የብርቱካን ሲሰሙት ህሊናን የሚፈታተነው ቃለ ምልልስና ቅንብር በተለያዩ ወገኖች ክርክር አስነስቷል። ቪዲዮውን ለራሳቸው ፖለቲካዊ ፍላጎት ጎራ ለይተው የተጠቀሙበት፣ በየዋህነት “የፍትህ ያለህ” ሲሉ የጠየቁ የታዩበትና፣ እውነታው እንዲጣራ አበክረው የሚወተውቱ ዜጎች ፈጥሯል።
ብርቱካን ተመስገን ከኢቢኤስ ቲቪ ጋር ያደርገችው ቆይታ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ ግራ የተጋቡ ጥቂት አይደሉም። በስፋት የማህበራዊ ሚዲያ አውዶች ላይ የተሰራጨው ይኸው ቃለ ምልልስ አየር ላይ ከዋለ በሁዋላ መስቀለኛ ጥያቄ በማንሳት ሙግት ያነሱ ወገኖች “በግል ፍላጎታችሁ ሳቢያ ፍትህን አታዳፍኑ፤ እውነቱ ይጣራ” በሚሉት ወገኖች የተሸፈኑ ይመስላል። ዕውነቱ እንዲጥራ የሚቀርበውን ጥያቄ መቃወም አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጹ ራሱ ኢቢኤስ ኃላፊነቱን ወስዶ በድጋሚ አድምቶ እንዲሰራም የመከሩ አሉ።
በየሰዓቱና ደቂቃው አዳዲ መረጃ እየጎረፈበት ውሎ ካደረ በሁዋላ አሁን ላይ ጋብ ያለው የብርቱካን ጉዳይ ወደ ፖሊስ ምርመራ መሸጋገሩን፣ ጣቢያውም ተዘጋ የሚሉ ዜናዎች በማህበራዊ ገሶች እየተሰሙ ነው። ግን በይፋ ከሚመከተው አካል የተባለ ነገር የለም።
ቃለ ምልልሱ ህሊናን በሚፈታተን መልኩ የቀረበ ከመሆኑ አንጻር አንድ ብሄር ሌላውን እንዳጠቃ በማድረግ ለቅስቀሳ የተጠቀሙበት ክፍሎች ጉዳዩን አጡዘውታል። የሻዕቢያ ደጋፊና ተከፋይ ሚዲያዎች ጉዳዩን የራሳቸው አድርገው በጡዘቱ ላይ ነዳጅ ሲረጩ ውለው ነው ያመሹት። ” መረጃው በርጋታ ሊጣራ ይገባዋል” በሚል ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግ የጠየቁ አሉ።
በሰብአዊነት ብቻ ቃለ ምልልሱን ሰምተው ስሜታቸው የተነካ ” ጥፋተኛ” ያሉትን አካል እያወገዙ ቪዲዮውን በማህበራዊ ገጻቸው እያንሸራሸሩ ባለበት ሰዓት የቪዲዮው መነሳት ተሰማና ሌላ ዜና ሆነ። በካቶች ቀድተውና እንዳሻቸው እየቆራረጡ የለጠፉት የብርቱካን ቪዲዮ መነሳቱ ወይም እንዲነሳ መደረጉ ምን ሊከላከል እንደሚችል ያልገባቸው “ለምን ይነሳል? ማን ነው ይህን የሚያደርገው” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ።
ኢቢኤስ በጥንቃቄና በበቂ ዝግጅት ይፋ ያደርገውን ቪዲዮ ከአየር ላይ ማውረዱን ተከትሎ ” መንግስት አስፈራርቶ ነው” የሚል መረጃ በስፋት በመሰራጨቱ የኢትዮሪቪው የአዲስ አበባ ተባባሪ ጉዳዩን አጣርቷል። ከሁለቱም ወገን መረጃ አግኝቷል።
