ኢትዮሪቪው – “ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካን ማቋቋም ነው” ሲሉ አብይ አሕመድ በፓርላማ ፊት ቀርበው አስታወቁ። አጀንዳው ታላቅና ኢትዮጵያ አንጡራ ሃብቷን አሟጣ የምትገብረበት በመሆኑ ዜናው የዕለቱ መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል። የሚያማቸው ቢኖርም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ከአፍሪካ አንደኛ ሆናለች።
ኢትዮጵያ በዓመት 24 ሚሊየን ኩንታል ገደማ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋት ጠቅሰው አጀንዳው አንገብጋቢ መሆኑን ያመለከተቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ የፋብሪካው ግንባታ በሶስት ዓመት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ይፋ አድርገዋል።
ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ የተነገረለት የማዳበሪያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያ ሌላው የህዳሴ ግድብ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በቅርቡ የህዳሴ ግድብ ሪባን እንደሚቆረጥ አስታውሰው የማዳበሪያ ኝባታውም ብሄራዊ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባው የጠቆሙት አብይ አሕመድ፣ “ሁለተኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካን ማቋቋም ነው” ሲሉ ፕሮጀክቱን ከወዲሁ ብሄራዊ ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንዳሉት ኢትዮጵያ ማዳበሪያን ማምረት አለመቻሏ በርካታ አርሶ አደርን የሚነካ ጉዳይ በመሆኑ በዘላቅነት ለመፍታት ጥናት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል። በተደረገው ጥናት መሰረት ለግንባታው ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋል፤ የማዳበሪያ ፋብሪካውን አቋቁሞ ለመስራት በትንሹ ሶስት ዓመትና ከዚያ በላይ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ግንባታው ከተቻለ ከግሉ ዘርፍ ጋር፣ በግለሰብ ኢንቨስትመንት ካልተቻለም መንግስት በራሱ የሚገነባ ይሆናል ብለዋል።
የአፍር ማዳበሪያ የኢትዮጵያን ፍላጎት በሚመልስ መልኩ መመረት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ፋብሪካው የማቋቋም ሂደቱ ምናልባትም በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚጀመሩ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ 24 ሚሊየን ኩንታል ገደማ የአፍር ማዳበሪያ የሚያስፈልጋት ሲሆን፤ በቀን 150 ሺህ ኩንታል የአፍር ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ሀገር ውስጥ ታጓጉዛለች፤ ይህንን ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደር በወታደር ታጅቦ ይሰራጫል።
በአማራ ክልል ለሚገኙ አርሶአደሮች 7ሺህ የጭነት ትራንስፖርት የአፍር ማዳበሪያ በመከላከያ ሰራዊት ታጅቦ መዳረሱን አስታውሰው፤ መንግስት በብዙ ሂደት አልፎ ማዳበሪያውን ወደሀገር ውስጥ ካመጣ በኋላ ለአርሶ አደሩ ማዳረሱም ሌላ ወጭ እየሆነበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግረመንገዳቸውን መንግስት ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ለማድረስ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉበት ገልጸዋል። አርሶ አደሩ ማዳበሪያ እንዳይደርሰው ከሚያደርጉ ታጣቂዎች ዘረፋና የስርጭት መስተጓጎል ለመከላከል ማዳበሪያ በወታደር አጀብ እንደሚከፋፈልም ተናግረዋል።
ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር እንዳይደርስ የሚያደርጉ ወይም የሚያስተጓጉሉ ታጣቂዎች ይህን የሚያደርጉበትን ምክንያትና ይህን ባማድርጋቸው ምን እንደሚጠቀሙ ገልጸው አያውቁም። አብረዋቸው የሚሰሩትም ሚዲያዎች ይህንን ሲያወግዙ ወይም ምክኛቱን ጠይቀው ለህዝብ ይፋ አያደርጉም። አርሶ አደሩ በተደጋጋሚ ቅሬታውን ሲያሰማ ምስማት ኝ የተለመደ ነው።
በተመሳሳይ የግብርና ዜና ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ አንደኛ ስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ከሰባት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያለነሰ መሬት በሰንዴ ሰብል ሸፍናለች። ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት ይጠበቃል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የሚያማቸው ሰዎች ቢኖሩም እውነታው ይህ ነውና ማመን አለባቸው ሲሉ ሰሞኑን በዘመቻ ሲቀርብ ለነበረው ተቃውሞ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ በአፍሪካ ከፍተኛው ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያማቸው ሰዎች ቢኖሩም እውነታው ይህ ነውና ማመን አለባቸው ነው ያሉት።
የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በሚመለከት መንግስት የ10 ዓመት የልማት እቅድ ማዘጋጀቱን አስታውሰው፤ ትልቁን እቅድ ከግብ ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ያለፈው ዓመት የሰብሰሃራን የኢኮኖሚክ እድገት አራት ነጥብ ሁለት በመቶ እንደሚሆን መገመታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በባለፈው ዓመት ሪፖርት እንደተመላከተው ኢትዮጵያ ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ የዒኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች።
በዚህ ዓመት ለሰብ ሰሃራን ኢኮኖሚያዊ እድገት የተሰጠው ግምት እምብዛም የራቀ ባይሆንም ኢትዮጵያ ስምንት ነጥብ አራት በመቶ ለማደግ አቅዳ እየሰረች እንደምትገኝ አመላክተዋል፡፡
ባለፉት ስምንት ወራት የነበሩ የኢኮኖሚ እቅድ አፈጻጸም እንደሚያመላክተው በሚቀጥለው አራት ወራት ጥረታችንን ከደገምን ካቀድነው በላይ እናሳካለን ተብሎ ይጠቃል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪ እየሰጡ ይገኛሉ።