የባሕር በር ጉዳይ የመጪውን ትውልድ የመኖር እና ያለመኖር ሁኔታ የሚወስን ስለሆነ ከወዲሁ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሃሳቡ ተስፋ ገለጹ፡፡
አቶ ሃሳቡ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሚያስተዳድራት በራሷ መንግሥት ድጋፍ አድራጊነት የነበራትን የባሕር በር እንድታጣ መደረጓ ሁሌም የሚያስቆጭ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ የባሕር በር ከሉዓላዊ ግዛትነቱም በላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጥቅሙ የሕልውና ጉዳይ ያደርገዋል፡፡
አንድ ሀገር የባሕር በር አለው ማለት ሌሎች የባሕር በር ካላቸው የዓለም ሀገራት ጋር ይዋሰናል ማለት ነው ያሉት መምህሩ፤ ይህ ደግሞ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የንግድ ልውውጥ እና ማኅበራዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ መምህር ሃሳቡ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ በዚያው ልክ ፍላጎቱና የንግድ እንቅስቃሴውም አድጓል፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩም ጨምሯል፡፡ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ቁጥር እና ፍላጎት አንጻር፤ የባሕር በር በተለይም የመጪውን ዘመን ትውልድ የመኖርና ያለመኖር ሁኔታ የሚወስን በመሆኑ ከወዲሁ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም የባሕር በሯን አሳልፋ የሰጠችበት ሁኔታ በአንገት ላይ ገመድ እንደማስገባት የሚቆጠር ነው ያሉት አቶ ሃሳቡ፤ ያ ጥፋት በተለይም በመጪው ትውልድ ላይ ትልቅ ዕዳን ያስከተለ ነው ብለዋል፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያ ብዙ ቢሊዮን ብር አውጥታ የማስፋፊያ ሥራ የሠራችበት የአሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ ይገባታል ብሎ ማስቀረት ሲቻል፤ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን መገንጠል እወቁልኝ ማለቱና ወደቡንም አሳልፎ መስጠቱ ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ስህተት ከመጪው ዘመን ትውልዶች ፍላጎትና ከዓለም የኢኮኖሚ ትስስር ጋር አብሮ ስለማይሄድ ከወዲሁ መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ የታሪክ ገጾች ላይ በዚህ ልክ የሀገሩን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ መንግሥታዊ ሥርዓት የለም ያሉት አቶ ሃሳቡ፤ አሁን መንግሥት እያቀረበ ያለው የባሕር በር ጥያቄ ተገቢነት ያለውና በተለይም ለመጪው ትውልድ ሕልውና ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡
ለኤርትራ መገንጠል የመጀመሪያውን እውቅና የሰጠችው ራሷ እናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ነች ያሉት አቶ ሃሳቡ፤ በወቅቱ ናይጄሪያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተቃውመው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ለኤርትራ መገንጠል እውቅና ይሠጥ ቢባል እንኳን ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ማድረግ ይቻል ነበር ነው ያሉት፡፡ ይህም ዘላቂ የሆነ ቀጣናዊ ሰላምን፣ ደኅንነትን፣ ኢኮኖሚያዊ እድገትንና ትብብርን ያጠናክር እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
‹‹በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት በ1940ዎቹ የኤርትራ ጉዳይ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ መነጋገሪያ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ነበር፤ በወቅቱ የኃያላኑ ሀገሮች ጉባዔ የኤርትራ ጉዳይ ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን በመለሰ መልኩ እልባት እንዲያገኝ ወስኗል። አንደኛ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ፤ ሁለተኛ የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት፤ ሦስተኛ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥን ግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ የተሰጠው ነበር፡፡ የ1983ቱ የሕወሓት ውሳኔ ያንን ታሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ውሳኔ የጣሰና ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር ያስቀረ፤ ቀጣናውንም ቋሚ አለመረጋጋት ውስጥ የከተተ ሆኗል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የባሕር በር ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ አሁንም ማንሳት የማይቻልበት ምክንያት ዝግ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሕግ ዋናው ማስፈጸሚያው ድርድር ነው ያሉት አቶ ሃሳቡ፤ አንዳንድ ሀገራት ይገባኛል የሚሏቸውን ግዛቶች በሰጥቶ መቀበል ወይም ይዘው መደራደር የተለመደ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው ላለመስጠት የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉም ብለዋል፡፡ ትራምፕ በግሪን ላንድና በፓናማ ላይ እያደረጉ ያሉት የይገባኛል ጥያቄ የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ያደረጉት መሆኑን መርሳት አያስፈልግም ነው ያሉት፡፡
አሜሪካ በግሪን ላንድና በፓናማ ከምታነሳው የይገባኛል ጥያቄ በላይ ኢትዮጵያ የምታነሳው የባሕር በር ጥያቄ ዓለም ከሚያውቀው ታሪካዊ ባለቤትነቷ በተጨማሪ በሌሎች መለኪያዎችም ቢታይ ሚዛን የሚደፋ ነው ብለዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄውን በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርሕ በዲፕሎማሲ መንገድ ማቅረብና ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መውሰድም ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የማደግ ተስፋ፣ ከሕዝብ ብዛቷ፣ ከታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነቷ በይበልጥም ከመጪው ትውልድ ፍላጎት አንጻር ኢትዮጵያ ሰላማዊ አማራጭን ተጠቅማ የመጪውን ትውልድ የባሕር በር ጥያቄ ከወዲሁ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡
via EPD