ቪዲዮው እንዲነሳ ማስፈራሪያ ሰጥቷል የተባለው ፖሊስ በመሆኑ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ የጠየቀው ተባባሪያችን ከፌደራል ፖሊስ ” ጉዳዩ በተቃራኒው ነው። እንዲያውም ለምን እንዳነሱት ነው ጥያቄያችን” ሲሉ ለጊዜው ከዚህ በላይ መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የኢቢኤስ ሁለት ሰራተኞችን በሚቀርቧቸው ሰዎች አማካይነት የጠየቀው ተባባሪያችን ስም እንዳይጠቅስ “አደራ” ተብሎ ምስክርነት ተሰጥቶታል።
በዚሁ ምስክርነት መሰረት ብርቱካን ራስዋ ቪዲዮው እንዲነሳላት ቢሮ ድረስ በመምጣት ጥያቄ አቅርባለች። ራስዋ ቢሮ ድረስ ሄዳና ፈርማ ቃለ ምልልሱን እንዳደረገች የገለጹት ምስክሮች፣ በጥያቄዋ መሰረት ” የሚጎዳት ከሆነ” በሚል ቪዲዮው እንዲነሳ መደረጉን አመልክተዋል። ይነሳ ያለችበትን ምክንያት ግን ለማስረዳት ፈቃደኛ አልሆኑም።
” የሰላም ሚኒስቴርና ፖሊስ ቪዲዮውን መልሱ በሚል እየወተወተ መሆኑን እናውቃለን” ያሉት ሁለቱ ሰራተኞች በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ መረበሽ እንደተፈጠረም ሳይሸሽጉ ገልጸዋል።
የብርቱካንን ቪዲዮ አይተው በየዋህነት፣ በአዘኔታና በሰብአዊነት ስሜታቸውን የገለጹ ያሉትን ያህል ለራሳቸው ፍላጎት አዙረው የተጠቀሙበት መኖራቸው ተስተውሏል። ላለፉት ሶስትና አራት ወራት በልዩ ዝግጅት ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ እየተከታተሉ የሚጽፉ አፍቃሪ ሻዕቢያ ሚዲያዎች “ብርቱካን ታሰረች” ሲሉ አዲስ ዜና ይዘው የወጡት ከሁሉም ቀድመው ነው።

የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የተካተቱበት ድሮኖችን ኢትዮጵያ ማምረቷን ስታስታውቅ ” ጸረ ድሮን አለን” በሚል ምላሽ የሰጡት እነዚህ ሚዲያዎች በማህበራዊ ገጽ አውዳቸው ” አይ ጦቢያ” ሲሉም ከኤትዮጵያ የተሻለ ነጻነት እንዳላቸው አድርገው ፌዝ ቀላቅለዋል።
ኢትዮጵያ ያመረተቻቸው ድሮኖች በእንደገና ምህንድስና የተሻሻሉ፣ ለኢትዮጵያ ከፍታ እንዲያመቹ ተደርገው የተመረቱና በከፍተኛ ርቀት ላይ የሚንሳፈፉ እንደሆኑ መገለጹ ይታወሳል። የድሮን ማምረት ዜና እንደተሰማ “ድሮን ጃም እናደርጋለን፣ እናከሽፋለን” ሲሉም ምላሽ ሲሰጡ ከርመዋል።
ኢትዮጵያ የምታመርታቸው ድሮኖች ዒላማ የማይስቱ፣ አጥፍተው የሚጠፉ፣ ጃም የሚያደርጋቸውን የሚያወድሙ፣ ጸረ ድሮኖችን አቅጣጫ በማስቀየር ወደ መጡበት የሚመልስ ቴክኖሎጂ ያላቸው እንደሆኑ በምረቃው ወቅት ሲገልጽ ” ኢትዮጵያ ጦረኛ ናት” በሚል ክስ ሲያሰሙ የከረሙት እነዚሁ ሚዲያዎች የብርቱካንን ዜና ለራሳቸው ፋላጎት ሲተቀሙበት ታይቷል።
በቀርቡ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ አስመልክቶ ፖሊስ ማንም ሰው ድሮን ሳያስፈቅድ መጠቀም እንደማይችል ሲያሳስብ፣ ህጉን የሚያከብር ድሮን ቢታይ “ድሮኑን ቀልበን ከየትና ማን እንዴት እንደላከው በመለየት ባለቤቶቹን ለህግ እናቀርባለን” ማለቱ አይዘነጋም። ይህ ዜና ኢትዮጵያ በዘርፉ ላቅ ብላ በሄዷን የሚይሳይ ሆኖ ሳለ እነዚሁ ሚዲያዎች ሊያታጥሉት ሲሞክሩ ታይቷል።
