በባህር ዳር ዛሬ የተሰማው የሞት ዜና መረን የወጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማሳያ ነው። የዓይን እማኞች እንዳሉት ሶስት ዩኒፎርም የሚመስል ነገር የለበሱ አንጋቾች ናቸው ዶክተር አንዷለም ከስራ ሲወጡ ጠብቀው መኪናቸው ውስጥ የገደሉዋቸው። ባልደረባቸው መኪናቸው በተመሳሳይ በጥይት ብትመታም አምልጠዋል። ይህ አስደንጋጭ ዜናው ለሕዝብ ይፋ የሆነበት አግባብም ይህንኑ መረን በወጣ ፖለቲካ ፍርሃቻ የታጀበ ይመስላል። “ ዜናው አንባቢ ይፍረደው” አይነት እንደሆነ አስተያየት የሰጡ አሉ።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽት እና የሃሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊቲ ሃኪም፣ ተመራማሪ፣ መምህር እና በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ክፍል ዳይሬክተር የነበሩት ዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ተገድለዋል። ተገደሉ የተባሉት ባልታወቁ ኃይሎች ነው። ዶክተር አንዷለም ብዙ መስራትና ህዝብን ማገለገል የሚችሉ፣ ተተኪ ማፍራት ላይ የተሰማሩ ባለሙያና መምህት ነበሩ።
|ዶ/ር አንዷለም ዳኘ ጠብቀው በተወለዱ በ37 ዓመታቸው በደረሰባቸው ድንገተኛ ሞት የተሰማንን መሪር ሃዘን እየገለፅን ለሟች ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦች እና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መፅናናትን እንመኛለን” ሲል የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ገልጿል።
“ዶ/ር አንዷለም በዩኒቨርሲቲያችን፣ ብሎም በአገራችን አሉን ከምንላቸው በቁጥር ትንሽ የዘርፉ ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞቻችን ውስጥ አንዱ የነበሩ ሲሆን ከስራ ውለው ወደቤታቸው ሲመለሱ በአጋጠማቸው ግድያ ህይወታቸውን አጥተዋል። በሐኪማችን ላይ ያጋጠመውን ግድያ እና በተደጋጋሚ በዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ተደጋጋሚ ያልተገባ መሰል ድርጊት ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በጥብቅ ያወግዛል። በየትኛውም አካል ሊሰነዘር የሚችል ይሄን አይነት መሰል ድርጊትም ለአገርም ሆነ ለወገን አጉዳይ እንጅ አንዳች የሚጨምር ነገር እንደሌለ ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባ ጉዳይ ነው” ነው ሲል ዩኒቨርስቲው ሃዘኑን አስታውቋል።
ግድያው ባልታወቁ ሰዎች መፈጸሙ ቢገለጽም ዩኒቨርስቲው ባስራጨው የሃዘን መግለጫው ተግባሩን በጥብቅ ኮንኗል። “ዶክተር አንዷለም ተተኩሶበት ተመትቶ የተገኘው መኪናው ውስጥ ነው ። አንድ ሀኪማችንም ተተኩሶበት መኪናው ሁለት፤ ሦስቴ ተመትቶታል” የጤና ኮሌጁ ሰራተኞች እማኝነታቸውን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ጥር 24/2017 ዓ.ም ምሽት 1፡30 ሰዓት ገደማ ዶክተር አንዱዓለም ዳኘ ሥራ ቆይተው ጥበብ ግዮን ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እየሄዱ ባለበት ወቅት በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እስካሁን በውል ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን እንድተናገሩ አሚኮ ጽፏል።
ሁለት ተሽከርካሪዎች ተከታትለው እየሄዱ ባለበት ወቅት አንደኛው ተሽከርካሪ ሲያመልጥ ዶክተር አንዱዓለም በነበሩበት ተሽከርካሪ ላይ በተደጋጋሚ ጥይት በመተኮስ የግድያ ወንጀል መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ድርጊቱ እንደተፈጸመ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ቦታ በመሄድ የማጣራት ሥራ እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ በሥፍራው የተገኙ የቴክኒክ ማስረጃዎችን የማንሳት እና ሌሎች ሥራዎች መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ድርጊቱን ማን ፈጸመው እንዴት ተፈጸመ የሚለውን ለመለየት ሥራ ላይ መኾኑን ነው ጅጃላፊው አመልክተዋል፡፡ ዶክተር አንዱዓለም እያሽከረከሩ በነበረበት ወቅት በተተኮሰ ጥይት መገዳላቸውንም አረጋግጠዋል፡፡ ፖሊስ አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እያደረገ መኾኑንም አስታውቋል፡፡
ፖሊስ እንዳለው እማኞችም በተመሳሳይ ዶክተር አንዷለም መኪናቸውን እያሽከርከሩ ሳለ በተጠቀሰው ቦታ ሲገልጹ፣ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል።
ለቲክቫህ እማኝነታቸውን የሰጡትና ስማቸውን የደበቁ የኮሌጁ ባልደረቦች ስለገዳዮቹ ለጊዜው በውል የታወቀ ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ከዶ/ር አንዷለም በፊት በራሱ ተሽከርካሪ ሲጓዝ በነበረ ሌላ ሀኪም ላይ በተመሳሳይ ለመግደል ጥይት ቢተኮስበትም ሊያመልጥ ችሏል።
እነዚህ ምስክሮች እንዳሉት ግድያው ሲፈጸም ‘ሦስት የሚተኩሱ ሰዎች እንደነበሩ አመልክተዋል። መለየት ባይችሉም “ዩኒፎርም ነገር” ሲሉ የገለጹትን ለብሰው ነበር።
በጥበበ ግዮን ግቢ ህክምና ጤና ሳይንስ ኢንተርን ሀኪሞች በበኩላቸው፣ “ ዶክተር አንዷለም ከከተማ ከሥራ ውሎ ሲመለስ ምሽት ላይ ነው የተመታው። ግን ማን እንደመታው የተረጋገጠ ነገር የለም ” ሲሉ ነግረውናል።
“ አስከሬኑም ለፓሊስ ተደውሎ ነው ማታ የተነሳው ” ያሉት ኢንተርን ሀኪሞቹ፣ “ አሁን ሀኪሞቹም፣ ነዋሪዎችም ሁሉም የባሕር ዳር ዩኑቨርሲቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች ሀዘኑን እየተካፈልን ነው ያለነው ” ብለዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶክተር መንገሻ ከሰዓታት በፊት በሰጡን ቃል “ አስከሬን ይዘን ከቤት ወደ ቤተክርስቲያን እየወጣን ነው ” ብለዋል።
ስለገዳዮቹ ማንነት የታወቀ ነገር እንዳለ የጠየቅነው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጸጥታ ክፍል በሰጠን ምላሽ፣ “ ግድያው ከግቢ ውጪ ስለተፈጠረ ምንም ያወቅነው ነገር የለም ” ብሏል።
“ ያወቅነው መረጃ የለንም። እኛም እንደማንኛውም ሰው መሞቱን ብቻ ነው የሰማነው ” ሲል አክሏል።
የሚመለከታቸውን የከተማውን የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ የምናቀርብ ይሆናል።
ዶክተር አንዷለም ዳኘ የዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስፔሻሊስት፤ የጉበት፣ የቆሽት፣ የሀሞት ጠጠር መስመር ሰብ ስፐረሻሊስት ሀኪም፣ እንዲሁም የልጆች አባት ነበሩ። የሚያውቋቸው ደግ፣ ሩህሩህ፣ ለሁሉም ምሳሌ የሚሆኑ፣ መልካም ሰው እንደነበሩ ተናግረዋል። ኮሌጁ ጉዳቱ ለአገርና ለህዝብ እንደሆነም አመልክተዋል።