ሸጋው ጫኔ አንለይ፣ መሀመድ ሀምዛ ያሲን፣ አቤኔዘር ተስፋዬ በየነ እና ጌትነት ደምለው ዳምጤ የተባሉ ግለሰቦች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ደብረወርቅ ህንፃ አካባቢ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የቀድሞ የደምብ ልብስ የሚመስል በማሰፋት በጎዳና ንግድ ላይ የሚተዳደሩትን ግለሰቦች ንብረት በመበተንና በመደብደብ የቢሮውን ገፅታ በሚያንቋሽሽ መልኩ የሀሰት ቪዲዮ አዘጋጀተው በቲክቶክ ማሰራጨታቸውን ተከትሎ በቀረበባቸው አቤቱታ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ግለሰቦቹ በተቋሙ እና በሰራተኞቹ ላይ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር አስበው የተቋሙን የቀድሞ የደምብ ልብስ የሚመስል አዘጋጅተው ድርጊቱን መፈፀማቸውን ፖሊስ አስታውቋል፤ የፈፀሙት ድርጊት በህግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡
ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት በህግ የሚያስጠይቅ በመሆኑ መሰል ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ከህገ ወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
በቴሌግራም ያግኙን https://t.me/+f_kxmaPjD-9jYTdk