ልብ ላለው የዋጋ መናሩ ጉዳይ ሳይሆን ዋጋው የናረበት አግባብ ራስ ያማል። አንድ 12 ብር ከመኪና ላይ የሚገዛ ውሃ በአንድ መቶ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ከ25 ብር እስከ 100 ብር ይሸጣል። በተመሳሳይ በዚሁ ራድየስ ውስጥ ሽሮ ከ300 ብር እክሰ 1600 ብር መልኩ ላይ ማጭበርበሪያ እየተበጀለት ይሸጣል። እንዲህ ያለ አንድ አካባቢ ላይ ያለ የዋጋ መዛባት ምን የሚሉት ምድራዊ ምክንት ይቀርበበታል?
በአጭሩ አብዘኞቹ ነጋዴዎች ይሉንታ ቢስ፣ ህዝብን ከአጥንቱ ላይ የሚግጡ ሆነዋል። ተቆጣጣሪዎቹ ደግሞ በሌብነት የተጨማለቁ፣ ከሕዝብ አጥንት ላይ ተግጦ ከተገኘው የሚካፈሉ ጅቦች ሆነዋል። በመሆኑም ህዝብ አጥንቱ ድረስ ዘለቀው በሚግጡት ነጋዴዎች ሲደማ አይታያቸውም። ቀናዎች ቢኖሩም ሌቦቹ ስለሚበዙ ሚናቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለሁሉም በኩር ጋዜጣ ከስር ያለውን አስፍሯል።
የገበያ አለመረጋጋት እና የኑሮ ውድነት አሁንም የዜጎች ፈተና ሆኖ ቀጥሏል:: እንደ ሀገር በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች በቀጠሉበት እና በነጻነት ተንቀሳቅሶ በመሥራት ግለሰባዊ ገቢን ለመጨመር ባልተቻለበት ነባራዊ ሁኔታ በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ያጋጠመው የዋጋ መናር ችግሩን አባብሶታል::
ለመሆኑ የኑሮ ውድነት የዜጎች ፈተና ሆነ የሚባለው የምርቶች ወይም እቃዎች ዋጋ ጭማሪ ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው? የሚለውን ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ መመልከት ተገቢ ነው:: የዋጋ ንረት የእቃዎች፣ የምርቶች ወይም የአገልግሎቶች ዋጋ ከሚፈለገው በላይ ሲጨምር እና ይህንንም ተከትሎ የገንዘብ የመግዛት አቅም ሲዳከም የሚከሰት የመኖር ህልውና ፈተና መሆኑን ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳዮችን በፌስቡክ እና ዩቱዩብ ገጾች ጥልቅ ትንታኔ የሚያደርገው የ‘ኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ቪው’ ሀተታ ይጠቁማል::
የፍላጎት መናር፣ የማምረቻ ወጪ መጨመር፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ደግሞ ለዋጋ ንረት መነሻ ምክንያቶች ናቸው:: እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የዋጋ ንረት መንስኤዎች ሰው ሠራሽ በሆኑ ምክንያቶች ሲባባሱ ችግሩ የዜጎች ፈተና ይሆናል:: ለአብነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ተጠቃሽ ነው:: ይህም አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዳያመርቱ፣ ያመረቱትንም ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ በማድረግ የምርት አቅርቦት ለፈጠረው የኑሮ ውድነት ይዳርጋል:: በተጨማሪም ሕገ ወጥ ደላላዎችን መቆጣጠር አለመቻል፣ ዓለም ዓቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የአንበጣ መንጋ እና የሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት መሠረቶች ሆነው ተነስተዋል::
እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ቪው መረጃ በእነዚህ ምክንያቶች እየተፈጠረ ያለው የኑሮ ውድነት በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል:: የዋጋ ግሽበት ምጣኔው በዓመት ከሦስት በመቶ ሳይበልጥ በዝግታ እየጨመረ ከሄድ የአምራች ክፍሉን የሚያበረታታ ጤነኛ የዋጋ ንረት ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሎ ይታመናል:: ጤነኛ የነበረው የዋጋ መጨመር በሂደት ከፍ እያለ በዓመት እስከ ዘጠኝ በመቶ በዝግመት መጨመር ሲጀምር የዋጋ ግሽበት ጥንቃቄ ወደ ሚፈልግበት ደረጃ ላይ ለመድረሱ ጠቋሚ ነው::
የዋጋ ንረት የመጨረሻ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ እና ኢኮኖሚውን በሚያሽመደምድ ደረጃ ላይ ደረሰ የሚባለው ደግሞ የምርት፣ የቁሳቁስም ሆነ የአገልግሎት ዋጋ አማካይ ጭማሪ ከ20 በመቶ እስከ እጥፍ ደረጃ ሲደርስ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ቪው ትንታኔ ያሳያል::
አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን የዋጋ ንረት መሠረት አድርጎ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃው እስከ ፈረንጆቹ 2025 አጋማሽ የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት 25 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ማስታወቁ አይዘነጋም:: ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሳው መንግሥት በነዳጅ ዘርፍ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ ነው::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛው ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ2016 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ከነበረበት 29 ከመቶ በ2017 ዓ.ም ወደ 15 ከመቶ መውረዱን ገልጸዋል::
ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ በምርቶች ላይ የተፈጠረው የዋጋ መጨመርም ሸማቹን አነጋግሯል፤ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተጠይቋል:: ወይዘሮ አየሁ ጀምበሩ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የገበያ ቦታዎች ውስጥ አንዱ በሆነው እና በተለምዶ ኪዳነ ምህረት የገበያ መዳረሻ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ሸምተው ሲወጡ ነው ያገኘናቸው:: ባለ ሦስት ሊትር ዘይት አንጠልጥለዋል፤ ሌሎች አስቤዛዎችንም በፌስታል ቆጣጥረዋል:: ገበያው እንዴት ነው? ስንል ጠየቅናቸው:: “ከአትክልት እና ፍራፍሬ ጀምሮ ሁሉም ምርቶች ገበያው ከነበረበት ይበልጥ ሊረጋጋ እንደሚችል ተስፋን ሰጥቶን የነበረ ቢሆንም በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ የአብዛኛዎቹ ምርቶች ዋጋ እጥፍ በሚባል ደረጃ ጨምሯል” በማለት ተናግረዋል::
“እኔ ከአሁን ቀደም አምስት ሊትር ዘይት ነበር የምጠቀም፣ የዛሬው ዋጋ ግን ያለኝን አብቃቅቼ እንድጠቀም ወደ ሦስት ሊትር አወረደኝ:: እስከ 700 ብር ይሸጥ የነበረውን ባለ ሦስት ሊትር ዘይት አሁን ላይ አንድ ሺህ ብር ገዛሁት፣ ባለ አምስቱ እስከ አንድ ሺህ 700 ብር እየተሸጠ ነው:: የሽሮ ክክ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዴት ከ60 ብር በላይ ይጨምራል!? ምስር 300 ብር እንዴት ይሸጣል!?… ብቻ ሁሉም ነገር እንቆቅልሽ ሆኖብናል!” በማለት የኑሮ ውድነቱ ያሳደረባቸውን ጫና ተናግረዋል::
ለጊዜው ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላዋ ሸማችም “ገበያው ተቆጣጣሪ አጥቷል!” ሲሉ በማሳያ ያስረዳሉ:: “ከቤት ቁጭ ብዬ እያለ ስልኬ ጮኸ፤ ደዋዩ በንግድ ሥራ የተሠማራ ነው፤ ስልኩን ሳነሳው የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ሊጨምር እንደሆነ እና በፍጥነት እንድሸምት ተነገረኝ:: እኔም ሌላውን ሥራዬን በይደር ትቼ ከወር በላይ የሚያቆየኝን አስቤዛ ሸመትኩ:: በሰዓታት ውስጥ የገዛኋቸው ሁሉም ምርቶች ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨመረ” በማለት አስታውሰዋል::
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገዢ እና ሻጭን ለማገናኘት ያለመ ውይይት ባካሄደበት ወቅት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የዘይት ፋብሪካዎች እንደሚገኙ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል:: እነዚህ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ የገቡትም ከመንግሥት ቦታ በነጻ ወስደው፣ የፋብሪካ መሳሪያዎችንም ከቀረጥ ነጻ አስገብተው፣ የጥሬ እቃ ግብዓት ማምረቻ የእርሻ ቦታዎች ተሰጥቷቸው እንደሆነ ገልጸዋል:: ይሁን እንጂ የዘይት ፋብሪካዎችም ሆኑ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ከመንግሥት የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ ዋጋ ምርቶቻቸውን እያቀረቡ እንዳልሆነ አንስተዋል::
አንዳንድ ያደጉ ሀገራት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁመው ከራሳቸው ሕዝብ አልፈው የሌሎች ሀገራትን ሕዝብ ሲደግፉ እንደሚታዩ አንድ የውይይቱ ተሳታፊ በትዝብት ጠቁመዋል:: ዛሬ አማራ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ ፍጹም የተቃረነ ነው:: “አንድ የመንግሥት ሠራተኛ እንዴት አምስት ሊትር ዘይት አንድ ሺህ 700 ብር እንዲገዛ ይወሰንበታል?” ሲሉ ነጋዴዎች አሁንም የሕዝብን የመግዛት አቅም ባገናዘበ ዋጋ ምርቶችን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል::
የደላላ ጣልቃ ገብነትን በማስወጣት ቀጥታ ከፋብሪካው ጋር በማገናኘት ምርቶችን ለሸማቹ ማቅረብ ከችግሩ መውጫ መንገድ ሆኖ ተጠቁሟል:: የግብይት ሥርዓቱም በደረሰኝ እንዲከናወን ማድረግ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ዋና መንገድ ሆኖ እንዲሠራበት ተጠይቋል::
