47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ስልጣን እንደመጡ ሊያደርጓቸው ካቀዷቸውና ለደጋፊዎቻቸው ቃል ከገቡላቸው ጉዳዮች አንዱ ከቻይና፣ ሜክሲኮ፣ ካናዳ እንዲሁም ከአውሮፓ በሚመጡ ምርቶች ላይ ታሪፍ በመጣል የአገር ውስጥ አምራቾችን ማጠናከር ነበር።
ፕሬዚዳንቱ በገቡላቸው ቃል መሠረትም ሰሞኑን በቻይና የተለያዩ ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣላቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢም በሜክሲኮ እና በካናዳ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ መጣላቸውን አስታውቀው ነበር።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ እና ሜክሲኮ መሪዎች ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ታሪፍ መጣሉን ለ30 ቀናት ለማራዘም መስማማታቸው ተገልጿል።
ትራምፕ ታሪፉን የሚጥሉት ለአሜሪካ ኢንዱስትሪዎቸ ጥበቃ ለማድረግ እንደሆነ ቢገልጹም በርካታ የኢኮኖሚ ባላሙያዎች ግን ለአሜሪካዊያን የዋጋ ንረት ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህ ታሪፍ ተፈጻሚነት የሚኖረው ከሆነ የሚከተሉት እቃዎች ዋጋቸው ሊጨምር ይችላል ነው የተባለው።
🚘 መኪኖች
ትራምፕ በውሳኔያቸው ከጸኑ በአሜሪካ የመኪኖች ዋጋ ቢያንስ በ3 ሺሕ ዶላር ይጨምራል ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ የአሜሪካ መኪናዎች የሚሰሩባቸው መለዋወጫዎችን ከካናዳ እና ከሜክሲኮ ስለሚያስገቡ።
ስለሆነም እነዚህን የመኪና መለዋወጫዎች ለማስገባት ብዙ ታክስ መክፈል ስለሚኖርባቸው የመኪኖቹ ዋጋ መጨመሩ አይቀሬ ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ከሜክሲኮ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ጀርመን እና ደቡብ ኮሪያ በሚሊየን የሚቆጠሩ መኪኖችን ስለምታስገባ ውድ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።
🏘 ቤት
አሜሪካ ለቤት መስርያ የሚሆን ጣውላና የእንጨት ግብዓቶች በከፍተኛ መጠን ከካናዳ የምታስገባ ሲሆን ታሪፉ የነዚህን የመስርያ ቁሳቁስ ዋጋ በእጅጉ እንዲጨምር ያደርጋል። ይህም የቤት ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት እንደሚሆን ይገመታል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከሚያስፈልጋት በላይ ጣውላ አላት ቢሉም የአሜሪካ ብሔራዊ ቤት ሰሪዎች ማህበር ግን የቤት መስርያ ቁሳቁስ ከታሪፉ ነጻ መሆን አለባቸው ብለዋል። አለበለዚያ የአሜሪካዊያን ቤት የመግዛት አቅም ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አሳስበዋል።
⛽️ ነዳጅ
ካናዳ የአሜሪካ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ አቅራቢ ሀገር ናት። ስለሆነም ካናዳ ለአሜሪካ አጸፋዊ ምላሽ ብትሰጥ በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሚያሳይ ይሆናል። በተለይ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ዜጎቻቸው በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች እንዲጠቀሙ የሚያበረታቱ በመሆናቸው ችግሩ ቀላል አይሆንም ነው የተባለው።
🥑 አቮካዶ
ሜክሲኮ ባላት ምቹ የአየር ንብረት ምክንያት አቮካዶን በብዛት ታመርታለች። 90 በመቶ በአሜሪካ ገበያ ላይ የሚቀርብ አቮካዶ ደግሞ ከሜክሲኮ የሚላክ ነው። ስለሆነም ትራምፕ በሜክሲኮ ላይ ታሪፍ ከጣሉ ለአሜሪካዊያን አቮካዶ ይወደድባቸዋል ማለት ነው።
🍻 የአልኮል መጠጦች
በርካታ አሜሪካዊያን የሚጠቀሟቸው እንደ ቢራ፣ ውስኪ፣ ሻምፓኝ እና የሜክሲኮ ተኪላ የመሳሰሉ የአልኮል መጠጦች በአሜሪካ ታሪፉን ተከትሎ ከሚወደዱ እቃዎች መካከል ናቸው።
በፈረንጆቹ 2023 በአሜሪካ ቁጥር አንድ የቢራ ብራንድ የሜክሲኮ ምርት የሆነ ቢራ ነው። በዓመት ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የአልኮል መጠጦችን ከካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ ወዘተ የምታስገባው አሜሪካ በታሪፉ ምክንያት ዋጋው ለዜጎቿ የማይቀመስ ሊሆን ይችላል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
Via EPD