“እኛ በመላው ዓለም የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ የተለያዩ የሲቪክ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ወክለን በጊዜያዊ ኮሚቴ (ሕብረት) ሥር የተሰባሰቡን ሀገር ወዳድ ዜጎች ነን” ይላል የአዲሱ የትግል አቅጣጫ ጥሪ ደብዳቤ፡፡
ደብዳቤው ብልጽናን በከፋፋይነት፣ በኃይማኖት ጸርነት፣ “የተቀደሰ ኃይማኖታችንን” በማለት ኦርቶዶክስን ከስልምና ጋር በማጋጨት፣የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ በመጣልና በመሳሰሉት ጉዳዮች ይከስና “ኢትዮጵያን ከምን ጊዜውም በላይ የሚያሰጋትን ወቅታዊ ፈተና ለመመከት፣ የኛን የተበታተነ ጥረታችንን አንድ አድርገን በማሰባሰብ፣ በሚደረገው ወሳኝ ውይይት ላይ እንድትሳተፉ ጋብዘንዎታል” ሲል “ህብረት” የተሰኘ ድርጅት መመስረቱን ይጠቅሳል፡፡ ጥሪውም በህብረቱ ስም መሆኑን ያመለክታል፡፡
ህብረቱን የመሰረቱት የኢትዮጵያ አሜሪካን ሲቪክ ካውንስል፣ኢትዮጵያዊነት፣ የአሜሪካ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴና ኢትዮጵያን እናድን ድርጅቶች ናቸው፡፡ ደብዳቤው የመስራች ድርጅቶችን ስም ዘርዝሮ “በአንድነት ቆመናል” ብሏል፡፡አክሎም “ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን የህልውና ስጋቶች ለመፍታት እና ተጨማሪ ቀውሶችን ለመከላከል የተባበረ ግንባር (ኅብረት) ለመመስረት ቆርጠን ተነስተናል” ይላል፡፡
ህብረቱ ወደ ካውንስል እንደሚቀየር በቨርቹዋል ስብሰባው ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ስብሰባው የተካሄደው ባለፈው ቅዳሜ ነበር፡፡
የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ግብ አስቀምጦ እንደሚሰራ ያስታወቀው ህብረቱ፣ ከተጠቀሱት አራት ድርጅቶች ሁለት ሁለት ተወካዮች ያሉበት ስምንት የስራ አስፈጻሚ ሰይሟል፡፡
ሚናቸው በግልጽ ባይቀመጥም አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ አቶ ክፍሉ ታደሰ፣ የቪኦኤው አቶ ንጉሴ አክሊሉ፣አቶ አበበ ገላው፣በጀርመን የሚኖሩት የቀድስማዊ ኃይለስላሴ ልጅና ሌሎችም የተካተቱበት ግብረኃይል መቋቋሙን ስብሰባውን ተጋብዘው የተሳተፉ ነግረውናል፡፡
አራቱ ቡድኖች የየራሳቸውን አባላት በመያዝ ህብረቱ ባዘጋጀው የጋራ መርህና ዓላማ መሰረት የየራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ታውቋል፡፡
ህብረቱ በጠራው የቭወርቿል ስብሰባ ላይ ከስቴት ዲፓርትመንት ሰዎች ጋር መነጋገራቸውንና ተጠናክራችሁ አንድ ሆናችሁ መምጣታችሁ አግባብ ነው መባላቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ከፋኖ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ወጥ አመራር አለመኖሩ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ እየገለሸ ባለበት፣ የውጭ አካላትም በተመሳሳይ በፋኖ አደረጃጀት ላይ አሳብ ስለሚሰጡ ህብረቱ ይህን ቀዳዳ ደፍኖ ከምንግስት ጋር ለመደራደር ያመቸው ዘንድ ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሆነ እኚሁ ተሳታፊ ነግረውናል፡፡
“ችግሩ” አሉ መረጃውን ያካፈሉን ” ችግሩ ሌሎች አሊያንሶችም እየተፈጠሩ ነው፡፡ እሽቅድምድም ይምስላል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አገር ቤት ያለው የፋኖዎች አደረጃጀት አላውቃቸውም ሊል ይችላል የሚል ግምት አለኝ” ሲሉ የተለመደው መከፋፈል እንደሚከተል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
