ከለውጡ ማግስት ተበትኖና አፈር ለብሶ የነበረውን አየር ኃይሏን ዳግም ያደራጀችው ኢትዮጵያ ድሮን ማምረት መጀመሯን ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኗን የኢትዮሪቪው የመረጃ ሰዎች አመለከቱ።
እንደ መረጃ ሰዎቹ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሮጌ ተዋጊ ጀቶችን ከማዝመንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ከማድረግ ጎን ለጎን ድሮን ለማመረት በያዘው ዕቅድ መሰረት ያለፉት ሁለት ዓመታት በስፋት ሰርቷል። በዚሁ መሰረት መንግስት ይህንኑ የድሮን ማምረት ብስራት ይፋ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ድሮን ለሌሎች አገራት መሸጥ እንደሚጀመርም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በፓርላማ ሪፖርታቸው ኢትዮጵያ ከውጭ የምትገዛቸውን አብዛኛ መሳሪያዎች በአገር ውስጥ ማምረት መጀመሯን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአምቦ ወደ ጉደር በሚወስደው መንገድ ደጋፊሌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ላይ ወደ ቀኝ ታጥፎ በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም የተገነባው የሆሚቾ ኦሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን ተተኳሽ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ማምረት መጀመሩ በሳምንቱ መጀመሪያ ተገልጿል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እንዳስታወቀው የሆማቾ ኦሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የተላያዩ ዓይነት ተተኳሾችን በማምረት የተቋቋመበትን ዓላማ በማሣካት ላይ የሚገኝ ኢንዱስትሪ ሆኗል። ኢንዱስትሪው አሁን ላይ ከስምንት እጥፍ በላይ ተተኳሾችን ማምረት እንዲችል ሆኖ ተገንብቷል።
አዲስ የተገነቡ የቀላልና የከባድ መሣሪያ ተተኳሽ ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም በከፍተኛ አመራሮች ተጎብኝቶ ሥራ መጀመሩን የኢንዱስትሪው ሥራ አሥኪያጂ ኮሎኔል ስለሽ ነገራ ተናግረዋል።
በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜ አጠቃላይ የፕሮጀክት ሥራው ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት የቻለው የቀላል እና የከባድ መሣሪያ ተተኳሽ ማምረቻ ፋብሪካ ከተጠበቀው በላይ ዕድገት ማሥመዝገብ ያሥቻለበት ዋናው ምክንያት የኢንዱስትሪው አመራር እና አባላት በመናበብ ቀን ከሌሊት በመሥራታቸው ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማመሥገናቸውን ኮሎኔል ስለሽ አሥረድተዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው በአካል በመገኘት አቅጣጫ በመሥጠት ሙያተኛውን በማበረታታት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አድረገው የፕሮጀክቱ ውጤት እዚህ በመድረሱ ኮሎኔል ሥለሽ ምስጋና አቅርበውላቸዋል።
የኢንዱስትሪው አመራሮች ሙያተኞች ከውጪ ተሞክሮዎችን በማምጣት ሥልጠና በመሥጠት ያለ መታከት ቀን ከሌሊት በመሥራት የተገኘ የጋራ ውጤት በመሆኑ ለእኔ የህይወቴ ስኬት ነው ብለዋለሰ ዋና ሥራ አሥኪያጁ ኮሎኔል ስለሽ ነገራ።
የሆሚቾ የቀላልና የከበድ መሣሪያ ጥይት ማምረቻ ፋብሪካን ዘመኑ በደረሰበት የዲጂታል ሥርዓት ውስጥ በማስገባት፤ ለከባድ፣ ቀላልና መካከለኛ መሣሪያ ተተኳሾችን ማምረት የተጀመረ ሲሆን ከሀገሪቱ የአቅርቦት ፍላጎት በላይ የውጭ ገበያንና ትውልድን ታሳቢ ተደርጎ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከጉብኘቱ በሁዋላ ኢትዮጵያ ተተኳሽ መሳሪያዎችን ከውጭ መግዛት ማቆሟን ገልጸው ምርቱ ለውጭ ገበያም እንደሚውል አስታውቀዋል።
ፋብሪካውን ከጎበኙ በሁውላ ከፋብሪካው መገንጠያ እስከ ጉደር ከተማ አርሶ አደሮችን ሰላም እያሉና እያነጋገሩ በእግራቸው ተጉዘዋል። በአምቦ ከተማ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተማዋን በእግራቸው በመዘዋወር ተመልክተዋል። ከሕዝብ ጋርም ተቀራርበው ሰላምታ ሲለዋወጡና ፎቶ ሲነሱ ውለዋል። ለተደረገላቸው አቀባበልም የአምቦን ህዝብ አመስነዋል።
ለትክከለኛ መረጃ በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk በኢሜል ሰብስክራይብ ያድርጉ