በሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ የተመራ ልዑክ ትላንት ወደ አማራ ክልል መዲና ባህርዳር ከተማ አቅንቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረገብት ወቅት ክልሉ ቀድሞ የተኩስ አቁም እንዲያውጅ ጥያቄ ማቅረብ ተገለጸ።
ሸገር እንደዘገበው ልዑኩ ወደ አማራ ክልል ያቀናውና ጥያቄውን ያቀረበው የአማራ ክልል የአጃንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በሚካሄድበት አስቻይ ሁኔታ ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር ለመነጋገር ነው።
ኮሚሽኑ ምክክሩን አካታች በሆነ ሁኔታ ማከናወን እንዲችል በማንኛውም አካባቢ በፖለቲካ ጉዳዮች ምክንያት የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት በራሱ በኩል እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም በሌሎች ላይም ግፊት እንዲያደርግ ልዑኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት ጥያቄ አቅርቧል ተብሏል፡፡
በክልሉ ያለው ግጭት ቆሞ አስቻይ የምክክር ሁኔታ እንዲኖር ራሱ የክልሉ መንግስት ” ተኩስ አቁሜአለሁ ” ብሎ በማወጅ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስድም ኮሚሽኑ ጠይቋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በክልሉ የሚያካሂደው የምክክር መድረክ እንዲሳካም ድጋፉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል ተብሏል፡፡
ምክክሩ አሳታፊና አካታች በሆነ አስቻይ ሁኔታ እንዲካሄድም ኮሚሽኑ ያቀረባቸው ጥያቄዎች በክልሉ መንግስት በኩል ተገቢው ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