ከጉዳዩ ጋር ባይገናኝም፣ ስለ ድሮን ማንሳት የተፈለገው የሻዕቢያ ደጋፊ ሚዲያዎች የመንግስታቸውን ስጋት በተደጋጋሚ እንደሚገልጹ ለማሳየትና፣ ማናቸውንም በኢትዮጵያ ሁከት፣ ረብሻና ትርምስ የሚፈጥር ጉዳይ ሆን ብለው የሚያራግቡት ከዚሁ ስጋት በመነጨ እንደሆነ አካሄዱ የገባቸው ዜጎች አስተያየት የሚሰጡበት ጉዳይ በመሆኑ ነው።
ዜናውን በሚፈልጉት አግባብ መጠቀም ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ ሻዕቢያ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ለበርካታ ዓመታትበነጻነት ሲሰሩ የኖሩትን የኢቢኤስ ቲቪ ባለቤት ኤርትራዊ መሆናቸውን እየገለጹ መንግስት ሚዲያውን እንደሚዘጋው የቅድሚያ ትንበያ እየሰጡ ነው።
ኢቤኤስም ሆነ እዚያ የሚሰሩ ሰራተኞች ስለ ጣቢያው መዘጋት ለጊዜው ምንም ባላሉበት ሁኔታ የሻዕቢያ ደጋፊ ሚዲያዎች በተደራጀ መልኩ ስለ ጣቢያው መዘጋት አስቀድመው በስፋት መዘገባቸው ሌላ አጀንዳ እንዳላቸው አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
ስለ ብርቱካን ቃለ ምልልስ የዝግጅት ክፍላችን በድጋፍም ሆነ በነቀፌታ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት አይፈልግም። ጥርት ያለ የምርመራ ስራ እንዲሰራበትና ሕዝብ እንዲማርበት በሚል የሚመለከታቸው ሁሉ ኃላፊነት ወስደው የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ማሰሰብ ግን ይወዳል። ስለ ብርቱካን ከየአቅጣጫው በሚወጡ ዘገባዎች ላይ የልጇን ምስል መለጠፍ ፍጹም አግባብ ነው ብለን ስለማናምን ሌሎችም በልጆች ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ሊወስዱ እንደሚገባ እንመክራለን።
የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል።
በ14/7/ 2017 ዓ.ም በEBS ፕሮግራም ላይ በተደረገ ቃለ ምልልስ ብርቱኳን ተመስገን ከበደ የተባለች በ2013 የትምህርት ዘመን በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ ነበርኩ በማለት የሰጠችዉ ሃሳብ ስህተት መሆኑና ዩኒቨርሲቲው የፋርማሲ ትምህርት ሲሰጥ በ2013 የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እንዳልነበረው ይገልጻል።
