ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት የአሰራር ሂደቶችን በማረምና ለጉድለቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦችን የህግ ተጠያቂ በማድረግ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ደምጤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተገኘበትን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁነት የለውም ብለዋል። ተጀምሮ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት ገንዘብ ወጪ ተደርጓል።
- ተቋሙ የተገኘበትን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁነት የለውም፣
- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጀምረው ላልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ክፍያ ፈጽሟል
- ከህግ አግባብ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎችን ኦዲት በማድረግ በ15 ቀናት ሪፖርት እንዲቀርብ ታዟል፣
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አላግባብ የህዝብና የመንግሥት ሀብት እንዲባክን ማድረጉን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሰታወቀ።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት ውልና የሰው ሀብት አስተዳደር አፈፃፀም የክዋኔ ሪፖርትን ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ወደ ትግበራ ከመግባታቸው በፊት የቅድመ አዋጭነት ጥናት ግምገማ ተደርጎላቸው እንዲከናወኑ አልተደረገም ብለዋል።
በመንግሥት በጀትና በዓለም አቀፍ ድጋፍና ብድር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች የትግበራ ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው ለምክረ ሀሳብ ለሚመለከታቸው አካለት አለማቅረቡ ተገቢነት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል።
ለትራንስፖርት ኪራይ፣ ለዳታ ማዕከል ግንባታ፣ ለሳይንስ ካፌና ለሰራተኛ ደሞዝ ያለአግባብ የወጣውን ወጪ ኦዲት በማድረግ በ15 ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ለተገኘበት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት የአሰራር ሂደቶችን በማረምና ለጉድለቱ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦችን የህግ ተጠያቂ በማድረግ ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቅ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ደምጤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የተገኘበትን የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁነት የለውም ብለዋል። ተጀምሮ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት ገንዘብ ወጪ ተደርጓል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሰው ሀብትና የንብረት አስተዳደር ሂደቱ ደካማ ነው ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤ ከህግ አግባብ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎች ላይ በፍጥነት የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። በኦዲት ክፍተቶች ላይ የፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ክትትል በማድረግ የህግ ተጠያቂነት ማስፈን ይጠበቅበታል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ የሚሰራቸው ሥራዎች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው በአንዳንድ ዘርፎች የኦዲት ጉድለት መከሰቱን ተናግረዋል።
ችግሮቹን ለመፍታት የድርጊት መርሐግብር በማዘጋጀት የተወሰዱ እርምጃዎችን ለቋሚ ኮሚቴው እናቀርባለን ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም ባንክና ከአጋር አካለት ጋር የሚሰሩ ሥራዎች በአይነትና በቁጥር በርካታ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህ መነሻ የተስተዋሉ የኦዲት ክፍተቶችን ለማረም ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
በክብረአብ በላቸው ኢፕድ