ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪን ሲመርቁ “ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገር ውስጥ ድሮን የማይታሰብ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። አሁን ግን ነገሩ ተቀይሮ ኢትዮጵያ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ። ጸረ ድሮኖችን ማምረቷን አብስረዋል። ድሮኖቹ በግዳጅ ላይ የሚታጠቁት የአገር ውስጥ ተተኳሾች ሲሆን በግዳጅ ላይ ጸረ ለጥቃት የሚመጣን ድሮን የሚጥሉበት ጸር ድሮን አቅም አላቸው።
ኢትዮጵያ ድሮን አምርቶ ከመጠቀም ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መገንባቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲያስታውቁ “ምርቱ ብዙ ስለሆነ የድሮን ገበያ ላይ መረባረባረብ አለብን” ብለዋል።
” ከዚህ ቀደም ገዝተን ከታጠቅናቸው ድሮኖች የሚለያቸው በከፍተኛ altitude መብረር መቻላቸው፣ በAI የታገዙ በመሆናቸው redundant communication system ያላቸው መሆናቸው ፣ Anti Drone Jammer ስላላቸው ነው ” – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)
“ብዙ ዓይነት አገልግሎት የሚሰጡ ድሮኖችን በራሳችን ባለሙያዎች ዲዛይን አድርጎ የማምረት አቅም ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው” ያሉት አብይ አሕመድ “ትንንሽ አቅም ይዘው ውጊያ ለሚያስቡ ኃይሎች የማሰቢያ ጊዜ ይሰጣል” በማለት እግረመንገዳቸውን ምክር ለግሰዋል።
“እንደ ድሮው አንለምንም፣ አንገዛም፣ ምርቱ ብዙ ነው፤ እናባዛለን” በማለት በድሮን ምርት ራስን መቻል ያለውን ፋይዳ ያስታወቁት አብይ አህመድ፣ ተረት ይመስል የነበረው ጉዳይ ዛሬ እውን በመሆኑ መላው ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ደስ ያለን ብለዋል። አያይዘውም የድሮን ገበያውን መቀላቀል ላይ በስፋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሲቪልና ወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) የሚያመርተውን የስካይ ዊን ኢንዱስትሪን መርቀው ከመክፈታቸው ሁለት ቀን በፊት ኢትዮሪቪው ዜናውን አስቀድማ መስራቷ የሚታወስ ነው።
ኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ በጸጥታና ደኅንነት ዘርፍ በቴክኖሎጂ ራሷን ለመቻል የጀመረችው ጥረት አካል መሆኑን ያስታወቁት አብይ አሕመድ፣ ድሮኖቹ ጸብ ለሚጭሩ ጦርነትን የሚያሳጥር ትልቅ አቅም እንደሆነ አመልክተዋል። ኢንዱስትሪው የሚያመርታቸው ድሮኖች ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የመጠበቅ አቅሟን ይበልጥ የሚያሳድጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
ድሮኖቹ በከፍተኛ መልካዓ-ምድር ላይ በብቃት አገልግሎት የሚሰጡና ጸረ-ድሮን ጭምር የታጠቁ መሆናቸውንም ሲገልጹ አዲሶቹ ድሮኖች ለኢትዮጵያ አየር ንብረት ተስማሚ ሆነው መሰራታቸው ለሚሰጣቸው ግዳጅ ውጤታማነት ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህ መሆኑ ከዚህ ቀደም በግዚ ሲመጡ ከነበሩት በላይም ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቀሙም ጠቁመዋል።
ድሮኖቹ መረጃ ለመሰብሰብ፣ ለመከላከል አቅም እንዲሁም ለማጥቃት እንደሚውሉ ጠቅሰው፤ ኢንዱስትሪው ድሮኖችን ከኢትዮጵያ ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።
