“አክትሟል” አሉ አብይ አሕመድ። ያለምንም ማጀቢያ ” የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄና ፍላጎት ሊደበቅ አይችልም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ይህ ፍትሃዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት የማይቀለበስና ያከተመለት ጉዳይ ነው። “ጦርነት አንፈልግም። አንድም ጥይት አንተኩስም። ትንኮሳ ካለ ግን ምላሹ የከፋ ነው። ምክኛቱም በቂ ዝግጅት የተደርገበት ጉዳይ ነውና ትንኮሳ እንዳይሞከር እመክራለሁ” ሲሉ ለኤርትራ ህዝብ ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ የኀልውና ጉዳይ ነው። ብልጽግና ኖረ አልኖረ፣ ይሄ ምክርቤት ኖረ-አልኖረ፣ የትውልዱ ቋሚ ጉዳይ ሆኖ ይቀጥላል።
በማርላማ ዲስኩራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል እንዳሉት የባህር በር ጉዳይ ህልውና ነው። ማንም ሊያስቆመው የሚችልም አይደለም። ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ጥያቄዋን ለማስፈጸም ጥይት ትተኩሳለች ማለት ዓይደለም።
ኢትዮሪቪው ከቀናት በፊት አንድ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊን ጠቅሳ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ኤርትራ ላይ አንዳችም ዓይነት ጦርነት የመክፈት እቅድ እንደሌላት መዘገባችን የሚታወስ ነው። ዛሬ አብይ አሕመድ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጥይት እንደማትተኩስ ሲያስታውቁ “የዓለም አገራት አነጋገሩን፣ አደራድሩን” ሲሉ በይፋ ጥሪ በማድረግ ነው።
በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እየገሰገሰች ያለችው ኢትዮጵያ 130 ሚሊዮን ሕዝቧ ላይ ከየአቅጣጫው ድንበሯን እየቀናነሱ በመቆለፍ ማኖር እንደማይችል ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ብልጽግና ኖረም አልኖረም አጀንዳው የመላው ፍትህ ወዳድ ሕዝብ በመሆኑ ያከተመ ጉዳይ እንደሆነ በግልጽ ተናግረዋል።
በቀደመው መንግስት የቀይባህርንም ሆነ የአሰብን ጉዳይ ማንሳት ወንጀል ተደርጎ እንደሚቆጠር፣ የባህር በር አጀንዳ ማንሳት ” የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ” እንደሚያሰኝና በአደባባይ እንደሚያስወነጅል እያዩና እየሰሙ ለኖሩ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጉዳዩን የመንግስታቸው ዋና አጀንዳ ማድረጋቸው ከፍተኛ የብሄራዊ መነቃቃት ማዕበል አስነስቷል።
በተቃዋሚ ፓርቲ ጎራ ካሉትና በተለይም መንግስትን በመተቸት ብቻ ከሚታወቁ ወገኖች “ኢትዮጵያ የባህር በር አያስፈልጋትም” በሚል ተቃውሞ እየገጠመው ያለው ይህ ብሄራዊ አጀንዳ እነዚህ ወገኖች ባሰቡት ደረጃ ሕዝብ ጆሮ አልሰጣቸውም። ለዚህ ይመስላል አብይ አሕመድ ጉዳዩን የፖለቲካ መጠቀሚያ፣ አጀንዳ መሸጪያ፣ ብሎም የምርጫ ማሟሟቂያ አድርገው ለሚወስዱት ” በመድመር ትውልድ ላይ ከሶስት ኣመት በፊት የጂኦፖለቲካ እይታ በሚል ርዕስ ገጽ 245 ላይ በግልጽ ተቀምጧል አንብቡት” ሲሉ ተስደምጠዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ። 120 ሚሊዮን ህዝብ ተዘግቶበት አይኖርም ። አንድ ግለሰብ ማርስ ላይ እወጣለሁ በሚልበት ዘመን 120 ሚሊዮን ህዝብ በ 45 ኪሜ ርቀት ላይ ስለሚገኘው ቀይባህር አትናገር ሊባል አይቻለውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ
ስማቸው “ኢትዮጵያዊ” የሆኑ የዩቲዩብ አክቲቪስቶች ከፕርቲቶሪያው የሰላም ስምምነት በሁዋላ ከኤርትራ መንግስት ጋር አብረው በማኩረፍ “አገሬ” በሚሏት ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጠር ዘመቻ በመክፈት ኢትዮጵያ ኤርትራን ለመውረር እንደተዘጋጀች አድርገው በተከታታይ ቅስቀሳ ማሰራጨት ከጀመሩ ቆይተዋል። ከትህነግ አንጃ ጋር ኝኙነት የጀመረውን ሻዕቢያን በኢትዮጵያ አዲስ መንግስት ለመመስረት መሪ አድርገው እየሳሉም ነው።
በተለያዩ ማስረጃዎችና መረጃዎች ከሻዕቢያ ጋር ጥምረት ፈጥሮ እየሰራ ያለው የጎጃም ፋኖ፣ በዶክተር ደብረጺዮን የሚመራው አፈንጋጩ ትህነግ አማራና ትግራይ ክልልን የጦርነት ማዕከል ለማድረግ መሳማማታቸውን ጠቅሰን አስቀድመን መዘገባችን ይታወሳል። ወይዘሮ ፈትለወርቅ በአንድ ቃለ ምልላሳቸው ከሻዕቢያ ጋር ንግግር መጀመሩን ማመናቸውን በጠቀሰው በዚሁ ዜና ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ክተት ሳይቀር አውጆ ኃይሉን ትግራይ በማስረግ፣ በሽሬ በኩል ለማምለጫ የሚሆን ጥርጊያ መንገድ በማዘጋጀትና ምሽግ በመቆፈር ስራ መጠመዱም ተመልክቶ ነበር።
በዛሬው የፓርላማ ውሎ ለዚህና ለበርካታ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አብይ አሕመድ ” ለኤርትራ ሕዝብ የማርጋግጠው ጉዳይ” በማለት ኢትዮጵያ አንድም ጥይት ወደ ኤርትራ የመተኮስ እቅድ እንደሌላት አስታውቀዋል። የባህር በር አጅንዳ መያዝ ጦርነት የመክፈት አጀንዳ እንዳልሆነ አስታውሰው፣ የዓለም አገራት በዓለም የንግድ፣ የአብሮ መስራት፣ የጋራ ተጠቃሚነት አግባብ በሰጥቶ መቀበል ህግ አንጋግሩን ሲሉ ሰላማዊ ጥሪ አቅርበዋል።
“በሌላ በኩል ግን” አሉ አብይ አህመድ፣ “በሌላ በኩል ግን ትንኮሳ ካለ ምላሹ የከፋ ነው። በቂ ዝግጅት የተደርገበት ጉዳይ በመሆኑ ትንኮሳ እንዳይሞከር እመክራለሁ” ሲሉ ለህዝብም ለፓርላማውም፣ በስፍራው ለነበሩ የውጭ ሚዲያዎችና ዲፕሎማት ይፋ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በግራ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆነ ዲፕሎማቶች አፈንጋጩ የትህነግ ኃይል ከሻዕቢያ ጋር በመሆን አገሪቱን ለማተራመስና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመቀልበስ እየሰሩ መሆኑን ” አለም ይወቅልን፣ ሃይ በሉልን፣ አስታግሱልን፣ አለበለዚያ ውርድ ከራስ” በማለት ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
ከኤርትራ በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ጊዜው ያለፈበት ጥያቄ በማንሳት አሰብን ለመውረርና ኤርትራ ላይ ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀቷን በመጥቀስ ክስ መቅረቡ አይዘነጋም።
ኤርትራ “ጊዜው ያለፈበት” በማለት ለትቆልፈው የሚገባውን ጉዳይ ነው አብይ አህመድ “አሱ ያከተመለት ጉዳይ ነው፣ የህልውና መሰረት ነው። እያልን ያለነው እነነጋገር ብቻ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው አቋም ሊቀለበስ እንደማይችል ይፋ ያደረጉት።
በኢትዮጵያ ለውጡ ይፋ ሲሆን ሻዕቢያ አሰብን አስመልክቶ በንግድ ውል ለኢትዮጵያ ለመስጠት በመርህ ደረጃ ተስማምቶ ዝርዝር የውል ሰነድ ቀርቦለት ነበር። በድንገት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲደረግ ” ለምን ስምምነቱ ተፈረመ” በሚል አኩርፎ ኝኙነቱን ማቋረጡ አይዘነጋም።
ሻዕቢያ ቀደም ሲል ጀመሮ አማራ ክልል ላይ በተከለው መዋቅሩ አማካይነት አሁን ያለውን ረብሻ ማወለዱን ከአዲስ አበባ ወደ በዱባይ ያቀናውና ይህንኑ ስራ ሲሰራ የነበረው የቀድሞ የኢሳያስ ታማኝ ቀደም ሲል ምስክርነቱን መግለጹን በተለያዩ ሪፖርቶች ይፋ ማድረርጋችን የሚታወስ ነው።