አሁን ላይ በጋምቤላ እርሻ ስራ ላይ እንደተሰማሩ የሚነገርላቸው አቶ ኦባንግ ሜቶ አሁን ተካተቱበት በተባለው አዲስ ህብረት ከነ ድርጅታቸው ወይም በግል ተሳታፊ ስለመሆናቸው አልታወቀም፡፡ አቶ ኦባንግ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖሩ ለማግኘት ቢሞከርም አልተቻለም፡፡
በሌላ ተመሳሳይ የጥምረት ዜና አቶ ጃዋር መሀመድ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ እና አቶ አሉላ ሰለሞን የተካተቱበት ጥምረት መፈጠሩ ተሰምቷል፡፡ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት አቶ ልደቱ አያሌው ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የወሰኑት ከዚህ ጥምረት ሚሽን ወስደው እንደሆነ የመንግስት ሰዎች መረጃው ደርሷቸዋል፡፡
የማሪካ የአፍሪካ ጉዳዮችን ከሚወስኑት ውስጥ አብዛኞቹ ከምንግስት ጋር ግብብ ስላላቸው በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውም ተሰምቷል፡፡ ይህ ጥምረት ከጀርባው ሆኖ የሚመራው ሻእቢያ በመሆኑ በአሜሪካን ዘንዳ አልተወደደም፡፡
ሻእቢያ ከኢራን ጋር ሆኖ በአሜሪካንና በእስራኤል ጥቅም ላይ ተጻራሪ ሚና ስለሚጫወት፣ ይህም በእስራኤል ሚዲያዎች መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
የአፍሪካ ጉዳዮች ሰክሬታሪ ይሆናሉ ተብለው አሁን ካልው ግሩፕ ውስጥ የሚጠበቁት ፒተር ፋም በምስራቅ አፍሪቃ ፖለቲካ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው፣ በዚሁ ዴስክ እንደ አምባሳደር ቲቦርናጌ፣ ማይክል ሮበን፣የመሳሰሉ ስላሉበት አሜሪካ በምስራቅ አፍሪቃ የምትከተለው አካሄድ ለኢትዮጵያ መንግስት ስጋት እንደማይሆን ዜናውን ያካፈሉን ገልጸዋል፡፡
የሚዲያ መሪዎችና አክቲቪስቶች እየተቀራመቱት፣ በውስጡ መከፋፈልና በሚከተለው ያልጠራ የፖለቲካ ጉዞ መደነቃቀፍ ውስጥ ያለው ፋኖ ይህን ጥምረትም ሆነ ሌሎቹን አስመልክቶ ጥርት ያለ መረጃ ይህ እስከተጻፈ ድረስ አልሰጠም፡፡ ፋኖ የተለያዩ አደረጃጀቶች እንዳሉት ስለሚታወቅ አሰላለፉን አስመልክቶ ለጊዜው ምንም ማለት እንደማይቻል ጉዳዩን የሚከታተሉ ይናገራሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጃዋር መሀመድ እስር ላይ በነበረበት ወቅት በመዐዛ መሀመድ መልእክት አመላላሽነት የተጀመረው የትህነግና የጃዋር ጥምረት አሁን ላይ ከላይ በተገለሸው መሰረት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ እንቅስቃሴው አሁን ላይ አማራና ትግሬን በማግባባት አዲስ የትግል አቅጣጫ ለመመስረት ያለመ ነው፡፡ ትግሬና አማራን አስማምቶ አዲስ ትግል ለመጀመር የተያዘው እቅድ የወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራን ጉዳይ አስመልክቶ ግልጽ ያደረገው ነገር የለም፡፡
ቀደም ሲል የሻዕቢያ ሰላይ የነበረውና በዱባይ የሚኖረው የመረጃ አጋራችን ቀደም ሲል ወልቃይት ጠገዴ ላይ ሻዕቢያ ልዩ ፍላጎት እንዳለው አስታውቆ ነበር፡፡ ይኸው ሰላይ እንዳለው በጎጃም ከሚንቀሳቀሱት ፋኖዎች መካከል አንዱና ዋና የሚባለው ይህን አስመልክቶ ከሻዕቢያ ጋር ስምምነት ማድረጉን ቀደም ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ለመንግስት የድርድር ሰነድ ያሰገቡ መኖራቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