ስለሆነም ይህ ድርጊት በጣም ሃላፊነት የጎደለው እና ምንም አይነት ማስረጃ የሌለው ስለሆነ ግልጽ የሆነ ስም ማጥፋት እና የዩኒቨርሲቲያችንን ስም የምያጎድል ስለሆነ ኢቢኤስ ይህን ውንጀላ እስካልቀለበሰ ድረስ ዩኒቨርሲቲው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደምወስድ ይገደዳል።
ብርቱካን “ታሪኬ” ስትል የዘረዘረችውን ቪድዮ በመመልከት ጨመቀው ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያ ያስረጩት ወገኖች ትውልዷ ምስራቅ ጎጃም እንደሆነ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በፋርማሲ የትምህርት ዓይነት ጀምራ የሁለተኛ ዓመት ላይ ስትደርስ፣ አንድ ምሽት ከላይብረሪ ስትመለስ በግቢ ውስጥ ረብሻ ተከስቶ ከውስጥም ከውጪም ተኩስ ሲበረታ ነበር “ቶሎ አምልጡ” በማለት መኪና ውስጥ ግቡ ብለው ያገቷቸው አካላት ይዘዋቸው ወደ ጫካ ያመሩት።
“የፈልግናችሁ ለስልጠና ነው አብራችሁን ትሆናላችሁ ብለውን ጫካ አስቀመጡን በጣም የመከራ ጊዜ ነበር የሚበላ የሚጠጣ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ሁኔታ ዓመት ከስድስት ወር ተቆጠረ ከዚያም ‘አሁን ስራችንን እንጀምር’ በማለት ሁላችንንም ልብስ አስወልቀው አሰለፉን እኔ ስድስተኛ ነበርኩ እየተፈራረቁ ነበር የሚደፈሩን ከዛ በኋላ ሰውነቴ ደንዝዟል። በፌሮ ይወጉት ነበር “ብላለች በማለት ለምስሏ ባዘጋጁት መግቢያ ላይ ገልጸዋል።
በስድስተኛ ቀኔ ስነቃ ደም እየፈሰሰ ነበር፣ ነገ ህይወቴ ይለወጣል፣ ነገ ጥሩ ቦታ እደርሳለሁ ያልኩት ልጅ መጨረሻው እንደዚህ ሲሆን በጣም ከፋኝ፣ ህይወቴን በምን መልኩ ነው የምቀጥለው፣ አይዞሽ የሚለኝ ሰው የለኝም። መጨረሻ ላይ የጎዳና ተዳዳሪ ሆንኩ” ማለቷንና ከተደፈረች በኋላ በማርገዟ ልጅ እንወለደች ገጠመኝ ባለችው ታሪኳ አመልክታለች። ታማሚ መሆኗን ጠቅሳ መደገፍና መለወጥ እንደምትፈልግ፣ ህይወቷ ድጋሚ እንዲለመልም ተስፋ የሚሰንቅላት ወገን እንደምትሻ ከንግግሯ ጠቅሰው ብርቱካን ከኢቢኤስ ጋር በነበራት ቆይታ አጋርተዋል።
ይህንኑ ዜና ተከትሎ መስቀለኛ ጥያቄ ያነሱ አካላት ኢንተርቪውን በዶክመንታሪ መልክ አሳምሮ ያቀረበውን ኢቢኤስ ” የጋዜጠኝነት ህ ሁ የሚባለውን ማመዛዘን የት ጣለው” ሲሉ፣ አለን የሚሉትን ማስረጃ በማከታተል እያወጡ እየሞገቱ ነው።

ትምህርት ቤቷን፣ ስሟን፣ ምስሏን፣ መታወቂያዋን፣ የቤተሰቦቿን ሁኔታ፣ የትዳር ባልደረባዋን ወዘተ በምስልና በማስረጃ አጅበው በማቅረብ ስህተት መሰራቱን የሚጠቁሙ ወገኖች ኢቢኤስ መከሰስ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የፕሬስ ህግም በመታሱ ሊቀጣና ለሌሎች መማሪያ እንዲደረግ የሚሉ ጥቂት አይደሉም። በሌላ በኩል ግን ጥፋቱን አርሞ ዘገባውን ሙሉ አድርጎ እንዲያቀርብ የተማጸኑም አሉ።