ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የትግራይ ሕዝብ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ የጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚመራ ዕጩ በኢሜል ጥቆማ እንዲስጠ ጥሪ ቢያቀርቡም “አፈንጋጭ” የሚባለው ቡድን ” ሌ/ጄነራል ታደሰን መርጫለሁ” በሚል ጥቆማውን እንደማይቀበለው ማስታወቁ አይዘነጋም። ቡድኑ ይህን አስታውቆ ባሰራጨው መግለጫ “የፌደራል መንግስት የትግራይን ሕዝብ ትዕግስት እየተፈታተነ ነው” ሲል ጦርነት ምርጫው ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ አሳይቶም ነበር።
ከዚህ ቀደም ብሎ የአገር መከላከያ ሰራዊት የትህነግ ታጣቂዎች አመራር ከሆኑት መካከል ጀነራል ምግበን ጠቅሶ በሳቸው የሚመሩ ክፍሎች የፋኖ ኃይልን በማደራጀት በስምንት አቅጣጫ ጦርነት እንዲከፍቱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ማስታወቁን ማስጠንቀቂያ መስጠቱ አይዘነጋም። ትህነግ የአገር መከላከያን ማስጠንቀቂያ ውድቅ በማድረግ ምግበ ፣ምንም ውስጥ እንደሌሉ ምላሽ ሲሰጥ ድርጊቱ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጣስ እንደሆነ በመጥቀስ ነበር።
ቀደም ሲል በትህነግ ለሁለት መከፈል ተጀምሮ የጊዚያዊ አስተዳደሩን እስከማፍረስና ስልጣን እስከመቀማት የደረሰውን ቡድን የሚደግፉት የታጣቂው ክፍል አመራሮች ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት መጀመራቸውንና አንዳንድ የጦርነት ዝግጅት መጀመራቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቀዋል።
ቀደም ሲል ሌ/ጄነራል ጻድቃን ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት የጀመሩ አካላት እንዳሉ በግልጽ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፣ እሳቸውን ተከትለው በትግራይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አቶ ገብሩ አስራት በተላያዩ ጊዜያት በተመሳሳይ ድርጊቱን በማውገዝ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
በትግራይ ያለውን ነዳጅ በመሰብሰብ ለጦርነት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም ደብቀዋቸው የነበረውን ከባድ መሳሪያ ሮኬቶች፣ ታንክና መድፎችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ማንቀሳቀስ መጀመራቸውን በትግራይ የትግራይ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ቢሮ ሃላፊ ማጋለጣቸውን በምስልና በድምጽ ተደግፎ ይፋ ሆነ።
ትርጉሙ “ነዳጁን በሙሉ ወስደው ጨርሰውታል።እሱም አልበቃ ብሏቸው ከራያ አላማጣና ከአፋር እያስመጡ ነው።ከጂቡቲ የሚመጣውን ነዳጅ በሙሉ በቀጥታ አዲ ፀፀር (ሸራሮ አካባቢ ) ፣ አዲክልተፐ፣ ገዛ ተጋሩ ፣ ዛና ፣ ህርሚ ፣ ሰመማ ፣ አዲደቂ በቅሊ ወዘተ በሚባሉ አካባቢዎች ውስጥ አከማችተውታል።ከባባድ መሳሪያዎቻቸውንም ከቦታ ወደ ቦታ እያንቀሳቀሷቸው ነው ያሉት።ማለቴ ..በርክክቡ ወቅት ደብቀው(ቀብረው) ያቆይዋቸውን ሮኬቶችን ጨምሮ መድፎችንና ታንኮቻቸውን ከቀበሩበት እያወጡ ወደ አዲ ደቀበቅሊ እና የጭላ ወስደው ደብቀዋቸዋል ይሄ ሁሉ ጥድፊያ ለጦርነት እየተዘጋጁ እንደሆነ ግልፅ ነው። እነዚህ ሰዎች ጦርነት እየጠመቁ ያሉት ለትግራይ ደህንነት አስበው አይደለም” – ለስልጣናቸው ሲሉ ነው
—– አቶ ጠዓመ አረዶም (የትግራይ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ቢሮ ሃላፊ )
የትግራይ ሕዝብ በበኩሉ አብላጫው “ጦርነት በቃን” በሚል የአፈንጋጭ ቡድኑን እንቅስቅሴ በገሃድ እየተቃወመ እንደሆነ የሚያሳዩ በማስረጃ የተደገፉ ዜናዎች ጎን ለጎን ይወጣሉ። የታጣቂው ኃይል አመራሮችና ወታደሮች ሳይቀሩ በተቃውሞ የተሰለፉበት የአፈንጋጩ ኃይል የጊዚያዊ አስተዳደሩን የሚያፈርስ እንቅስቅሴ በስኬት የተጠቃለለ እንደሆነ ተደርጎ ቢታይም አሁን ላይ የተሰማው ዜና የተለየ ነው።
መንግስት በተደጋጋሚ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ ዲፕሎማቶችና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ሻዕቢያ የሚጋልባቸው አፈንጋጭ ኃይሎች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመጣስ ቋፍ ላይ መድረሳቸውን ” አስታግሱልን፣ እወቁልን” በማለት ማስታወቁን ተውከትሎ አሜሪካና የአውሮፓ ታላላቅ አገራት አቋማቸውን ለትህነግ ሰዎች ማሳወቃቸው ተሰምቷል።
