በአገር አቀፍ ደረጃ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች በውል ተለይተው አለመመዝገባቸው እና የብቃት ዕውቅና አለመኖሩ ሞያዊ ክፍተት መፍጠሩ ተነግሯል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩ ጋዜጠኞችን የሚያካትት የሞያ ማንነት ምዝገባ ለማከናወን የሚረዳ መመሪያ ለውይይት ቀርቦ የተለያዩ ሃሳቦች ተሰንዝረውበታል።
በአዝማን ሆቴል በተካሄደው የጋዜጠኞች ምዝገባ፣ የሞያ ማረጋገጫ እና ብሔራዊ ሚዲያ ሽልማት ዕውቅና ላይ ያተኮረው የማረጋገጫ ዓውደ ጥናት ላይ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ውስጥ የሚሰሩ ባለሞያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ምዝገባ እና የሞያ ብቃት ምዘና እና ብሔራዊ ሚዲያ ሽልማት ጉዳዮችን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት መምህር የሆኑት ዶክተር አየለ አዲስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ፣ “የሞያ ማንነት ማረጋገጥ ስንል የሞያ ብቃት መስጠት ማለት ነው” በማለት ገልጸው፣ ይህን አገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ምዝገባና የብቃት ዕውቅና የመነሻ ጥናቶችን፣ ሞዴል የሕግ እና የተሞክሮ ማዕቀፍ፣ መመሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችን በውስጡ ያቀፈ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በመገናኛ ብዙሃን ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ጋዜጠኞች ሞያዊ ብቃት አለመመዘኑ እና ባለሞያዎቹም በውል ተለይተው አለመታወቃቸው በዘርፉ ላይ ክፍተት እየፈጠረ እንደሚገኝ ያስረዱት ዶክተር አየለ፣ በዚህ የምዝገባና የሞያ ብቃት ስርዓት አማካይነት ለእያንዳንዱ የሚዲያ ባለሞያ ዕውቅና የሚሰጥበት፣ ዕውቅና የሚሰጣቸው እና የማይሰጣቸው ተለይተው የሚታወቁበትና ልየታውን ለማከናወን የሚረዱ የመመዘኛ መስፈርቶች የሚወጡበት ሂደቶች እንደሚኖሩ ተናግረዋል። አያይዘውም፣ በጥናቱ ሂደት ውስጥ የሌሎች አገራት ተሞክሮ መፈተሹን ዶክተር አየለ አመልክተዋል።
በመሆኑም በጥናቱ ውስጥ በተካተቱ መስፈርቶች መሰረት ተደርጎ፣ በተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ አማካይነት ጋዜጠኞች የሞያ ብቃታቸውን የሚያሳይ መታወቂያ (የፕሬስ መታወቂያ) በዲጂታል አሰራር የሚያገኙበት አሰራር ለመተግበር መታቀዱን ዶክተር አየለ ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ሃይሉ፣ ይህ መታወቂያ እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ፣ የጋዜጠኝነት ሞያ የተከበረ መሆኑን ለማሳየት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ይህም አሰራር በሌሎች አገራት የተለመደ መሆኑን ያነሱት አቶ ታምራት፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ቢደረግ ለዘርፉ የራሱን ዕመርታ እንደሚያሳርፍ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።
በዓውደ ጥናቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የዘርፉ ባለሞያዎች የተለያዩ ጥያቄ እና አስተያየቶችን አንስተዋል። ለጋዜጠኞች የፕሬስ መታወቂያ መሰጠቱን በአጽንዖት የተቃወሙ እና አሰራሩ በሌላ አማራጭ ሃሳብ እንዲተካ የጠየቁ ባለሞያዎች ሲኖሩ፣ ሌሎች ደግሞ መታወቂያ የመስጠቱ ሂደት የምክር ቤቱ ሃላፊነት ስለመሆኑ በአንክሮ ጠይቀው፣ ጉዳዩ እንደገና እንዲፈተሽ ያሳሰቡ ነበሩ።
ዓውደ ጥናቱ ለረቂቅ መመሪያውም ሆነ ለሌሎች የአሰራር ሂደቶች እንደሃሳብ ግብዓት ማሰባሰቢያ ያገለገለ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ታምራት፣ በቀጣይም ምክር ቤቱ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የረቂቅ መመሪያውንም ሆነ ሌሎች የአሰራር ሂደቶችን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ ነው ያመለከቱት።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Vua AdissAdmas