ይህን የእድገት ጅማሮ ለማዝለቅ ቀጣይነት ባለው የምርምር ሥራ ላይ፣ ገበያ በማስፋት ተግባር ላይ እና በሀገር ውስጥ የስማርት ሴንሰር ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
” ይህንና እንደ ሆሚቾ የተተኳሽ ኢንጂነሪንግ ፋብሪካ ያሉትን አቅሞቻችንን የምናሳድገው፤ ግጭትን ለማቀጣጠል አይደለም፤ ግጭትን ለማስቀረት እንጂ” ሲሉ በአጽንኦት የሰጡት አብይ አሕመድ፣ “ግጭትን በሚፈልጉ ተዋንያን ፊት ግጭትን ለማስቀረት የሚችል አቅም በመፍጠር ሰላም እና መረጋጋትን ለማፅናት ነው ፍላጎታችን” ሲሉ ትንኮሳ ለሚያስቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሁሉም ዓይነት መሳሪያዎች ተተኳሽችን ማምረቷን ይፋ ባደረገች ቀናት ልዩነት ድሮን ማምረቷን ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ ቀጣይ ትኩረቷ ምን ሊሆን እንደሚችል ሲጠቁሙ ” ዋናው ዓላማ ግጭት ማስቀረት ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያ ትልቅ የሚባል የመከላከያ ኃይል ከገነባች በሁዋላ “ከዛስ” ለሚሉ ወገኖች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብረሃኑ ጁላ ” ኢትዮጵያን ከአሁን በሁዋላ መውረርም ሆነ መተንኮስ የሚችል የውጭ ኃይል የለም” ሲሉ በደፈናው የተናገሩት መልስ እንደሚሆን ተመልክቷል። ኢትዮጵያ ዝግጅቷ ታሪካዊ ጠላቶቿ የሚያደቡባትን ደባ ለማፍረስና ራሷን በደረጀ ኃይል ለመከላከል እንደሆነ የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ማስታወቃቸውን እዚህ ላይ ይነሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለ ሆምቾ ተተኳሽ ማምረቻ የሚከተሉትን ነጥቦች ማንሳታቸው ይታወሳል።
👉 በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ጥይቶችን የማምረት ሙከራዎች ቢኖሩም እስከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ድረስ ሀገራችን ከውጭ በማስገባት ላይ ተመስርታ ቆይታለች፡፡
👉 አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተተኳሽ ከማምረት አልፎ ወደውጭ የመላክ ዐቅም አሳድጋለች፡፡
👉 ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በመጠኗ፣ በታሪኳ እና በሀብቷ ልክ እራሷን ጠብቃ ለልጆቿ መሸጋገር መቻሏን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
👉 ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ ጥይት (መሣሪያዎች) የማምረት ሙከራዎች ነበሩ፤ እንደዚህ ዓይነት ስትራቴጂክ ዐቅሞች ኢትዮጵያ ካልገነባች በሆነ ጊዜ ማንም መጥቶ ጥቃት ሊፈጽምባት ይችላል የሚል ግምገማ ነበር፡፡
👉 በ2014 ጥይት እንገዛ ነበር፤ ይሁን እንጂ 2015 ላይ ፋብሪካውን መትከል ጀምረን አሁን ለምንገኝበት ደረጃ ደርሰናል፡፡
👉 ዛሬ ኢትዮጵያ ክላሽ፣ ብሬን፣ ስናይፐር፣ ዲሽቃ፣ ታንክ፣ ሁሉም ዓይነት መድፎች ከራሷ አልፎ ለገበያ በበቂ ሁኔታ የማቅረብ ዐቅም ገንብታለች፤ ፋብሪካው ዘመናዊ እና በሠዓት በጣም ከፍተኛ የማምረት ዐቅም አለው፡፡
👉 የፋብሪካው አጠቃላይ ግቢ እና የማምረት ዐቅሙ ኢትዮጵያን ይመጥናል፤ ሀገራችን እንደዚህ ዓይነት ዐቅም ሲኖራት ማየት በጣም ደስ ይላል፤ ያኮራል፡፡
👉 ክላሽ እና ስናይፐርን ጨምሮ ሌሎች መሣሪያዎችን እናመርታለን፤ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ከመግዛት ወጥተን ለሀገራት ለመሸጥ በመብቃታችን እና ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ይህ ዐቅም ተገንብቶ በማየቴ ከፍተኛ ክብር እና ደስታ ተሰምቶኛል፡፡
