የትህነግ ኃይሎች ለሁለት መከፈላቸውን ተከትሎ ከትግራይ የሚወጣው ዜና አጋጣሚውን ለመጠቀም ካሰፈሰፈው የሻዕቢያ የትርምስ አጀንዳ ጋር ተዳምሮ ህዝብ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች በስፋት እየተሰራጩ ናቸው። ፖለቲከኞቹም በቀደመው ጦርነት ሚሊዮን የሚጠጋ ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት መሆናቸውን ዘንግተው ህዝቡ ለሚያሰማው ጩኸት ጆሮ ዳባ ብለዋል።
“ትህነግ ራሱን ለትግራይ ህዝብ ልዩ ጠበቃና ከለላ የሚያደርግ መሲህ አድርጎ ሲያቀርብ ያስገርመኛል” የሚለው የአውሮፓ ነዋሪ የትግራይ ተወላጅ ” ባለፉት 27 ዓመታት ለትግራይ ህዝብ ምን ሰሩ? በሴፍቲ ኔት ስንዴ እየሰፈሩ የሚቀልቡትን ይሆን እንደ ገልድል የሚያወሩት ወይስ በሰፈር ተቧድነው የዘረፉትን ሃብት? ወይስ የትግራይን ህዝብ ዙሪያውን ካለው ህዝብ ጋር ጠላት አድርገው .”
ራሳቸው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጦርነት መክፈታቸውን በገሃድ አምነውና እንደ ታላቅ ገድል ለህዝብ በሰበር ዜና አስታውቀው ሲያበቁ በተቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ የደረሰው ጥፋት ሃዘኑ ሳይጠግ፣ ሰላባዎች ዱላ ሳይጥሉ፣ አካለ ስንኩላኖች ከተማውን ሞልተውት፣ ወዘተ የትህነግ ኃይሎች ለስልታን ሲሉ ዳግም ወደ ጦርነትና ግጭት መንደርደራቸው እሱን ብቻ ሳይሆን በርካቶችን እንዳሳዘነ ይገልጻል።
ችግር መኖሩን፣ የተፈናቀሉ ንጹና ዜጎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚናገሩ፣ ትህነግ ዳግም ከኤርትራ ጋር ለማበር መርመጥመጥ መጀመሩን “በሬ ካራጁ” እያሉት ነው። በጦርነቱ ወቅት የኖረ ቂሙን የትግራይ ህዝብና ንብረት ላይ የተወጣው የኢሳያስ ጦር በደሉና ግፉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በጄኖሳይድና በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያስጠይቀው ሆኖ ሳለ አንደኛው የትህነግ አፈንጋጭ ኃይል ተመልሶ እነሱ ስር መግባቱ ትግራይን ይበልጥ ተጎጂ እንደሚያደርጋት ስጋታቸውን የሚያቀርቡ ጥቂት አይደሉም።
በ2015 የተፈረመው የሠላም ስምምነት ሊፈርስ ይችላል፣ አልፎ ተርፎም በኢትዮጵያ እና በጎረቤቷ ኤርትራ መካከል ቀጥተኛ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት እየናጣቸው ያሉ የመቀለ ነዋሪዎችን ቢቢሲ አነጋግሮ ካሰፈረው ላይ አስተያየቱን ብቻ በመውሰድ ከስር አቅርበናል።
የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ በቀጥታ ወታደሮቹን በማሰማራት ተሳትፏል።
ነገር ግን የሁለቱ አገራት ግንኙነት የፕሪቶርያ ሠላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ እየሻከረ መጥቷል።
በመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ቀጣይ ግጭት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ገብቷቸዋል።
ጫማ በመጥረግ ሕይወቱን የሚመራው እና እድሜው በሀያዎቹ የሚገመተው ተስፋይ ገብረአብግዚ “ወጣቶች ግጭት ሰልችቷቸዋል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
“በጦርነቱ ወቅት ብዙ ሰዎች የመዋጋት ፍላጎት ነበራቸው፤ አሁን ግን ተሰላችቷል።”
አትክልቶችን በመሸጥ የምትተዳደረው እና እድሜዋ በ50ዎቹ የሚገመተው ሐይማኖት ገብረማርያም ደግሞ በ2013 የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሁለቱ ልጆቿ በትግራይ በኩል ጦርነቱን መቀላቀላቸውን ትናገራለች።
ሴት ልጇ በሰላም ስትመለስ ወንድ ልጇ ደግሞ የአካል ጉዳት አጋጥሞታል።
ወደ “ጨለማው ዘመን” መመለስ እንደማትፈልግ የምትገልጸው ሐይማኖት፣ አሁን ያለው ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“አሁንም የምንኖረው ካለፈው ጦርነት ቁስል እና ጠባሳ ጋር ነው። ዳግመኛ እንባችንን ማፍሰስ አንፈልግም።”
ፀጋነሽ ካሳ በማዕከላዊ ትግራይ፣ ሽሬ የምትኖር የቀድሞ ታጋይ ስትሆን፣ በጦርነቱ ወቅት እግሯ ክፉኛ ቆስሏል።
አሁን በክራንች የምትራመድ ሲሆን በቋሚነት ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋታል።
ለቢቢሲ ጦርነት “ቤተሰቤን አቃውሶታል” ብላለች።
“የአካል ጉዳተኛ ነኝ፤ የቤተሰቤ ኢኮኖሚ ላሽቋል። ያንን እንደገና ማየት አልፈልግም። በድንኳን ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንኳን አልተመለሱም።
አክላም “ማንም ሰው ሌላ [ዙር ጦርነት] ማስተናገድ አይችልም” ብላለች።
የትግራይ ክልል ጦርነቱ ካስከተለው አስከፊ ጉዳት ሙሉ በሙሉ አላገገመም።
ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም።
አንዳንድ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ገና አልተጠገኑም።
በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በግልጽ የሚታይ ጭንቀት ቢኖርም መደበኛ ሕይወት ግን ቀጥሏል።
ንግዶች እና ሱቆች በመደበኛነት እየሰሩ ናቸው፤ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ብዙ የጸጥታ ኃይሎች አይታዩም
ነገር ግን በአፍሪካ አስከፊ ከሚባሉ መካከል አንዱ የሆነውን ጦርነት በቅርቡ ያስተናገደችው ከተማ ነዋሪዎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እና መግለጫ በንቃት እና በቅርበት ይከታተላሉ።
በአንድ ቡና መሸጫ ካፌ ውስጥ የተሰባሰቡ ወጣቶች አንገታቸውን ስልካቸው ውስጥ ቀብረው ይታያሉ።
በቅርቡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከፌዴራል ባለስልጣናት ጋር “ለመመካከር” በሚል አዲስ አበባ ከሄዱ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምለሽ እየተመለከቱ ነው።
በሌላ ካፌ እንዲሁ አንድ ወጣት ሐሙስ ዕለት በተቃዋሚው የህወሓት ቡድን የተሾመው፣ አዲሱ የከተማዋ ከንቲባ ሕዝቡን ለማረጋጋት እንደሚያደርግ ለመስማት እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል።
ሁሉም ሰው፣ የሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ምን እንደሚያመጡ ለማየት እየጠበቀ ያለ ይመስላል።