ሰሞኑን ከትግራይ የሚወጡ ዜናዎች መላው የኢትዮጵያ፣ በተለይም የትግራይ ህዝብ አስጨንቋል። 50ኛ ዓመቱን ለሁለት ተከፍሎ ለማክበር መግለጫ እየተሰጠለት ያለው ትህነግ፣ ጎን ለጎን ለትግራይ ህዝብ ምን ሰራ? እየተባለም ነው። “ጦርነት በቃን። የመኖር ዕድል ስጡን” የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡም በርክተዋል። ሞንጆሪኖና ጌታቸው ረዳ በጦርነት ስጋት የተለያየ መልክ ይዘው ብቅ ብለዋል። ተፈናቃዮች መከራ ላይ ናቸው። አስመራ በጎዳና ላይ ጭፈራ ደብረጽዮን ተዘፍኖላቸዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ተወግዘዋል።
ምንም ይባል ምን፣ በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የትህነግ ፍንካች ጦርነት ለማድረግ ዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ማስተባበል አይቻልም። ከሻዕቢያ ጋር ገጥሞ፣ አማራ ክልል በተለይም ጎጃም ካለው ኃይል ጋር ተናቦ እየሰራ ስለመሆኑ ማስተባበል እንደማይቻል ሰፊ ማስረጃና መረጃ አቅርበው የሚከራከሩ ብዙ ናቸው። የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅቶችና እንቅስቃሴውን የሚታዘቡ ወገኖች በየቀኑ ምስክር እየሆኑ ነው። በድሮን በየዕለቱ በሚሰበሰብ መረጃ መቀመጫውን ሽሬ ያደረገ የጦርነት ዝግጅት፣ ወደ ኤርትራ የሚዘለቅ የጥርጊያ መንገድ ግንባታ፣ የምሽግ ቁፋሮ፣ የእህልና የገንዘብ መዋጮ እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል። የሰራዊት ንቅናቄም አለ።
ይህን የሚያውቁ የትግራይ ተወላጆች በትግራም በአዲስ አበባም ” ጦርነት በቃን። እንኑርበት” የሚል የሰላም ድምጽ ለእነ ደብረጽዮን ቡድን አስተላልፈዋል። ከሻዕቢያ ኃይሎች ጋር ለገጠሙት ሁሉ “እረፉ” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ቀደም ሲል ትህነግን በከፍተኛ ደረጃ ሲያወድሱና “ግፋ በለው. ጦርነት ባህልህ ነው ” በማለት ውጭ ተቀምጠው ህዝቡን ወደ ጦርነት ሲነዱ የነበሩት የሚዲያው ክንፎችም ናቸው። እነዚሁ የሚታወቁት ሚዲያዎች ” የጦርነት ሲግናል፣ አንቴና፣ ከስህተቱ የማይማር …” እያሉ ሲምሉበት የነበረውን ድርጅትና አመራሩን እያበሻቀጡ ይገኛሉ። የሰራዊቱን አመራሮችም ” ባህላዊ” በማለት ወቅትን የማይመረመሩ በማለት እየዘለፉ ነው።
በትግራይ፣ በመላው አዲስ አበባና በውጭ አገር ጦርነት እንዳይጀመር አብዝተው የሚጮሁ፣ በተመሳሳይ የተፈናቀሉ ዜጎች ለጊዜው ወደ ነበሩበት ቀዬቸው እንዲመለሱና ወደፊት በጥናት ላይ የተመሰረተ ህዝብ የሚያጸናው ፖለቲካዊ እንዲወሰንም ደጋግመው እየጠየቁ ነው። ተፈናቃዮችን የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እንዲቆም የሚነሳው ጥያቄም ከቀድሞው ይልቅ እየጎላ ነው።
ወታደራዊ ክንፉ አቶ ጌታቸው ስልጣናቸውን ለእነ ደብረጽዮን ቡድን እንዲያስረክብ ማስታወቁን ተከትሎ የተነሳው የህዝብ ተቃውሞ ማየሉን ተከትሎ ” በትግራይ በማንኛውም መመዘኛ ጦርነት የሚጋብዝ አንዳች ሁኔታ የለም ” ሲሉ በሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ትህነግ ትግራይ መግለጫ ያሰራጨው። በተመሳሳይ ” በአሁኑ ወቅት በትግራይ በማንኛውም ደቂቃ በሆነ ሰው በሚፈጠር ስህተት ለግጭት የሚዳርግ ሁኔታ ሰፍቷል ” በማለት አቶ ጌታቸው ረዳ ይፋ ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ተንተርሶ ለትግራይ ህዝብ በተለይም ለትግራይ ሊህቃን ” አስቡበት” የሚል ይዘት ያለው መልዕክት እና ምክር ማስተላለፋቸው ይታወሳል።
ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው ” ህዝቡ ያለፈው አልበቃ ብሎት የትናንት ቁስሉ ሳይሽር አሁንም በሽብር እና በጦርነት ወሬ ስሜት ወስጥ ይገኛል ” ሲሉ እንደ መንግስት ካላቸው መረጃና ማስረጃ ተነስተው የዘረዘሯቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲያስቡበት አሳስበዋል።
በፓለቲካ ፣ በንግድ ፣ ፀጥታ ፣ አካዳሚ እና ሚድያ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች ለተሰማሩ የትግራይ ልሂቃን ወገኖች ባስተላለፉት መልዕክት ” የትግራይ ህዝብ እስከ ዛሬ የተሰቃየው የከፈለው ዋጋ ይብቃው ፤ ልዩነትን በመነጋገር እና በውይይት የመፍታት ባህልንና ልምድ ታጠቁ ” ብለዋል።
50ኛ ዓመት ልደቱን በመኖርና አለመኖር መካከል ሆኖ፣ ለሁለት ተቧድኖ፣ አንድ እግሩን ከሻዕቢያ፣ አንድ እግሩን ከመነግስት ጋር በማድረግ ደፋ ቀና እያለ ያለው ትህነግ በተለያዩ ወቅቶች ያካሄዳቸውን ጦርነቶች የህልውና እንደሆኑ በመጥቀስ አብይ አህመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ሊወርፍ ሞክሯል።
ልሂቃኑ ከፌደራል መንግስት እና ሌሎች ሃይሎች ያላቸው ልዩነት በአገሪቱ ህገ-መንግስት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግባባት ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። የውስጥ ችግራቸውንም ሆነ ማናቸውንም ጉዳዮች በውይይት ለመፍታት እንዲቻል ደጋግመው ጥሪ አሰምተዋል።
በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በሚመራው ትህነግ የፓለቲካዊ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ምላሽ ሰጥተዋል። ወይዘሮዋ ምላሹን የሰጡት 50ኛው ዓመት የትግራይ ህዝብ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ መሆኑም ተመልክቷል።
” ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ህልውና የነበረው ተሳትፎ አስመልክተው የተጠቀሙበት አገላለፅ ልክ ነው። የትግራይ ህዝብ ሚና ባሉት ደረጃ ነው መገለፅ ያለበት ብለን እናምናለን። የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ነፃነት ፣ ልማት እና ዴሞክራሲ የከፈለው ዋጋ እጅግ ውድ ነው። እሳቸው በፅሁፋዊ መልእክታቸው የተጠቀሙበት አገላለፅ የምንጋራው እና ክብር የምንሰጠው ነው ” ነው ሲሉ ወይዘሮ ፈትለወርቅ አመልክተዋል።
“የመልእክታቸው አንኳር ነጥብ ህዝቡ ጦርነት ስለማያስፈልገው የትግራይ መሪዎች እና ልሂቃን ልብ ግዙ ተመካከሩ የሚል ነው” ያሉት የቀድሞዋ የንግድ ሚኒስትር ወይሰሮ ፈትለወርቅ የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ህዝብ ጦርነት ገልጸዋል። አክለውም በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብም ጦርነት አያስፈልገውም ብለዋል።
ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደማያስፈልገው ካወሱ በሁዋላ “ይሁን እንጂ የትግራይ ህዝብ ባለፉት 100 ዓመታት ከማእከላዊ መንግስቱ ጋር ያደረጋቸው ጦርነቶች ከመሬት ተነስቶ ያደረጋቸው፣ ተንኳሽ እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ በደብዳቤው የቀረበ አገላለፅ ልክ ነው ብለን አንወስድም ” ሲሉ ተናግረዋል። የተዋጋውም ለመብቱ እንደሆነ አመልክተዋል። ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለየ የትግራይ ህዝብ መቶ ዓመት እንዲዋጋ ያደረገውን በደል አልዘረዘሩም።