👉 ወታደር ነኝ ይገባኛል፤ በውትድርና አካባቢ የሚጎድሉ ነገሮች በኦፕሬሽን ጊዜ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆኑ እረዳለሁ፡፡
👉 አሁን ኢትዮጵያ ሥጋት የለባትም፤ ጭንቅላት ያላቸው ልጆች አሏት፣ ጀግና ወታደሮች አሏት፣ ከግብዓት አንጻርም የነበረባትን ውስንነት ከሞላ ጎደል ፈትታለች፡፡
👉 ልብስ፣ ጫማ፣ ጥይት፣ ክላሽ፣ ስናይፐር ለወታደሩ ከውጭ እናስገባ ነበር፤ አሁን በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን መከላከያ ልብሱን ያመርታል፣ ጫማ አምርቶ የሚያንሰውን ከሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ይቀበላል፡፡
👉 ኢትዮጵያ ለበርካታ ሀገራት ጥይት ለማቅረብ የሚያስችላትን ስምምነት (ውል) ፈጽማለች፡፡
👉 በሦስት ወራት ብቻ ከ30 ሚሊየን ያላነሰ ዶላር ሽያጭ ፈጽመናል፤ ይህም ማምረት እና መሸጥ ስለቻልን የተገኘ ውጤት ነው፡፡
👉 በወታደራዊ ዐቅም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው፤ በተለይ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ሴክተሮች አንዱ ኢንዱስትሪው ነው፡፡
👉 የመከላከያ ኢንዱስትሪ ብቻ ያመጣው ዕድገት በጣም ተስፋ ሰጭ እና ኢትዮጵያ በእውነትም እያንሠራራች መሆኗን ማሳያ ነው፡፡
👉 የጥይት ፋብሪካው ኢትዮጵያ ከሥጋት ወጥታ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች አምርታ እራሷን ለመከላከል ብሎም ለማሳደግ የሚያስችል ዐቅም እየፈጠረች ነው የሚለውን በደንብ ያሳያል፡፡
👉 ሀገር ሁል ጊዜም ቢሆን ማምረት የሚገባት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነሱም ምግብ፣ ልብስ እና መድኃኒት ናቸው፡፡ እነዚህን በበቂ ሁኔታ የማታመርት ሀገር ለማንኛውም አደጋ ትጋለጣለች፡፡
👉 በሁሉም መስክ ስመለከት በጣም ችግር የነበረ፤ በቀላሉ ልናሟላቸው የነበረ ነገሮች ምላሽ እያገኙ ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ተስፋ አላት፣ ኢትዮጵያ እያንሠራራች ነው፣ ኢትዮጵያ ጀምራ እየጨረሰች ነው፡፡
👉 በአንድ ዓመት ተኩል እና በሁለት ዓመት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት የራስን ፍላጎት ሸፍኖ ለውጪ ገበያ ማቅረብ የሚችል ኢንዱስትሪ ማየት በጣም ትልቅ ክብርና ኩራት ነው፡፡
👉 ለዚህ ሥራ የመከላከያ ሚኒስቴር አመራሮች፣ የኢንዱስትሪው ኃላፊዎች፣ በሺህ የሚቆጠሩ የአካባቢው ሠራተኞች ከፍተኛ ክብርና ምሥጋና ይባቸዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚስፈልጋትን ዐቅም ፈጥረዋል፤ ገዝተው ሳይሆን አምርተው፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚሸጥ ዐቅም ገንብተዋል፡፡ ለዚህም ኩራት እና ክብር ሊሰማቸው ይገባል፤ እኔም በበኩሌ እጅግ አድርጌ አመሠግናለሁ፤ ደስ የሚል ፍሬ ነው ያየነው፡፡
👉 በርቱ ይቀጥል፤ እንዳይቆም፤ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ስለሚገባት መርካት ሳይሆን ብዙ መጠማት እና መፈለግ ይገባል፤ ሠራተኞች እንዲመራመሩ እንዲሠሩ ይጠበቃል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለትክከለኛ መረጃ በቴሌግራም ይከተሉን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk በኢሜል ሰብስክራይብ ያድርጉ