በእገታ ወንጀል የደብረ ማርቆስን ሕዝብ ሲያሰቃዩ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች የግፍ ገንዘብ ለመቀበል ሲሉ እጅ ከፈንጅ ተይዘዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው ላመስግን ካክች አስማረ፣ እሱባለው ጥበብ አስማረ እና እድሜዓለም ታገለ ይርዳው የተባሉ ግለሰቦች መጋቢት 10/2017 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ከአንዲት ግለሰብ ቤት በኃይል ገብተው እና አግተው 1 ሚሊዮን ብር እንድትሰጣቸው ይጠይቋታል። ግለሰቧ በሰዓቱ ምንም ብር እንደሌላት እና በቀጣዩ ቀን የጠየቁትን ገንዘብ አፈላልጋ እንደምትሰጣቸው ታግባባቸዋለች።
አጋቾቹም ነግቶ ገንዘቡን ከመስጠቷ በፊት ለጸጥታ ኃይልም ይሁን ለማንኛውም ግለሰብ ስለጉዳዩ ብትናገር እንደሚገድሏት በማስፈራራት ወጥተው ይሄዳሉ። ከወጡ በኋላም ከግለሰቧ ጋር የስልክ ንግግር እያደረጉ እሷም የተጠየቀችውን ገንዘብ መጠን እንዲቀንሱላት ትለማመናቸዋለች። ከብዙ የሰልክ ልውውጥ እና ማንገራገር በኃላ ገንዘቡ ወደ 300 ሺህ ብር እንደሚወርድላት ነገሯት።
ግለሰቧም መጋቢት 11/2017 ዓ.ም ወደ ፓሊስ ጣቢያ በመሄድ ጉዳዩን አስረዳች። ለገንዘብ ጠያቂዎች ደግሞ የጠየቁትን ብር እንደያዘች እና የት መገናኘት እንዳለባቸው እየነገረቻቸው እነርሱም መቀባበያ ቦታውን እያመቻቹ ነበር።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ፓሊስ መምሪያ ባልደረቦች ደግሞ የግለሰቧን ጥቆማ ተቀብለው በፓሊሳዊ ጥበብ መዘጋጀት ጀምረዋል። ገንዘብ ጠያቂዎቹ ግለሰቧ ላይ ተደጋጋሚ ስልክ እየደወሉ ቦታ ይቀጥሯታል። መልሰው በመደወል የቀጠሯትን ቦታ ይቀያይራሉ።
ከሦስት ጊዜ የቀጠሮ መቀያየር በኋላ ስውር እና ምቹ ያሉት ቦታ ላይ ገንዘቡን ይዛ እንድትመጣ ቀጠሯት። እሷም እሽ አለች።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አባላትም ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል። ራሳቸውን በጥበብ ከልለው ከተስፋው ብር መቀባበያ ተገኙ። ግለሰቧም በተለመደው የስልክ ልውውጥ “ኑ ተቀበሉኝ” አለቻቸው።
እነዚህ ግለሰቦች ገንዘብ ሊቀበሉ ቢመጡም የበደሉት ሕዝብ እምባ ሌላ ነገር ላይ ጣላቸው። ጀግኒቷ ሴት ከሌላት ላይ ሊቀሟት የመጡ ሕገ ወጦችን በሕግ እጅ ላይ ጣለቻቸው።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ ግለሰቧ ጥቆማ እንደሰጠቻቸው ጠንካራ ፖሊሳዊ ክትትል በማካሄድ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ግለሰቦች በከተማው የእገታ፣ የዘረፋ እና የግድያ ወንጀሎችን እንደሚፈጽሙ ተጠቁሞ ሲፈለጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ከግለሰቦቹ አንዱ የታጣቂው ቡድን አባል ኾኖ ሰላምን ሲያደፈርስ የቆየ እና ይቅርታ ጠይቆ የገባ እንደኾነም ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ ገንዘብ ሊቀበሉ እጅ ከፈንጅ ከተያዙ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ሁለት ክላሽ ከ55 ጥይት ጋር፣ አንድ ሽጉጥና ጎራዴ መገኘቱን ኮማንደሩ ገልጸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ የተጠለሉበት ቤት የአንደኛው ግብረ አበራቸው እንደኾነ እና ሁሉም የተያዙ መሳሪያዎች ቤት ውስጥ ተቆፍሮ ተደብቀው እንደተገኙም ገልጸዋል።
“ደብረ ማርቆስ በቁርጠኛ ልጇ እና በትጉህ የፖሊስ አባላቶቿ ጥረት እፎይ ብላለች፤ ለወራት ነዋሪዎቿን ሲያሸብሩ የከረሙ ግለሰቦች በሕግ ጥላ ስር ውለዋል” ነው ያሉት ኮማንደር ቢምረው።
በሕገ ወጦች እንዲህ ዓይነት ገንዘብ የሚጠየቁ ነዋሪዎች በሚደርስባቸው ተራ ዛቻ ሳይሸበሩ ጉዳዩን ለጸጥታ ኃይሎች በመጠቆም ማስያዝ እንደሚችሉ የዛሬው ድል ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ከሕዝብ ጥቆማ ጋር በመተባበር ከተሠራ ለሰላም እንቅፋት የሚኾን አንዳች ኃይል እንደማይኖርም አረጋግጠዋል።
ደብረ ማርቆስ ከተማ እና ነዋሪዎቿ አሁን ሰላም ናቸው፤ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣም በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንን የመምሪያ ኀላፊውን ጠቅሶ አሚኮ ዘግቧል።
በቴሌግራም ያግኙን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk