ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር የስልክ ውይይት ካደረጉ በሁዋላ ከየአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርማርኮ ሩቢዮ ጋር መምከራቸውን አሜሪካ አስታወቀች፡፡ ” አሜሪካ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን ትደግፋለች ” ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር መወያየታቸውን ያስታወቀው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውይይቱ የአፍሪቃ ቀንድ መረጋጋትን ያካተተ እንደነበር አመልክቷል፡፡
አነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ ተመልሰው ወደ ዋይትሀውስ ከገቡ በኃላ በመሪ ደረጃ ውይይት መደረጉ በይፋ ሲገለጽ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የሩቢዮ ውይይት በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን ጨምሮ በጋራ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር በደፈናው ከመገለጹ ውጭ ዝርዝር የተባለ ነገር የለም፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎ እንዳለው ውይይቱ የኢትዮጵያ እና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገም ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት ” አሜሪካ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ትደግፋለች ” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደገለሹላቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሜሪካ ለሶማሊ ላንድ እውቅና ለመስጠትና በምትኩ የጦር ቤዝ ለመመስረት ማሰቧን ተከትሎ ኢትዮጵያ አጋጣሚውን ልትጠቀምበት እንደምትችል በስፋት እየተገለጸ፣ ሻዕቢያ ትህነግን ይዞ ጋር ሆኖ ጦርነት ለማስነሳት ክተት በጠራበት፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን መንግስት ከአልሸባብ ወረራ ለመታደግ የአየር ጥቃት እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የሁለቱ አገራት ውይይት ክብደት ያለው እንደሚሆን ተገምቷል።
ባለፈው ሳምኝ “እስራኤል ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተዋሳኝ ለመሆን ለያዘችው ሁለንተናዊ ጥረት ያልተገደበ ድጋፍ ታደርጋለች!” በማለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ መናገራቸው ይታወሳል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ኔታንያሁ የስልክ ውይይት በሁዋላ የተሰማው ዜና ኢትዮጵያ ለጀመረችው ወደ ቀይ ባህር የመመለስ ትግል እንደ አንድ ከፍተኛ ድል ተወስዶ ነበር።
ዶናልድ ትራምፕ የሚመሩት መንግስት ከእስራኤል ጋር ካለው እጅግ ጠንካራና የማይታጠፍ አንድነት አንጻር ዛሬ ከአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰማው ዜና ትርጉሙ የገዘፈ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ።