ይህ ዘላቂ የደኅንነት ዋስትና ነው” ሲሉም አክለዋል።
ይህን መሰሉን ጥያቄ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ሉአላዊነትን አሳልፎ መስጠት ነው በማለት “ግዛታችንን መሸጥ አልችልም” ማለታቸው ይታወሳል::
ይህንንም ተከትሎ ታዲያ የአሜሪካው ተወካይ ኬሎግ ወደ ዩክሬን አቅንተው ከፕሬዝዳንቱ ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም እንደ ደኅንነት እና ኢንቨስትመንት ባሉ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር ሊደረጉ ስለሚችሉ ስምምነቶች ዝርዝር ውይይት እንዳደረጉ ዜለንስኪ ተናግረዋል።
ዜለንስኪ ከኬሎግ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ ጦርነት ለማቆም ከአሜሪካ ጋር “የኢንቨስትመንት እና የደኅንነት ስምምነት” ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ታዲያ ይህ የአሜሪካ ቅፅበታዊ የአቋም ለውጥ የዩክሬን ደጋፊ የሆኑ የአውሮፓ ባለስልጣናትንም አስደንግጧል።
እናም ዩክሬን አጣብቂኝ ውስጥ ከሆነች ሩስያን የሚደግፍ ስምምነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋትን ፈጥሮባቸዋል::
በሴራን ታደሰ