የዶ/ር ወዳጄነህ መሐረነ መልዕክት።”ሀኪሙን አትግደሉ!
(Whoever you are!)”
አንድ የህክምና ዶክተር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኖ ሳለ ባብዛኛው ሰቃይ የሚባል የደረጃ ተማሪ ስለሆነ እውቀትን ለመሰብሰብ፣ አንደኝነቱን ለማስጠበቅ በትጋት ይማራል፣ በር ዘግቶ ያጠናል።
ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ኮመን ኮርሶችን ካለፈ በኋላ ለማጥናት እጅግ ጊዜ የሚፈጁ እንደ አናቶሚ (Anatomy)፣ ፊዚዬሎጂ (Physiology)፣ ባዬኬሚስትሪ (Biochemistry)፣ ፋርማኮሎጂ (Pharmacology)፣ ፓቶሎጂ (Pathology) ማይክሮባዬሎጂ (Microbiology) የመሳሰሉ ኮርሶችን አንገቱን ደፍቶ ይማራል፣ ሌት ተቀን ያጠናል።
በሌሎች ካምፓሶች ያሉ ጓደኞቹ ዘና ፈታ ሲሉ የህክምና ተማሪው ግን ጊዜ የለውም። ገርል ፍሬንድ፣ የዳንስ ምሽት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት ብሎ ነገር አያውቅም።
እነዚህን ትምህርቶች በብዙ ትጋት ከጨረሰ በኋላ ክሊኒካል አመታት ይጠብቁታል ። የውስጥ ደዌ ህክምና፣ የቀዶ ጥገና፣ የማህፀንና ፅንስ፣ የህፃናት ህክምና፣ የአእምሮ ህክምና፣ የቆዳ የአይን ወ.ዘ.ተ የህክምና አይነቶችን ይማራል። ህሙማንንም ይጎበኛል። ከዚያም ኢንተርን ዶክተር ይሆናል።
ኢንተርን ሀኪም ሆኖ ሌት ተቀን ነው ስራው። ተረኛ ሆኖ አድሮ ጠዋት ወደ ቤቱ አይሄድም። ደክሞት፣ ርቦት ስራውን ይቀጥላል። ጊዜ መምጣቱ አይቀርምና የምርቃቱ ቀን ሲደርስ የህክምና ዶክተር ሆኖ ይመረቃል።
ሀኪሙ ገጠር ተመድቦ እጅግ ትንሽ በሚባል ደሞዝ በቀን ከ 30 እስከ 40 የሚደርሱ ታማሚዎችን ያክማል። አሁንም ለመዝናናት ጊዜ የለውም። የቀንም የሌሊትም ተረኛ ሀኪም እሱው ነው።
የገጠር አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላ ስፔሻሊስት ለመሆን ተመልሶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ይመጣል። እረፍት የሌለባቸው አራት አመታትን ያሳልፋ። እንደዚህ ነው ስፔሻሊስት ሀኪም የሚሆነው። ሰብ ስፔሻሊስት ለመሆን ደግሞ ተጨማሪ አመታት በሀገር ውስጥ ወይም በውጪ ሀገር መስራት ይኖርበታል።
በዚህ ሁሉ ዶክተሩ ለመዝናናት ፋታ የለውም። ለወሬ፣ ለአሉባልታ፣ ለአላስፈላጊ ንትርክ ጊዜ የለውም። ትኩረቱ ህመምተኞቹ ናቸው። እርካታው የእነርሱ መዳን ነው።
ሀኪም እርስ በርሱ አይወዳደርም፣ ምቀኝነት አያውቅም። አንዱ ዶክተር ወደ ሌላው ዶክተር “ለተሻለ ህክምና ” ብሎ ታማሚውን በሪፈራል ይልካል። በተለየ ትጋት ለታማሚዎ ይደክማል።
ዶክተር አንዷለም ዳኜ ስፔሻሊስት ብቻ አልነበረም። ሰብ ስፔሻሊስት ነበር። በእርሱ ደረጃ ያሉ ሀኪሞች ኢትዬጵያ ውስጥ ጥቂት ናቸው። በብዙ ወረፋ ነው የሚገኙት። ዶ/ር አንዷለም ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ ቢሆን ኖሮ በአመት ከ 200 እስከ 300 ሺ ዶላር ይከፈለው ነበር። በዚያ እንዳሉ ጓደኞቻችን ትልቅ ቤት ገዝቶ የአሜሪካንን ከፍ ከፍ ያሉ መኪኖች በሩ ላይ ይደረድር ነበር። እርሱ ግን ህዝቤን፣ ወገኔን ባገለግል ይሻላል ብሎ በሀገሩ መኖርን መረጠ፣ በባህር ዳር ከተመ። የድሆች ፈጥኖ ደራሽ፣ የሚስኪኖች መድሃኒታቸው ሆነ።
ምን አይነት የደነቆረ አእምሮ ነው የእርሱን ሞት የሚያቅደው?
ምን አይነት የአውሬ አይን ነው እርሱን በክፉ የሚመለከተው ? ምን አይነት የተረገመ ጣት ነው በእርሱ ላይ ቃታ የሚስበው? ምን አይነት ክፏ አጋንንት ነው በእርሱ ሞት ሀሴት የሚያደርገው? በተወደደ ሃኪም ሞት ምን ትርፍ ይገኛል? የልጆች አባትን መግደል እንዴት ድል ይሆናል?
እንዴት ነው ህዝብን አያገለገሉ ያሉ የህክምና ዶክተሮች ለግድያ የሚታጩት ? ለምንድን ነው የህክምና ባለሙያዎች በፍርሃት የሚኖሩት? እነርሱኮ የቆሰለ ሰው ሲመጣ የመንግስት ወታደር ይሁን፣ የፋኖ ታጣቂ ይሁን፣ የሸኔ ታጣቂ ይሁን ያለ ልዩነት ያክማሉ፣ ለመዳኑ ሌት ተቀን ይለፉለታል።
እባካችሁ ሀኪሙን አትግደሉት ! የጤና ባለሙያውን አታስጨንቁ ! መምህሩ ላይ አትተኩሱ ! ይልቁን መንግስትም ሆነ በተያየ ቦታ ያሉ ታጣቂዎች ለባለሙያው ጥበቃ ማድረግ ነው ያለባችሁ። ያልታጠቁ ሰዎችን መግደል የትም ሀገር ጀግንነት ሆኖ አያውቅም! ይህ ፅሁፍ የሚያስቆጣው ካለ ገዳይነቱን መሰከረ!
እግዚአብሔር ኢትዬጵያን ያስባት። የዶክተሩንም ልጆች ፈጣሪ ያሳድግለት።
ማንም ሁኑ ማን (whoever you are) ሀኪሙን አትግደሉ!