በውይይቱ ወቅት የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብል እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ግብይት ዳይሬክተር ልንገረው አበሻ በበኩላቸው በሰብል ምርቶች ግብይት ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ጭማሪ ምንጩ የማምረቻ ወጪዎች መናር ነው ብለዋል:: በወቅታዊ የጸጥታ ችግሩ ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ የምርት ዝውውር አለመኖር የአቅርቦት ውስንነት ለፈጠረው የዋጋ መናር ተጨማሪ ችግር አድርገው አንስተዋል::
የሚመረተው ምርት በጥራት ሸማችን የሚያረካ አለመሆን፣ አቅርቦት እና ፍላጎትን ዓመቱን ሙሉ አጣጥሞ ለማስቀጠል በዓመት አንዴ የሚመረተውን የግብርና ምርቶች ለረዥም ጊዜ ሊያቆይ የሚችል ዘመናዊ መጋዝኖች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖርን በተግዳሮትነት አንስተዋል:: ይህንን ችግር ለመፍታት የግብይት ማዕከላት ግንባታ ጅምሮች መኖራቸውን አመላክተዋል::
የዋጋ ንረት በተከሰተ ጊዜ ገበያውን ለማረጋጋት ምርትን በስፋት ለሸማቹ በቀጥታ ለሚያቀርቡ ጅምላ ነጋዴዎች በተለያዩ ከተሞች ጊዜያዊ ሸዶችን የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል:: አንዳንድ ከተሞች ገበያ ለማረጋጋት ጥረት የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲደግፉ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ያለማበረታታት ሁኔታዎች መኖራቸውን ቢሮው ማረጋገጡን አስታውቀዋል::
የግብይት እሴት ሰንሰለቱን ጠብቆ ምርት ቀጥታ ከሸማቹ እንዳይደርስ የሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል:: በተለይ ምንም ፈቃድ ሳይኖራቸው ከአርሶ አደሩ ምርት የሚሰበስቡ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች መኖራቸው ተመላክቷል::
በገጠሩ አካባቢ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ ንግድ ሥራ ለመቆጣጠር የተደራሽነት ችግር ቢኖርም በከተሞች አካባቢ ያለውን የንግድ ሥርዓት ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ እየተሠራ ነው:: ዳይሬክተሩ ማሳያ አድርገው ያነሱት በተለይ በዘይት ምርት ላይ ተመሳጥረው ዋጋ በጨመሩ ነጋዴዎች ላይ ሱቅን እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል::
በአምራች እና ሸማች መካከል ያለውን ደላላ በማስቀረት ግብይቱን ጤናማ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ሥራ መሆኑን ያስታወቁት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አትክልት አሳቤ ናቸው:: የዋጋ መናር በአብዛኛው ይበልጥ ተጎጂ የሚያደርገው ደመወዝተኛውን እና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ነው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ ለዚህም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለማኅበራት መተላለፉን አስታውቀዋል::
የዋጋ ንረትን በዘላቂነት በመከላከል የኑሮ ውድነት የዜጎች ፈተና እንዳይሆን ለማድረግ የሰላም ሁኔታው እንዲረጋጋ ማድረግ ይገባል ብለዋል:: የገበያ ማዕከላት መገንባት፣ ከእሁድ ገበያዎች በተጨማሪ አማራጭ ገበያን ማስፋት፣ ሕገ ወጥነትን በዘላቂነት መከላከል እና የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋት ላይ አተኩሮ በመሠራት መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል::
በአጠቃላይ የተረጋጋ ኑሮን ለመፍጠር ለወቅታዊ ሰላም እና መረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል:: የተረጋጋ ሰላም ያልተገባ ስጋትን ያስወግዳል:: ይህም ለነገ በመፍራት ዛሬ ላይ የሚኖርን ፍላጎት በልኩ በማድረግ ጤናማ ግብይት እንዲኖር ያደርጋል:: የተረጋጋ ሰላም ምርት አቅራቢዎች ያለ ስጋት ምርትን በሚፈለገው መጠን በሚፈለገው ቦታ በማድረስ የተረጋጋ ገበያ እንዲፈጠር ያደርጋል::
የተረጋጋ ሰላም ክትትል እና ቁጥጥር እንዲጠናከር በማድረግ በሕገ ወጥነት ግብይት ሊጎዳ የሚችለውን ሸማች ለመታደግም ፋይዳው የጎላ ነው:: በመሆኑም አሁናዊ የሰላም ሁኔታው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሁሉም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ) ከአሚኮ የተወሰደ