ከአፈንጋጭ ኃይሎቹ ጋርና ከጎጃም የፋኖ ኃይሎች ጋር ጦርነት እየጠመቀ ያለው ሻዕቢያ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ “ድረሱልን” የሚል ጩኸት ቢያሰማም በገሃድ ምላሽ የሰጠው አካል እስካሁን አልተሰማም፤ ይልቁኑም የትህነኝ አፈንጋጭ ኃይል ከጀመሩት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ፣ ይህ ካልሆነ ለሚደስባቸው ሁሉ ኃላፊነታቸውን ራሳቸው እንደሚወስዱ በግልጽ እንደተነገራቸው ለማወቅ ተችሏል። በተለይም ከሽብር ተግባር ጋር ከሚጠረጠረውና ከየመን ሃውቲዎች ጋር አልሸባብን ከማስታጠቅ ጋር በተያያዘ መረጃ ከተገኘበት ሻዕቢያ ጋር ማበራቸው ከቶውንም ቢሆን ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጾላቸዋል። ይህ ተግሳጽ ምን ወደፊት ለፍረጃ የሚያዘጋጃቸው ስለመሆኑ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
በዚሁ ማስጠንቀቂያ መሰረት ሁለት ጊዜ አዲስ አበባ በመመላለስ ጥብቅ ውይይትና ክርክር መደረጉን ኢትዮሪቪው ሰምታለች። ከዚህ በሁዋላ እንደቀድሞው አዲስ አበባ እየተሰማሙ መቀለ በመሄድ ማፍረስ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጣስ እንደማይቻል ጥብቅ አቋም መያዙ ተውቋል።
ከላይ በተባለው መነሻ መሰረት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ አዲስ አበባ ነበሩ፤ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል እና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ሌ/ጄኔራል ታደሰ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ የተባለው ስብሰባ ነው ያደረውጉት። ከስብሰባው መጠናቀቅ በሁዋላ ይተገበራሉ የተባሉ ዋና ዋና ነጥቦች ተነቅሰው ከተሰጧቸው በሁዋላ ተግባራዊ ለማድረግ ተስማምተው ወደ መቐለ ተመልሰዋል። ከስምምነት የደረሱት መቐለ ሄደው ጓዶቻቸውን አስታውቀው ከተመለሱ በሁዋላ በተደረገ የማጠቃለያ ውይይት ነው።
ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ሥምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች በሚል የቀረቡት ከዚህ የሚከተሉት ናቸው
- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወደቦታው ይመለሳል፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ተግባር የሚያድናቅፍ ማንኛውም አካል ላይ ተመጣጣኝ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል፣
- በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ይሰየማል፤
- ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ይሰራሉ፤
- ጄኔራል ተኽላይ አሸብር (ወዲ አሸብር) የታደሰ ወረደ የሃላፊነት ቦታ ይሰየማሉ ወይም ጸጥታ ኃላፊ ይሆናሉ፤
- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መቐለ ከተማን ጨምሮ በነባር ካምፖች ውስጥ ይገባል፤
- የትግራይ ታጣቂ ሃይል ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲገቡ ይደረጋል። የተቋረጠው የ DDR ተግባር በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በትክክል ይተገበራል፤ ለ DDR ገንዘብ የለገሱ ሃገራት (አሜሪካን ጨምሮ) ገንዘቡን እንዲለቁ ይደረጋል፤
- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ እንደገና የሚደራጅ ሆኖ በአዲሱ አደረጃጀት ትህነግ 50%፣ ብልጽግና 25% እንዲሁም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት 25% ድርሻ ይኖራቸዋል። በመጀመሪያው የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ የሰራዊት/ታጣቂ ወኪል የካቢኔ አባል የነበረ ሲሆን በአዲሱ አደረጃጀት ውክልና አይኖራቸውም፣
- ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ ፤ ከዚህ በፊት የተደራጀው የብሔራዊ ኮሚቴና የክልል ቴክኒክ ኮሚቴዎች በአዲስ መልክ ስራ እንዲጀምሩ የሚሉት ውናዎቹና አንኳር ጉዳዮች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአገር መከላከያ ሰራዊት ኃይሉን በተመረጡ ቦታዎች እያሰፈረ መሆኑ ታውቋል። አገር መከላከያ የሻዕቢያን እንቅስቃሴ በልዩ ትኩረት እየተከታተለ እንደሆነ የሚጠቁሙ ወገኖች፣ የትግራይ ነዋሪዎች መረጃ በመስጠት ትብብር እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በጦርነቱ ወቅት ሻዕቢያ ክፉ ተግባራትን መፈጸሙን የሚያስታውሱ የትግራይ ነዋሪዎች ዛሬ ከሻኧቢያ ጋር የገጠሙትን የትህነግ ክፋዮች በክህደት እንደሚፈርጇቸውም ለማወቅ ተችሏል።
ሻዕቢያ ገና ለገና ኢትዮጵያ በግፍና በክህደት የተወሰደባትን የአሰብ ወደብ በኃይል ታስመልሳለች በሚል ፍርሃቻ በአማራና ትግራይ ክልል ጦርነት አቀጣጥሎ ኢትዮጵያን ለርማተራመስ የያዘው ዕቅድ ስላልተሳካለት የሽምግልና ሂደት እንዲጀመር እየወተወተ መሆኑ ተሰምቷል።
የለውጡ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና ፐሬዚዳንት ኢሳያስን አገናኝታ ወርቅ የሸለመችው ሳዑዲ አረቢያ በወቅቱ ያፈራመችውን የንግድና የወደብ ስምምነት ሰነድ በማንሳት የማግባባት ስራ ለመስራት የተናጠል ውይይት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኗን ጉዳዩን የሚከታተሉ አመልክተዋል።