” የትግራይ ህዝብ ላለፉት 100 ዓመታት እና ከዛ በላይ የተዋጋው የሚወሩትን ፣ መብቱን የሚነፍጉትን እና ድምፁን የሚያፍኑትን ለመከላከል ሲባል መሆኑ ልብ ማለት ይገባል። ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ጦረኛ እና ተንኳሽ በሚመስል መልኩ የቀረበ አገላለፅ ልክ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ትናንት ፣ ዛሬ ይሁን ነገ አይገዛም አይምበረከክም። ልግዛህ ላምበረክክህ ለሚለው ወራሪ መልሱ እምቢ ነው። ከዚህ ውጭ ጦርነት ጀማሪ ሆኖ አያውቅም ፤ ማንንም ሄዶ አይወርም ልግዛህ አይልም ፤ ስለሆነም ጦርነት ጀማሪ በሚመስል የቀረበው አገላለፅ ልክ አይደለም ” ሲሉ ተደምጥዋል።
የትግራይም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ማንንም እንደማይወጉ የሚጠቁሙ፣ በትግራይ ህዝብን እየማገደ ያለው ትህነግ መሆኑን በመጠቀስ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ለተናገሩት ምልሻ ሰጥተዋል። የቀድሞ ደጋፊዎቹ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ትህነግ ህዝቡን እንዳስጨረሰ ደጋግመው እንደሚገልጹ የሚጠቁሙ፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ህዝብንና ትህነግን ለያይተው ሊያዩ እንደሚገባ፣ ህዝብ አሁን ላይ ትህነግን የሚያበትን አግባብ እንዲረዱ መክረዋል። ትህነግ ከከልሉ አልፎ አማራና አፋርን ወሮ ያደረሰውን ጉዳት በመዘርዘር “ወረራ ማለት ምን ማለት ነው” ሲሉ እንዲህ ያለው ሽምጠጣ የትም እንደማያደርስ ተናግረዋል። ” እኛ እንወረራለን እንጂ አንወርም ፤ ጦርነት ይከፈትብናል እንጂ በማንኛውም ህዝብ ላይ ጦርነት አንከፍትም ” ላሉት ሻዕቢያን በግልጽ ጠርተው ለምን እንዳላወገዙ ሌላ ጊዜ ምክንያቱን እንዲያስረዱ ጠይቀዋል።
” ማንኛውም የትግራይ ፓለቲካዊ ፓርቲ ፣ ስቪክ ማህበር እና ህዝቡ ከማንኛውም ህዝብ በላይ በጦርነት የወደመ የተጠቃ ፣ ጦርነት እጅግ አፍራሽ መሆኑ ስለሚያውቅ አሁንም የጦርነት ፍላጎት የለውም ” ሲሉ ህዝቡ ያሰማውን የጦርነት ይብቃ ጥያቂ የደገሙት ወይዘሮዋ፣ ” በትግራይ በኩል ለጦርነት የሚጋብዝ አንድም ምክንያት የለም ። እርግጥ ነው በትህነግ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ልዩነት እና መሳሳብ አለ። ይህንንም በሰለጠነ የፓለቲካ አግባብ ይፈታ እንደሆነ እንጂ ወደ ጦርነት የሚመራ ምክንያት ሊሆን አይችልም ” ሲሉ ጦርነት እንደማይኖር አመልክተዋል። እሳቸው ይህን ባሉበት ተመሳሳይ ቀን ሻዕቢያ በውጪ ለሚኖሩ ኤርትራውያን በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ ባዘጋጀው ጭፈራ ዶክተር ደብረጽዮንን የሚያሞግስ፣ አቶ ጌታቸውን የሚኮንን ” ወግድ በለው” የሚል የመከፋፈያ ዘፈን የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ሆኗል።
” ያለንን የፓለቲካ ልዩነት በውይይት እና በሰለጠነ የፓለቲካ አግባብ እንፈታዋለን እንጂ ወደ ጦርነት የሚያስገባን አይሆንም ” ማለታቸውን አብዛኞች በበጎ አይተው ምላሽ ሰጥተዋል።
” ከፌደራል መንግስት ጋር የሚያገናኘን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ነው። ስምምነቱ ማእከል በማድረግ የጎደለን ነገር በውይይት ለመሙላት ነው ‘እንወያይ ‘ የሚል ጥሪ እያቀረብን ያለነው። እንወያይ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈፃሚ ይሁን ፣ ወራሪዎች በሃይል ከያዙት ግዛታችን ይውጡ ፣ የግዛት አንደነታችን ይከበር ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው ይመለሱ ፣ የሁለትዮሽ ፓለቲካዊ ውይይት ይጀመር ወደ መደበኛው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የምንመለስበት ሁኔታ ይፍጠን ብሎ መጠየቅ የጦርነት መንስኤ ሊሆን አይችልም ” ብለዋል።
