“ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበ ሃይሌ እድሜ ልኩን በታሪኩ ግጭት እየጠመቀ የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት በማስገባት ያለ ምንም ወታደራዊ ዕውቀት ወጣቱን ወደ እሳት አሥገብቶ የማስፈጀት ታሪክ ያለው ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው” በሚል መግቢያ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ኃይል በማስተባበር የፕሪቶሪያውን የሰላም አማራጭ ስምምነት ማፍረሱን ገልጾ የአገር መከላከያ ላወጣው የጦርነት ውሎ ትህነግ ምላሽ ሰጠ።
መግለጫው ቃል በቃል “ምግበና አጋሮቹ” በሚል ለተገለጸው ክስ ቃል በቃል እየጠቀሰ ማስተባበያ ባይሰጥም፣ የአገር መከላከያ ይህን መሰሉን መግለጫ ማውጣቱን “ላም ባለዋለበት” ዓይነት እንደሆነ አመልክቷል።
“ምዕራብ ትግራይ” በሚል ስያሜ የሚጠራውን የወልቃይት ጠገዴን መንግስት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመልስ ያሳሰበው የትህነግ መግለጫ፣ ትግራይ ክልል ያሉ ታጣቂዎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ሲጠይቅ ሻዕቢያ በኃይል ስለያዘው አካባቢ ያነሳው ነገር የለም። ሙሉ መግለጫውን ያንብቡ።
ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!!
የትግራይ ህዝብ ሰላምና ጥቅም የሚረጋገጠው በሰላማዊ ትግልና ውይይት እንጂ በጦርነት አይደለም የሚል ፅኑ እምነት የትላንት፣ ዛሬና ነገ ኣቋም ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ጠብመንጃ አንስቶ የተቃጣበትን ዘር ማጥፋት ሲጋፈጥ፤የሚያጋጥመውን ሁለገብ ኪሳራ መገመት አቅቶት ሳይሆን እንደ ህዝብ ለመቀጠል ተገዶ የገባበት ብቸኛ ኣማራጭ ስለነበረ ነው።
የትግራይ ህዝብና ሰራዊትም ይህንን ከባድና የተወሳሰበ ትግል ተሸክሞ፣ ለአፍታ እንኳ አጋዥ ሳይጠይቅና ሳይለግም የትግራይ ህዝብ ከገፀ ምድር ለማጥፋት የተወጠነው ኣላማ በማክሸፍ አኩሪ ታሪክ ሰርቷል። የትግራይ ሰራዊትም የዚህ ሂደት ውጤት ነው፡፡
ሰላምን መፈለግ ኣስፈላጊ ቢሆንም፤ የኣንበሳውን ድርሻና ሃላፊነት ያለበት የፌደራል መንግስት የፕሪቶርያው የሠላም ስምምነት ሳይሸራረፍና በኣጭር ግዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
የተፈናቀሉ ወገኖች የሰላምንና ደህንነት ዋስትና ተረጋግጦላቸው ወደቀያቸው እንዲመለሱ፣ የትግራይ ህገ መንግስታዊ ግዛታዊ አንድነት ቅድመ ጦርነት ወደነበረበት እንዲመለስ፣ በትግራይ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች እንዲወጡ፣ ጦርነቱ ካስከተለው አስከፊ ጉዳት ክልሉ እንዲያገግም የትግራይ መልሶ ግንባታና በጦርነቱ ምክንያት የወደመው ንብረትና መሰረተ ልማት መልሶ የሚተካበትና የሚካካስበት ግልፅ ኣቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ኣለበት፡፡
ይህ በሚፈፀምበት ሁኔታ ሰራዊቱና የሰራዊቱ አመራር ለረዥም ጊዜ አይደለም፤ ለአንድ ደቂቃ እንኳን መሳርያ አንግተው ለመንከራተት የሚፈልጉበት ኣንዳችም ምክንያት የላቸውም። ምክንያቱም ጦርነት ምን እንደሆነ በወሬ ሳይሆን በተግባር ስለሚያውቁ። የትግራይ ሰራዊትና ኣመራሩ በትግራይ ህዝብ ላይ ለታወጀው የጅምላ ጭፍጨፋ ጦርነት ለመከላከል የወሰኑት በላያቸው ላይ ይወርድ የነበረው ግፍ እስኪቆም ድረስ ለመታገል እንጂ ጦርነት ምርጫቸው ስለነበረ ኣይደለም ።
በተለያዩ ግዜያት እንደ ታላቅ ገድል በሰበር ዜና በትግራይ ህዝብ፣ በተቋሞቹና መሪዎቹ በዘመን ኣመጣሽ የመገናኛ ኣውታሮች ጥላቻና ፕሮፖጋንዳ ሲሰበክ ከሩዋንዳው እልቂት ቀጥሎ ሊሆን ይችላል። የዚሁ ተቀጥላ በሆነው ድርጊት የተለያዩ ወገኖች ሰራዊታችንና አመራሩን በተደጋጋሚ መሬት ላይ በሌለ የፈጠራ ክስ ሲወነጅሉ እየተመለከትን ነው። ከነዚህ መሰል ክሶች አንዱ በቅርቡ በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በሚተዳደር ማህበራዊ ድህረ ገፅ የተዘረጋው በ ጀነራል ምግበይ ሀይለ ላይ ያነጣጠረ ውንጀላና ስም ማጥፋት ኣንዱ ነው።
በተሰራጨው ፅሁፍ ከተካተቱት መልእክቶች መካከል “ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል እሳቤ፤ ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያሥበላ ዉጊያ እምቢ ሲለው የራሱን ታጣቂዎች ረሽኖና ገድሎ ውጊያው ሳይሳካለት አከርካሪው ተመትቶ ሸሽቷል።” የሚል ይገኝበታል። ይህ መግለጫም የሂደቶቹ ተቀጥላና እሳቱ ባለበት ለማርገብ ከመጣር ይልቅ ማርገብገብ፣ ላጋጠመህ የራስ ችግር ለተግባራዊ መፍትሄ ከመጣር ይልቅ የማይመለከተው ኣካል በመፍጠርና ጣት በመቀሰር ሰላምና እድገትን እንዳይፀና የሚያደርግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በርግጥ ዜናውን ከውጭ ለሚያይ ወገን ሊያደናግር ይችል ይሆናል፣ እውነቱንና የሰራዊታችንን ፍላጎትና ዓላማ ለሚያውቅ ግን “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!!” ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ኣይኖረውም። ይህ ግልብና ብስለት የጎደለው ይዘት እንዳለ ሆኖ የትግራይ ህዝብ ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር የሚደረግ ተጋድሎ እንዲህ አቃሎና አንኳሶ ማቅረብ ግን የፕሪቶርያውን ስምምነት ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ትልቅ ድርሻ ካለው ተቋም የማይጠበቅና ሀላፊነት የጎደለው ስለሆነ በፍጥነት መስተካከል አለበት።
ጀነራል ምግበይና ጓዶቹ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በጥብቅ ዲሲፕሊን ተገዝተው ስራቸውን የሚፈፅሙ እንጂ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ምንም አይነት እንቅቃሴ የሌሉና ያልነበሩ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል። ሰላምን ለማፅናት ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ነገሮች አንዱ እውነት ላይ የተመሰረተ ሀቀኛ መረጃ እንጂ በክፋትና በተንኮል የተጆቦነ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሊሆን ኣይችልም፡፡ የሀገርን ሰራዊት ወክሎ መረጃ በሚያሰራጭ የመረጃ ቋት እንዲህ አይነቱ እርባና ቢስ ዜና መዘርጋት የትግራይ ሰራዊት ለሰላም እየከፈለ ያለውን ዋጋና ልፋት የውሃ ሽታ የሚያደርግና በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት ኣይነት መግለጫ መውጣቱ ከልብ ኣሳዛኝ ነው።
በመሆኑም የወጣው መግለጫ የምላስ ወለምታ ሊሆን ስለሚችል መልሶ ቢጠናና ይቅርታ ቢጠየቅበት፤ ሰላምን የሚያፀኑ የፕሪቶርያ ሠላም ስምምነት ሳይሸራረፉና በኣጭር ግዜ ውስጥ ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉ ሃቀኛ ተግባሮች እንዲከናወኑ እያሳሰብን፣ በኛ በኩል የፕሪቶርያ ሠላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ቁርጠኝነታችንን መግለፅ እንወዳለን፡፡
የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
13/07/2017 ዓ/ም