ብልጽና ትግራይን በግማሽ ውክልና እንዲያስተዳድር ስምምነት መደረሱ ተሰማ። ስምምነቱ የፕሪቶሪያው የሰላም አማራጭ ውል አካል እንደሆነ ታውቋል። በዚሁ ስምምነት መሰረት በትግራይ አዲስ አስተዳደር ይቋቋማል። ሻዕቢያ በትግራይ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈርስና የአገር መከላከያ ሰራዊት ጣልቅ እንዲገባ ያዘጋጀው ዕቅድ መክሸፉን ተከትሎ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት እደግፋለሁ” ሲል በይፋ በማስታወቅ እነ ደብረጽዮንን መክዳቱም ተገለጸ።
በትግራይ የትህነግ ኃይሎች መከፋፈላቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተካሄደ የተናጠልና የጋራ ውይይት በትግራይ አዲስ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑ አመልክተዋል። እነዚህ ወገኖች እንዳሉት ከሆነ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ብልፅግና አዲስ በሚዋቀረው የትግራይ አስተዳደር የሃምሳ በመቶ ድርሻውን ይይዛል። ከዚህ ቀደም በነበረውና አሁን እንዲፈርስ በተደርገው ጊዜያዊ አስተዳደር ብልጽና ” እናንተ ተስማምታችሁ ስሩ፤ እኔ ይቅርብኝ” በማለት በፈቃደኛነት የሃምሳ በመቶ ድርሻውን እንደተወ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች መናገራቸው አይዘነጋም።
ብልፅግና በድርሻው መሰረት በአዲሱ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚሳተፉ አመራሮችን የሚመድብ ሲሆን፣ የተቀረው ሃምሳ ከመቶ የአዲሱ አስተዳደር አመራሮች ከትህነግ፣በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የተቀናቃኝ ፓርቲዎች የሚያካተቱበት ይሆናል።
ይህ ከሆነ በሁዋላ በፕሪቶሪያው የሰላም አማራጭ ስምምነት መሰረት የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት መሰየም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በመሆኑ በዛው አግባብ መሰረት እንደሚከናወን ለመረዳት ተችሏል።
ሕዝብ ጦርነት መሸከም እንደማይችል በገሃድ እየገለጸ ባለበት፣ ከሻዕቢያ ጋር ኝኙነት በመፍጠር ትግራይን የጦርነት አውድማ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ውጥን መክሸፉን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
አፈንጋጮቹ የትህነግ ኃይሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን በማፍረስ ለሻዕቢያ መተማመኛ እንዲሰጡ በተደረሰ ስምምነት መሰረት ማህተም መንጠቅና ቢሮ መውረስ ሲካሄድ መሰነበቱን አቶ ጌታቸው ረዳ ማስታወቃቸው ይታወሳል። አቶ ጌታቸው ” ጥቂት ኝ አደገኛ” ያሉዋቸው አካላት ታጣቂዎችን በመያዝ ከሻዕቢያ ትዕዛዝ ተቀብለው እንደሚንቀሳቀሱ ሙሉ መረጃ እንዳላቸው በይፋ ማስታወቃቸውን ተከትሎ መንግስትም በይፋ በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው አፈንጋጩ ኃይል ከሻዕቢያና ከግብጽ ጋር ግንኙነት እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ” በቃህ በሉልኝ፣ የፕሪቶሪያውንም ስምምነት እየናደ ነው” በሚል ለዲፕሎማቶች አሳስቦ ነበር።
ሻዕቢያ ትግራይ ስትተራመስ የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ወደ ወልቃይትና አማራ ክልል ውጊያውን ለማስፋት አስቀድሞ የያዘው ዕቅድ በመክሸፉ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደሚደግፍ በይፋ ለማወጅ ተገዷል።
ከዛሬ ነገ የኢትዮጵያ መንግስት በግፍና በሴራ ኢትዮጵያ የተነጠቀችውን ወደብ ያስመልሳል የሚል ስጋት የወጠረውና ሙሉ በሙሉ የመዋጋት ፍላጎት የለውም የሚባለውን ጦሩ ውጊያ ከተከፍተ መቋቋም እንደማይችል የሚያውቀው ሻዕቢያ በዚሁ ስጋቱ መነሻ ነበር ትግራይና አማራ ክልልን የጦርነት ማዕከል ለማድረግ ያቀደው።
ከግብጽ መመሪያና ድጋፍ እየተቀበለ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደሚሰራ በበርካታ መረጃ የተያዘበትና ቀደም ሲል ጀምሮ በዚሁ ተግባሩ ብዙ ማስረጃ የሚደረደርበት ታሪካዊው የኢትዮጵያ ጠላት ሻዕቢያ ” ለፕሪቶሪያው ስምምነት ስኬት ድጋፍ አደርጋለሁ” ማለቱን የነ ስብሃት ነጋ አቀንቃኞች ” ክህደት” ብለውታል።
እነ ስብሃት ነጋ ” ለሻዕቢያ ግርድና የተቀጠሩ” በሚል በተቃዋሚዎቻቸው እየተወገዙ ቢሆንም የስብሃት ወገን የሆኑት አሁን ድረስ ከሻዕቢያ ጋር የተጀመረው ግንኝነት ፍሬ ያፈራል ሲሉም ይደመጣል። እነሱ ይህን ይበሉ እንጂ በትግራይ ብልጽግ ሃምሳ ከመቶ የሚቆጣጠረው አዲስ አስተዳደር ስለሚመሰረት ምን አልባትም አሁን ላይ ሻዕቢያ በኃይል ከያዛቸው አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቆ እንዲወጣ በይፋ መመሪያ ሊሰጠው እንደሚችል ዜናውን ያጋሩን አመልክተዋል።