“በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የምግበ ሀይለ ተላላኪ ፅንፈኞች በለኮሱት እሳት ተለብልበዋል” ሲል የአገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።
በቀድሞ በብርጋዲየር ጄኔራል፣ የአሁኑ የትግራይ ታጣቂዎች መሪ ምግበ ሀይለና ግብረ አበሮቹ አደራጅነትና አይዞህ ባይነት “ዘመቻ አንድነት” በሚል ስያሜ የተጀመረው ትንኮሳ መቋጨቱን የአገር መከላከያ ያስታወቀው የደረሰውን ጉዳት በመዘርዘር ነው። በተለያዩ የአማራ ክልል የዞን ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛው ቡድን በሞኝነት በገባበት ጦርነት መደምሰሱን መግለጫው አስታውቋል። ከመከላከያ ማህበራዊ ገጽ የተወሰደው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበ ሃይሌ እድሜ ልኩን በታሪኩ ግጭት እየጠመቀ የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት በማስገባት ያለ ምንም ወታደራዊ ዕውቀት ወጣቱን ወደ እሳት አሥገብቶ የማስፈጀት ታሪክ ያለው ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው።
ውጊያ ከብዶት የሸሸውን ወጣት ለምን ሸሸህ በሚል ሰበብ በጅምላ የመረሸን ልምድ ያለው ያለ ዕውቀት የትግራይን ወጣቶች ደም ሲመጥ የቆየ መሆኑ ሳያንሠው አሁን ላይም በሞኙ የፅንፈኛው መሪዎች ነን ባዮች አማካኝነት የሠላም ፈላጊውን የአማራን ወጣት ህይወት ለመቅጠፍ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑ ታውቋል።
ባለፈው ጊዜ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠር የትግራይ ወጣትን እየረሸነ እያሥረሸነ የፈጀ የጥቁር ታሪክ ፀሃፊነቱ ሳያንስ አሁን ላይም መሠል ድርጊት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ነው።
ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል እሳቤ ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያሥበላ ዉጊያ እምቢ ሲለው የራሱን ታጣቂዎች ረሽኖና ገድሎ ውጊያው ሳይሳካለት አከርካሪው ተመትቶ ሸሽቷል።
ምግቤ ሃይሌ ዘረፋና ሌብነት የተካነበት መደበኛ ሥራው ነው ። በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ወርቅ እየዘረፈ በኤርትራ በኩል አድርጎ እየሸጠ ይገኛል። በኢህአዴግ ዘመን በዘረፋና ሌብነት ታዋቂ የነበረ ብቻ ሳይሆን በሰረቀውና በዘረፈው ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ፎቆችን የደረደረ አለፍ ሲልም ዱባይ ላይ ፎቆችን ለመሥራት በቅርብ ጊዜ የተዋዋለ ሥለመሆኑ በሶሻል ሚዲያ ሲነገር ቆይቷል።
በጦርነት ከቀቀለው ወጣት በተጨማሪ የረሸናቸው በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በመኖራቸው ትግራይ ሰላም እንድትሆን ከቶውንም አይፈቅድም። ምክንያቱም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ይጠይቀኛል የሚል ስጋት አንደኛው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እያደረገ ያለው የወርቅ ዘረፋ እንዳይጋለጥበት በማሠብ ነው።
በሌላ በኩል ምግበ ሀይለ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲፈርስ እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ከመሆኑም በላይ የጊዜያዊ መሥተዳድሩን ማህተም ለመንጠቅ እና በሀይል አፍርሶ ሥልጣን ለመያዝ የሞከረ የፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው።
የሠላም ጠንቅ የሆነው ምግበ ሃይሌ ለዚህ መሰሪ ተግባሩ ጅላጅሉን ፋኖ እንደ ተባባሪነት በመጠቀም ፅንፈኛው ፋኖ በራሱ ክልል ላይ ያልተገባ ውድመት እንዲፈፅም አዞታል። ነገር ግን ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ፅንፈኛውን አሥተባብሮ በጀመረው ትንኮሳ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷበታል።
በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የምግበ ሀይለ ተላላኪ ፅንፈኞች በለኮሱት እሳት ተለብልበዋል።
በዚህ ሁለት ቀናት ብቻ 317 የተገደ’ለ፣ 41 የተማረከ፣ 125 የቆሰለ፣ 27 እጅ የሠጠ፣ 51 በምህረት የገባ፣ 15 መረጃ አቀባይ የተያዘ፣ በድምሩ 576 የሠው ኪሳራ ሲደርስበት 01 መትረየስ፣ 119 ክላሽ፣ 46 ኋላቀር መሣሪያ፣ 08 ሽጉጥ፣ 22 ቦምብ፣ 2,290 የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ 28 ትጥቅ፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክልና ሌሎች ልዩ ልዩ ቁሶችም በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ይህ በምግበ ሃይለና በግብረ አበሮቹ አይዞህ ባይነት ተነሳስቶ በህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የተነሳው ፅንፈኛ ቡድን በዚህ ልክ ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን በህይወት የተረፈው እግሬ አውጭኝ የተበታተነ መሆኑ ተረጋግጧል።
በቴሌግራም ያግኙን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk