ቀመሩ ምን እንደኾነ የማይታወቅ ስሌት ትውልድን በልቷል፣ ተስፋን ቀምቷል፣ የዕውቀት በሮችን ዘግቷል፣ መምህራንን ከተማሪዎች ጋር አለያይቷል።
ሚሊዮኖች ያለ በደላቸው ከዕውቀት ብርሃን ተከልክለዋል፣ ቢሊዮን ብር የፈሰሰባቸው ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል። እልፍ አዕላፍ ተስፋዎች ተቀጭተዋል። ልጆች ዕድሜያቸውን ተሠርቀዋል። ወላጆች የድካማቸውን ፍሬ ተነፍገዋል።
ጠመኔ ጨብጠው ዕውቀትን እንስጥ ያሉ መምህራን ተሳድደዋል፣ ተገፍተዋል፣ ተዳፍተዋል፣ በአፈሙዝ ተስፈራርተዋል። ከማስፈራራት አልፈው ተገድለዋል። በአስከሬናቸው ላይም የድል አድራጊነት መዝሙር ተዘምሮባቸዋል። ተፎክሮባቸዋል። ተሸልሎባቸዋል። መምህራንን መግደል እንደ ጀግንነት፣ ትምህርትን ማቋረጥ እንደ አርበኝነት፣ የተማሪዎችን ዕድሜ መስረቅ እንደ ትውልድ ተቆርቋሪነት ታይቷል።
ትምህርት ቤቶች ይከፈቱ ያሉ ሁሉ እንደ ባንዳ ተቆጥረዋል፣ እንደ አብዮት አደናቃፊ ታይተዋል፣ መምህራንን አትንኩ ያሉት ሁሉ ከእኛ ወገን አይደላችሁም ተብለው በጠላትነት ተፈርጀዋል። ከመንጋው ተለይተው ተገፍተዋል። በዱር በገደል ተሳድደዋል። የሞት መልዕክተኛ ተልኮባቸዋል። በተገኙበት ሁሉ ይገደሉ ተብሎ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል። የተገኙትም ተገድለዋል። ያልተገኙትም በየቀኑ የግድያ ዛቻ ይደርስባቸዋል።
ትምህርት ቤቶችን አታፍርሱ፣ ተማሪዎችን አትንኩ ያሉትም የመከራን ቀንበር ተቀብለዋል። ልጆቻችን ይማሩ ተስፋቸውን አትንጠቁ ያሉ ወላጆች እንደ በደለኛ ተቆጥረዋል። ከጠላቶቻችን ወገን ናችሁ ተብለዋል።
መምህራን ከተማሪዎቻቸው ፊት እየታፈኑ ታግተዋል፣ ከተማሪዎቻቸው ፊት ተንበርክከው ተገርፈዋል፣ በየአደባባዩ እየተዞሩ ወደ ትምህርት ቤት አንመጣም፣ ትምህርት አያስፈልግም እያላችሁ ልፈፉ ተብለዋል። በተከበሩበት ምድር ተቀጥተዋል። ከክብራቸው እንዲዋረዱ ተደርገዋል።
ትምህርት ቤቶችን የዘጉ ደግሞ እንደ ሕልውና ታጋይ ተቆጥረዋል። ተማሪዎችን ከትምህርት ቤት ያራቁ እንደ ጀብደኛ ታይተዋል። መምህራንን የገደሉ ደግሞ እንደ ጦር ሜዳ ጀግና ተሞግሰዋል። ተወድሰዋል።
ማን ይሙት! ትውልድን የገደለ ወይስ ትውልድን ላድን ያለ ነው ጀግና ተብሎ መሸለም የነበረበት? በዕውቀት ብርሃን ላመላልስ ያለ ነው ወይስ በዚህ ዘመን ወደ ጨለማ የሚመልስ ነው እንደ ጀብደኛ መታየት ያለበት? ትግሉ ምንድን ነው? ሚሊዮኖችን የአቡጊዳ ጀግና ማድረግ ወይስ ተወዳዳሪ እንዳይኾኑ አድርጎ ወደኋላ መመለስ?
ዓለም ላወቁት እንጂ ከዕውቀት ለራቁት ቦታ የላትም። ዓለም ለሠለጠኑት እንጂ በጨለማ ውስጥ ለሚመላለሱት አትመችም። የነጻነት ብርሃን በተባለች፣ የዕውቀት፣ የጥበብ፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የእሴት፣ የሥልጣኔ ቀንዲል በተሰኘች ሀገረ ኢትዮጵያ ከዕውቀት ጋር መጣላት፣ የዕውቀት አባቶችን መግደል ምን የሚሉት ትግል ነው? ምን የሚሉትስ ራዕይ ነው? ሀገርን በጨለማ በርኖስ መጠቅለል ወይስ ትውልድን ሳያሳውቁ መግደል?
በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። አደራችን እንወጣ ብለው ብዕር እና ጠመኔ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት የሄዱ መምህራን እየተገደሉ ነው። ዕውቀትን ፍለጋ ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑ ተማሪዎችም ማን ኑ አላችሁ እየተባሉ ተገርፈዋል። ተገፍተዋል።
ከሰሞኑም በሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ የዕውቀት አባት መምህራን ለምን አሥተማራችሁ ተብለው ተገድለዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ ታጣቂ ኀይሎች ወደ ከተማዋ ሠርገው በመግባት አራት መምህራንን እና ከስምንት ዓመታት በፊት የመራዊ ከተማ ከንቲባ የነበሩ አሁን ላይ በሌላ ሙያ የነበሩን ግለሰብ ገድለዋል ነው ያሉት። አንድ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አስተባባሪ ግለሰብን ደግሞ አግተው ወስደዋል።
የጸጥታ ኀይሉ በፍጥነት ባይደርስ ኖሮ በርካታ መምህራንን ለመግደል አስበው ወደ ከተማዋ መጥተው እንደነበር ነው ያነሱት። “አንደኛው መምህር ለማስተማር እየገባ ትምህርት ቤት በር ላይ ነው የገደሉት። ሌሎችን መምህራን እና የቀድሞውን ከንቲባ ደግሞ በየቤታቸው ሄደው ነው የገደሏቸው” ይላሉ። የታገተውን ግለሰብም ቤቱን ሰብረው ነው የወሰዱት ነው ያሉት።
“የተገደሉት መምህራን ጨዋ፣ በጣም ምሥጉን የሚባሉ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩ፣ ተማሪ የሚወዳቸው ናቸው። ይሄ ለንግግር አይደለም። ሐቅ ነው። የተገደሉበት ምክንያት ለምን አስተማራችሁ ነው፤ ሌላ ምንም ምክንያት የላቸውም። ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውግንናም የላቸውም፤ አንዳንዱ ከዚህም ከዛም የሚረገጥ አለ፤ እነዚህ ግን ገለልተኞች ናቸው” ይላሉ።
ታግቶ የተወሰደውም ለምን የማኅበረሰብ ጤና መድኀን ክፍያ አስከፈልክ ተብሎ ነው ሌላ ምክንያት የለውም ነው ያሉት። የቀድሞው ከንቲባም ከዓመታት በፊት ከኀላፊነታቸው የለቀቁ ። አሁን ላይ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎም ኾነ ውግንና የሌላቸው ሚዛናዊ የኾኑ ሰው ነበሩ ነው ያሉት።
በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎችን ወደ ትምህርት መመለሳቸውን ገልጸዋል። በርካታ ትምህርት ቤቶችም በመማር ማስተማር ሥራ ላይ ናቸው። በመራዊ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም ክፍት ናቸው። አሁን ላይ የተፈጸመው ድርጊት በተማሪዎች፣ በመምህራን እና አጠቃላይ በማኅበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል ነው ያሉት። እንዲህ ዓይነት ድርጊት መወገዝ አለበትም ብለዋል።
ትምህርት ከፖለቲካ ነጻ የኾነ፣ ሕጻናትን የሚገነባ ነው ያሉት ኀላፊው ትውልድን በሚያስቀጥል ተቋም ላይ ከፍተኛ ጫና እየደረሰ ነው ይላሉ። አሁንም ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች አሉ፣ የተከፈቱትንም ለመዝጋት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነውር ነው ብለዋል። በመምህራን ላይ የሚደርስ ግድያ በትውልዱ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ትውልድ የሚገድሉትን መቃወም አለበት፣ ከዚህ በላይ ዝም ማለት የለበትም፣ ማኅበረሰቡ እንዲፈራ፣ እንዲሸማቀቅ፣ አንገቱን እንዲደፋ ተደርጓል። ዝም ከተባለ ግን እያንዳንዱን የሚበላ በመኾኑ ከዚህ በላይ ዝምታ አያስፈልግም ይላሉ። በግልጽ መቃወም እና በቃችሁ ማለት ይገባል ነው ያሉት።
ለጸጥታ ኀይሎች መረጃ በመስጠት እና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል። የጸጥታ ኀይሉ የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ እና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የታጠቁ ኀይሎች እያደረጉት ያለው ድርጊት ከወግ እና ባሕል ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ዘላቂ ቀውስ ተክሎ የሚሄድ፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያናጋ፣ ከአማራ ሕዝብ ሥነ ልቦና ጋር አብሮ የማይሄድ ነው ብለዋል። ይሄን ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፣ ማኅበረሰቡ ድርጊቱን ማውገዝ እና ተው ማለት አለበት ነው ያሉት።
የተማረ ዜጋ በሌለበት የሠለጠነ ፖለቲካዊ ሃሳብ ማመንጨት፣ ማሰራጨት፣ ማስረጽ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማፍለቅ እና በሠለጠነ ሃሳብ ላይ የሚመሠረት እንዲኾን ማድረግ አይቻልም ብለዋል።
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለአማራ ሕዝብ መብት እታገላለሁ የሚል እና በተግባር ግን ያልኾነ ኀይል ትውልዱ ድንቁርና ውስጥ እንዲኾን እና ክልሉ ከሌሎች ክልሎች ጋር ተወዳዳሪ እንዳይኾን አድርጓል ማለቱ ይታወሳል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ መምህራን እና የትምህርት ቤት መሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አልተቻላቸውም፤ ይህም በመኾኑ የአማራ ክልል የትውልድ ቅብብሎሽን የሚገታ ታላቅ ስብራት ገጥሞታል።
ይህን ስብራት ለመጠገን እና ለዘመናት የሚቆይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ ሕዝብ የጽንፈኛውን ጸረ ትምህርት አቋም በመታገል ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልክ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።
ነገር ግን አሁንም የመምህራን ግድያ አልቆመም። ተማሪዎችንም ወደ ትምህርት እንዳይመጡ መከልከሉ ቀጥሏል፤ ግን አስከመቼ ነው ይህ ድርጊት የሚቀጥለው? መቋጫውስ መቼ ነው? ግቡስ ምን ይኾን?
አሚኮ