የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የአራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረውን እግድ ከዛሬ ጀምሮ ማንሳቱን አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የባለስልጣኑ እርምጃ መልካም የሚባል መሆኑን ገልጿል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ በሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ እና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ላይ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።
ባለስልጣኑ ባወጣው መግለጫም ድርጅቶቹ ላይ ባደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ህግን ተላልፈው በመገኘታቸው ምክንያት የእግድ እርምጃ ወስዶባቸው እንደነበር ገልጿል።
በታገዱ ድርጅቶች ዙሪያ የምርመራ ስራውን በማጠናቀቅ በውጤቱ ዙሪያ ከድርጅቶቹ ጋር በመነጋገር መታረም የሚገባቸው እንደሚታረሙና በቀጣይ በቅንጅትና ትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት መፍጠር መቻሉን በመግለጫው አመልክቷል።
በተጨማሪም በእግዱ ዙሪያ የብሄራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመራሮች ጋር ምክክር መደረጉንና በኮሚሽኑ በኩል ምክረ-ሀሳቦች መቅረባቸውን አውስቷል።
ይህንኑ ተከትሎ ባለስልጣኑ ዘርፉ እንዲጎለብት ካለው ቁርጠኝነት፤ ከታገዱ ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት የተፈጠረውን መግባባት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰጠውን ምክረ-ሃሳብ ግምት ውስጥ በማስገባት ድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ከዛሬ ጀምሮ በማስጠንቀቂያ እንዲነሳ ማድረጉን አስታውቋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹም በተቋቋሙበት ዓላማ መሰረት ገለልተኛነታቸውን በመጠበቅና በህግ አግባብ በመንቀሳቀስ የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ መስራት እንደሚገባቸው አሳስቧል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የጀመረውን የክትትልና የቁጥጥር ስራ አጠናክሮ በመቀጠል የላቀ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ነው የገለጸው።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ መልካም እርምጃ ነው ብሏል።
በሂደቱ ተባባሪ ለነበሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን እና ሌሎች የመንግሥት አካላት እንዲሁም ለአራቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምስጋና አቅርቧል።
በዚህ አጋጣሚ የሚከሰቱ ችግሮችን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ሀገራዊ ጥቅምን በማስቀደም በመቀራረብ እና በመወያየት የመፍታት ልምድ እንዲጎለብት ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል።