“ለእኛ ሲባል ኦሮሚያ ገሃነብ ትሁን ፖለቲካ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የኦፌኮ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስታወቁ። ኃላፊው ይህ ያሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) ከተለያዩ የኦሮሞ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ከየካቲት 12 እስከ 16 የ የአራት ቀን ውይይት ካደረጉ በሁዋላ ያወጡት መግለጫ ተከትሎ የተነሳውን ጫጫታ አስመልክቶ ነው።
ይህንኑ ውይይትና የውይይቱን መቋጫ አስመልክቶ መድኩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳዘጋጁት በመግለጽ ውሳኔውን የማጣጣል አካሄድ የተመረጠው ፓርቲዎቹ የደረሱበትን ባስታወቁ ቅጽበት ነው ። አብይ አህመድ ” ሰሜኖቹ፣ ኤርትራ፣ ትግራይና አማራ ሊወጉን ነው። እንተባበር” በማለት አቶ ዳውድ ኢብሳንና ፕሮፌሰር መረራን አሳምነው ውይይቱ መዘጋጀቱን በመጥቀስ ነበር የማጣጣሉ ዘመቻ በቅብብሎሽ የተስፋፋው። ሁሉም ይህን ቢሉም ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባለውን ሁሉ አላሉንም” ሲሉ ስማቸው የተጠቀሱት ምስክርነት ሰጥተዋል። አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ሰላም እንዲወርድ ቢተጉት ሊገርም እንደማይገባም ያመልከቱ አሉ፣ እነዚህ ወገኖች ይልቁኑም በአማራ ክልል የተጀመረው የሰላም ውይይት እንዲገፋ ሁሉም ውገገኖች አልይ ጫና ማሳደር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢትዮሪቪው ባላት መረጃና አዲስ አበባ በመገኘት ለማጣራት እንደሞከረችው በኦሮሚያ ክልል ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን የማግባባትና የማስማማት ስራ ከተጀመረ ዓመት አልፏል። ቀደም ሲል ከከሸፈው ሌላ በአዲስ የተጀመረው ድርጅቶቹን የማቀራረብ ስራ በትጋት መሰራት የጀመረው ” ህዝብ በተለያዩ መድረኮችና በሰላማዊ ሰልፍ ‘በቃን ሲል ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ድምጹን ማሰማቱን ተከትሎ ነው” ሲሉ በውይይቱ የተሳተፉ ነግረውናል።
መግለጫውን ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉ አክራሪ ቡድኖች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ጃል መሮ፣ የተለያዩ የብሄር አደረጃጀቶች፣ በአማራ ክልል ጠብ መንጃ ያነሱትን የፋኖ ኃይሎች የሚደግፉና የሚመሩ አካላት፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ወዘተ አምርረው የተቃወሙት ለምን ይሆን? የሚለው አበይት ጉዳይ እንዲያብራሩ የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲምን ጠይቀናቸው ” ለእኔ ጥቅምና ፍላጎት ስትሉ ኦሮሚያ ገሃነም እንድትሂን ፍቀዱ አይነት ተቀባይነት የሌለው ጩኸት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ኩሽ” ከሚሰኘውና የኦሮሞ ሕዝብ ጠበቃ እንደሆነ ከሚናገረው የዩቲዩብ አውድ ጋር ጥያቄና መልስ ያደረጉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከላይ በተገለጸው አግባብ የቀረበውንና እየቀረበ ያለውን ተቃውሞ አስመልክቶ ራስን ከሌሎች በላይ አድርጎ ከማሰብ የሚመነጭ ቅሬታ አግባብ እንዳልሆነ፣ ይልቁኑም ሁሉም በየአካባቢው ለሰላማዊ ንግግር ቅድሚያ ቢሰጥ የሚበጀ እንደሆነ ጎረቤት አገራት የገጠማቸውን ቀውስ ዘርዝረው ምላሽ ሰጥትተዋል።
የኩሽ ሚዲያ ጠያቂ በተደጋጋሚ ” ለምን ትነጋገራላችሁ? እጃችሁን ተጠምዝዛቸሁ ነው ወዘተ ” በሚል በተደጋጋሚ ላቀረበው ጥያቄ፣ ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሜኖቹን እንውጋ አላሉኝም” ሲሉ ደጋግመው ከመለሱ በሁዋላ ” በሰሜኑ ጦርነት ሁሉም ግፋ በለው ሲል እኛ ውይይት ይደረግ የሚል አቋም ነበረን። ይህ አቋማችን የጸና ነው። ዛሬም ሰላማዊ መንገድ ነው የምንከተለው። የዛኔ ዘራፍ ወደፊት ይሉ የነበሩ ተገልብጠው ዛሬ እኛን ለመውቀስ አይችሉም። የሰላም አማራጭ ውይይት በር ሲከፈት የመንችለውን ያህል መነገድ እንሄዳለን” ሲሉ ግልጹን አስታውቀዋል።
አቶ ሱልጣን ቃሲም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጥንቃቄና በሰከነ መንገድ ለሚረዱ ማናቸውም ኃይላት፣ የኦሮሚያ ሰላም መሆን ለድፍን ኢትዮጵያ ሰላም መሆን ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ የሰላማዊ ውይይቱን ጅማሪ ማድነቅ እንደሚገባቸው ይጠቅሳሉ።