” የ2013 ዓ.ም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ሳምታት ቀደም ብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ የአሁኑ አይነት ተመሳሳይ የፅሁፍ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር። ያኔም ወደ ትግራይ ማሰክ እንጂ የጥይት ቁምቡላ አንልክም ተብሎ ነበር። ቅኔ ነው የነበረው። አሁንም በውጭ ሲታይ ለስላሳ እና ጣፋጭ ውስጡ ሲታይ ግን ተጠንቀቁ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ሁኔታ ነው ያለው የሚል እንድምታ ያለው ደብዳቤ ነው የተሰራጨው ” በማለት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ተናግረዋል።
” ደብዳቤው ሆን ተብሎ ህዝብ ለማሸበር የተደረገ ነው። ይህ በትግራይ ህዝብ ላይ እየቀጠለ ያለውን በደል አካል አድርገን ነው የምንቆጥረው። የትግራይ ህዝብ ማስፈራራት አይገባም። አሁንም ‘ መጣሁብህ ገደልኩህ ‘ ማለት ለትግራይ ህዝብ ተገቢ አይደለም። የትግራይ ህዝብ አሁን የሚያስፈልገው የበደል ካሳ ፣ ሰላም ፣ ልማት እና ውይይት ነው በመሪዎች መካከል የተፈጠረው የፓለቲካ ልዩነት በሰለጠነ ውይይት መፍታት ያስፈልጋል ” ብለዋል።
” በአሁኑ ወቅት ትህነግም ሆነ የትግራይ ህዝብ የጦርነት ፍላጎት የላቸውም። በመላው ትግራይ ጦርነት የሚጋብዝ እንዳች ምልክት የለም። መብታችን ፣ ማንነታችን ይከበርልን ፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ሁሉም ነገር ይፈፀም የሚል ግን ጥያቄያችን አስኪመለስ ድረስ የምናቆመው አይደለም ይህ ዓይነት ጥያቄ በፍፁም የጦርነት መንስኤ ሊሆን አይችልም ” ብለዋል። ” በትግራይ ለጦርነት የሚጋብዝን አንዳች ነገር የለም ” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ንግግራቸው ይህዝቡን አቋም ካዩ በሁዋላ የእን ደብረጽዮን ቡድን ጦርነት ቢጀምር ሊሳካለት እንደማይችል ከመረዳት ወይም “ጦነት አንፈልግም” በሚል የምሬት ድምጽ ላሰሙት የትግራይ ተወላጆች ማበበያና ማዘናጊያ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩ አሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት 50ኛው ዓመት የትግራይ ህዝብ ትግል የጀመረበት የካቲት 11 በጊዚያዊ አስተዳደሩ ለማክበር እየተደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት በማስመልከት የክልሉ ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ መግለጫ ሰጥተው ነበር። ቲክሻህ ወደ አማርና መልሶ ያሰራጨው ዜና እንደሚያስረዳው፣ አቶ ጌታቸው ከወይዘሮ ፈትለወርቅ በተለየ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው በዚሁ ወቅት በትህነግ አመራሮች መካከላል ባለው ክፍፍል የግጭት ስጋት ስለመኖሩ አስታውቀዋል። ” በአሁኑ ወቅት በትግራይ በማንኛውም ደቂቃ በሆነ ሰው በሚፈጠር ስህተት ለግጭት የሚዳርግ ሁኔታ ሰፍቷል ” በማለት ነው ስጋታቸውን መጠን አጉልቶ የሚያሳይ ንግግር አድርገዋል።
ትግራይ ክልል ከአስከፊው ጦርነት ገና በቅጡ ያላገገመ ሲሆን አሁን ደግሞ ህዝብን በከፍተኛ ስጋት ላይ በጣለ የአመራሮች ክፍፍል እየታመሰ መሆኑም ተለምክቷል።