“የጊዜያዊ አስተዳደሩን ተግባር በብቃት መወጣት፣ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ይችላሉ ብላችሁ የምታምኑት እጩዎች ከዛሬ ጀምሮ ጠቁሙኝ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለትግራይ ሕዝብ ጥሪ አቀረቡ። “የትብብር ትግል እንዴት ይካሄድ” በሚሊል ርዕስ አቅጣጫ የማስያዝ ስራ እየሰራ ያለው ርዕዮት ሚዲያ ባለቤት ቴዎድሮስ ጸጋዬ አብይ አሕመድ ፕሬዚዳንት ለመሾም ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ታማኝ ምንጮች እንደነገሩት ገልጾ ማምሻውን ሰፊ ትንተና ሲሰጥ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ይድረስ ለትግራይ ሕዝብ” ሲሉ በግል የማህበራዊ ገጻቸው ባሰራጩት ጥሪ ሕዝቡ በነጻነት ጥቆማ እንዲሰጥ አበረታተዋል።
በቀጥታ ጥቆማ የሚሰጥበትን የኢሜል አድራሻ info@pmo.gov.et በማስቀመጥ ለትግራይ ሕዝብ በቀርበው ጥሪ ላይ የህግ አግባቡ የሚፈቅደው እንደሚከናወን ለማስጨበጥ ደንቦችና አሳሪ ህጎች ተጠቅሰዋል።
“እንደሚታወቀው በፌዴራል ሕገ መንግሥት 62(9) መሠረት፣ በፕሪቶሪያ ስምምነትና አዋጅ ቁጥር 359/1995 የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ እንዲገባ፣ አሳታፊ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ይደነግጋል፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 533/2 ነው” በሚል የህግ ጥያቄ ለሚያነሱም ሆነ መረጃው ለሌላቸው እንዲያምች ህጋዊ አግባቡ ተዘርዝሯል።
በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 15(3) መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቆየው ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው። ነገር ግን ትክክለኛ ምክንያት ካለ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችል ያስታወሱት አብይ አሕመድ፣ ከላይ በተጠቀሱት ህጎች እና በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጊዜያዊ የአስተዳደር ስራውን አጠናቆ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ህዝብ ለመረጠው መንግስት ኃላፊነቱን ማስረከብ እንደነበረበት አመልክተዋል።
“ነገር ግን” ይላል በትግርኛ ቋንቋ ለትግራይ ሕዝብ የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ቁልፍ ተግባራቶቹን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን አልቻለም። አንዱ ቁልፍ ተግባር ለምርጫ ሁኔታዎችን መፍጠር ነበር። እንዲህ ያሉትን ያልተጠናቀቁ ተግባራት ለማጠናቀቅ ይቻል ዘንድ ህጉን በማሻሻል የጊዜያዊ የክልሉን የሽግግር አስተዳደር የስልጣን ጊዜን በአንድ ዓመት ማራዘም አስፈላጊ መሆኑ ጭብጥ በማስቀመጥ ያስረዳል።
የፌደራል መንግስት የጊዜያዊ መንግስቱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም በጥሪው ተካቷል።
በቁጥር 533/2015 አንቀጽ 3(2) መሰረት የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሹመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነትና ስልጣን እንደሆነ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ምንም እንኳን ሹመት የመስጠቱ ስልጣን በህግ የእሳቸው ቢሆንም ” የጊዜያዊ አስተዳደርን ተግባር በብቃት በመወጣት፣ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ይችላሉ ብላችሁ የምታምኑትን እጩ ከዛሬ ጀምሮ info@pmo.gov.et በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኢሜል መላክ ትችላላችሁ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ትህነግ ወደ ትግራይ ጓዙን ጠቅልሎ ከሄደ በሁዋላ፣ ሰፊ ኃይል አደራጅቶ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ከተጀመረው ጦርነት በሁዋላ የተለያዩ መሪዎች ትግራይን እንዲያስተዳደሩ ቢመደቡም የተፈለገው ውጤት ሊገኝ
አልቻለም።በተለይ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በሁዋላ ትግራይን እንዲመሩ የተመደቡት የጦርነቱ ወቅት አፈ ቀላጤ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በትህነግ ውስጥ በተፈጠረ መሰንጠቅ ሳቢያ መስራት ተስኗቸው ቢሯቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በርካታ ሚስጢሮችን ይፋ ያደረጉት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።
“ትህነግ – ዲ” የሚባለውና በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን በትግራይ ሰራዊት የተወሰኑ አመራሮች ስለሚደገፍ የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር በኃይል በማፍረስ ቁልፍና ማህተም መረከቡን ተከትሎ የትግራይ ወጣቶች ተቃውሞ ማሰማታቸው፣ ይህ ሲሆን ታጣቂዎቹ ተኩሰው መግደላቸና ማቁሰላቸው፣ እንዲሁም በርካቶችን ማሰራቸው አፍቃሪ ትህነግ በሆኑ ሚዲያዎች ሳይቀር በቪዲዮ መረጃ ተደግፎ መዘገቡ ይታወሳል።
ይህንኑ ተከትሎ በተደጋጋሚ በተካሄደ ውይይት በትግራይ አዲስ የሽግግር አስተዳደር ለማቋቋም ስምምነት መደረሱን የዘገቡ አንዳንድ ሚዲያዎች ” ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ፕሬዚዳንት ሆኑ” በሚል ምንጮች እየጠቀሱ ሲዘግቡ ሰንበተዋል።
የርዕዮቱ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በትግራይ ብሄርተኝነት ስሜትና ቅኝት መነጽርና ድንበር አበጅቶ በሚመራው የግሉ ሚዲያው በትናንትናው ዕለት ለአንድ ሰዓት ከሃያ አራት ደቂቃ ብቻውን ባሰራጨው የግል ትንተናው፣ ስለ አዲሱ ፕሬዚዳንት ስያሜ የሰጠው መረጃ የተለየ ነበር።
” አብይን ለማስወገድ የሚደረግ ጥምረትን እንደግፋለሁ” የሚለው ቴዎድሮስ የትህነግ አመራሮች ቅድሚያ አንድነት መፍጠርና በጥምረቱ የበላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ግን ዋና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል።
ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ለረዥም ሰዓት ባቀረበው የብቻው ዲስኩር፣ አዲሱን ሹመት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን መረጃ እንዳለው ጠቅሶ ሲዘረዝር ተሰምቷል።
በዚሁ ዝርዝር ትንተናው ውስጥ አብይ አሕመድ የአገር መከላከያ በትግራይ ክልል ባሉ ካምፖቹ ተመልሶ እንዲሰፍር መፍቀድ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል አንዱና ዋናው እንደሆነ አመልክቷል።
ይህ በተላለፈ ሰዓታት ውስጥ አብይ አሕመድ “የትግራይ ሕዝብ ሆይ የትግራይን ሰላም የሚያስጠብቅ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራ ይሰራሉ ብለህ የምታስባቸውን እጩዎች ጠቁም” የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።