አሁን ከዚያም ከዚህም የሚሰማው ጩኸት በኦሮሚያ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አንድ መሰባሰባቸው ማዕከላዊ መንግስት ላይ የሚፈጠረውን ጫናና ተጽዕኖ ይቀንሳል ከሚል ስጋት እንደ ሆነ የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም አስታውቀዋል።
በተለይ ለኢትዮሪቪው ቃላቸውን የሰጡት አቶ ሱልጣን ቃሲም ይህ አሁን እየተሰማ ያለው ተቃውሞ “ኢትዮጵያን በብቸኛነት ከመቆጣጠር ያረጃ እሳቤ የተነሳ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። አክለውም ” ማንም ለሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል አካል የኦሮሚያን ገሃነብ መሆን አይመኝም። በኦሮሚያ ገሃነብ መሆን የሚያተርፍም የለም። እኛም አንፈቅድም” ብለዋል።
በኦሮሚያ መታመስ አተርፋለሁ የሚሉ ሁሉ በብቸኛነት ስልጣን የመቆጣጠር፣ የበላይነት እሳቤ ያላቸው፣ ጠብ መንጃ ነካሾች እንደሆኑ ያመለከቱት አቶ ሱልጣን፣” እነዚህ ኃይሎች ፍላጎታቸው የተዳከመች ኦሮሚያን ማየት፣ የተበታተኑ ኃይሎች የፍልሚያ አውድማ የሆነች ኦሮሚያን ነው” በማለት ህላማቸው ኧውን ቢሆን የመጀመሪያ ተጎጂዎች እነዚሁ ኃይሎች እንደሆኑ አመልክተዋል።
ማናቸውም ኃይላት ከበላይነት ስሜት የሚቀዳና ይህንኑ ስሜታቸውን ለማስጠበቅ ቢያልሙም ዛሬ ላይ ኦሮሚያ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሃዊ የፖለቲካና የስልጣን ድርሻ ከመጠየቅና ድርሻዋን ከማስከበር ወደ ሁዋላ የሚል አካል እንደሌለ አስታውቀዋል።
ተቃውሞ ያሰማው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጭምር ስለመሆኑ ተጠይቀው ” በመጀመሪያ የኦነሰ ተቃውሞ የተጀመረውን አካሄድ ሊያደናቅፍ እንደማይችል መታወቅ አለበት” ነው ያሉት፡፡ ሲያብራሩም የኦነሰ ደጋፊዎች በሰላማዊ መንገድ መታገል አይቻልም ብለው ጠብ መንጃ ያነሱ ሲሆኑ እኛ ደግሞ ከጅምሩ ጠብ መንጃ አያዋጣም በሚል ሰላማዊ መንገድ የምንከተል በመሆኑ ልዩነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
“በኦሮሚያ ሕዝብ በአደባባይ ሰላም እንደሚፈልግ፣ ጦርነት እንደሰለቸው ደጋግሞ አስታውቋል። እኛ የምነሳማው የሕዝብን ድምጽ ነው” የሚሉት አቶ ሱልጣን፣ “አሁን ላይ እኛ የምንለው ሁለቱም አካላት ወደ ይፋዊ ተኩስ አቁም ይምጡ ነው። የሚያዋጣውም እሱው ነው” ብለዋል። ፐሮፌሰር መረራም ለከኩሽ ሚዲያ ” ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪዬን አስተላልፍልኝ” በማለት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት በደምሳሳው “መንግስትን አትመኑ” የሚል ስጋት ላይ ላዩን ስጋቱን መግለጹን የዳሰሱት የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ “እኛ ሳናውቅ ለምን ተደረድራችሁ” የሚለው አቋሙ ፍጹም ስህተት እንደሆነ አመልክተዋል። ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው ልክ ፕሮፌሰር እንዳሉት ወደ ስለማዊው መንገድ እንዲመጡ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ብልጽና የሽግግር መንግስት መጠየቁን አስመልክቶ ” ቅዠት ነው” ማለቱን ፕሮፌሰር መረራ ” አስቆኛል” በሚል ያለፉት ሲሆን አቶ ሱልጣን ቃሲም በብኩላቸው፣ የራሳቸው የውስጥ የፖለቲካ ሽኩቻ ካልሆነ በቀር ከመንግስት የመጣ ነገር እንደሌለ ጠቁመው አልፈውታል።
ጅምሩ ምን ዓይነት እድገት እንዳለው ተጠይቀው ” እስካሁን ኦነግና ኦፌኮ የጋራ የመደራደሪያ ሃሳብ የማመንጨት ስራ አዘጋጅተዋል፤ በፊደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ወደ ቀጣዩ ድርድር ለማምራት እየሰራን ነው። ለጊዜው ከዚህ በላይ ማለት አይቻልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሁለቱ ድርጅቶች የመግባቢያ ሰነድ ከመፈራረም ውጪ በዚህ መልኩ በጋር አጀንዳ አዘጋጅተው ለመስራት የተስማሙበት ጊዜ አለመኖሩን አንስተው እርምጃው የሚደነቅ መሆኑን የኦፌኮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሱልጣን ቃሲም አስታውቀዋል።
ፕሮፌሰር መረራ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጡን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ” አሁን ጉዳዩ የሁለት ፓርቲዎች ነው። ጅምራችን መልካም በመሆኑ ጥንቃቄ ያሻናል። በጥንቃቄ የምንጓዝበት ወቅት በመሆኑ በጋራ መግለጫ እስክንሰጥ ታገሱን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በቴለኢግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk