ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “እውነትን ይዘን፣ ሕግን ተከትለን በጋራ ሃሳብ አብረን መኖር እንችላለን” ሲሉ ለትግራይ ተወላጆች አስታወቁ። ነዚህ ዘመን ይህን ከማድረግ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደማይኖርም አመልክተዋል። አንዱ ሌላውን በኃይል አንበርክኮ መኖር የሚቻልበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይገባም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን “አብሮነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ከትግራይ ተወላጆች ጋር ውይይት መካሄዱን ጠቅሶ አሚኮ እንደዘገበው የትግራይ ተወላጆች ” ሰላም እንፈልጋለን። ጦርነት ሰልችቶናል” ብለዋል።
በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን አንድን ሕዝብ በኃይል አስገብሮ መኖር አይታሰብም ሲሉ ኮሎኔል ደመቀ ገልጸው፣ “የወልቃይት ሕዝብ ከዚህ በኋላ በህወሃት ጭካኔ እየታሰረ፣ እየተጎተተ እና እየተገደለ መኖርን ስለማይፈቅድ በመከባበር አብሮ መኖር የተሻለ አማራጭ ነው” እንደሆነ ጠቁመዋል። አስረድተዋል። ዜጎች ባሻቸው ስፍራ የመኖር መብትና በሚኖሩበት ሁሉ በዜግነታቸው እኩል ክብር ያሻቸዋል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የትግራይ ተወላጆች እኛ የምንፈልገው ሰላም እና አብሮ መኖርን ነው ብለዋል። ከጦርነት ያተረፍነው ብቸኛው ነገር እልቂት ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎች በደርግ ዘመነ መንግሥት ወደ ወልቃይት ጠገዴ እንደመጡ እና አካባቢው በወቅቱ በጎንደር ክፍለ ሀገር ይተዳደር እንደነበር ትውስታቸውን አንስተዋል።
“በዚያ ዘመን እንደማንኛውም ሰው በሰላም እንኖር ነበር” ያሉት ተሳታፊዎቹ ቀደም ሲል አካባቢውን የምናውቀው በበጌምድር ሲጠራ ነው ብለዋል። ደርግ ከለቀቀ እና ህወሃት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ነው ወደ ትግራይ የተካለለው ነው ያሉት። ወልቃይት ጠገዴ ድሮም ጎንደር በጌ ምድር ነበር፤ አሁንም ማንነቴ አማራ ነው ያለው፣ ማንነቱ መከበር አለበት ብለዋል።
ስም ሳንሰጣጥ እና ሳንፈራረጅ አብረን መኖር ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ የዞኑ አሥተዳደር ለትግራይ ተወላጆች የሚሰጠውን ክብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የቃብታ ሁመራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አታላይ ታፈረ ህወሃት ያመጣው ክፉ አስተሳሰብ የትግራይንም ኾነ የአማራን ሕዝብ ጎድቶታል ብለዋል። በዚህ ድርጅት እኩይ ሥራ ምክንያት ምንም የማያውቀው ሕዝብ ገፈት ቀማሽ ኾኗል ነው ያሉት። ከዚህ በኋላ ሁሉም በቃህ ሊለው ይገባል ብለዋል።
ባሳለፍነው ጦርነት በርካታ የትግራይ ወጣቶች ረግፈዋል፤ ወላጆቻቸው ያለ ጧሪ እንዲቀሩም ኾነዋል ነው ያሉት። አንድን ሕዝብ በጦርነት አዙሪት ውስጥ ማኖር በሕዝብ ነፍስ መቀለድ እንደኾነም ገልጸዋል።
የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ በላይ ፈለቀ ህወሃት የፈጸመውን ግፍ እና በደል በግልጽ ማውገዝ አለብን ብለዋል። ህወሃት የፈጸማቸውን በደሎች ሁላችን እናውቃለን፤ የተፈጸመውን በደል በመደበቅ ሰላም ማምጣት እና አብሮ መኖር አይቻልም ነው ያሉት።
አማራነት አቃፊነት ነው፤ የዚህ ማሳያው ደግሞ በሕዝብ ላይ ወንጀል ካልፈጸሙ የትግራይ ተወላጆች ጋር እንዲህ ተከባብረን መኖራችን ነው ብለዋል። ሁሉም ሰው የትም በነጻነት የመኖር መብት አለው እኛም ይሄንን እያደረግን እንገኛለን ነው ያሉት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ወልቃይት ጠገዴ በታሪክ የትግራይ አካል ኾኖ እንደማያውቅ አንስተዋል። ጉዳዩን በማድበስበስ እና የትግራይን ሕዝብ እና ወጣት ስሜት በመቀስቀስ አካባቢውን መልሰው የመያዝ ፍላጎት ያላቸው አካላት መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ሕዝብ ነቅቷል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ “እውነትን ይዘን፣ ሕግን ተከትለን በጋራ ሃሳብ አብረን መኖር እንችላለን” ብለዋል። ይሄ ካልኾነ ግን ከዚህ በኋላ አንዱ አንዱን በኃይል አንበርክኮ መኖር የሚቻልበት ሁኔታ አይኖርም ነው ያሉት።
በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን አንድን ሕዝብ በኃይል አስገብሮ መኖር አይታሰብም ብለዋል። የወልቃይት ሕዝብ ከዚህ በኋላ በህወሃት ጭካኔ እየታሰረ፣ እየተጎተተ እና እየተገደለ መኖርን ስለማይፈቅድ በመከባበር አብሮ መኖር የተሻለ አማራጭ መኾኑን ጠቁመዋል።
የእኛ ጥያቄ ያለ ደም መፋሰስ በሕግ አግባብ መልስ እንዲሰጠው ነውም ብለዋል። ህወሃትም ለዚህ ሃሳብ ፈቃደኛ ይኹን፤ እናንተ ነዋሪዎችም እውነትን በመደገፍ የግጭት እና የእልቂት ሃሳብን በመቃወም በሰላም አብሮ ለመኖር የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ልታበረክቱ ይገባል ነው ያሉት።