የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ከየካቲት 22 እስከ የካቲት 24/ 2017 ዓ.ም. ሲያደርግ የነበረው ስብሰባ በድርጅቱ አሠራር ሒደት እና ወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በቀጣይ ስለሚኖሩ ድርጅታዊ ተግባራት ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
1) ድርጅታዊ ጉዳዮች፤
1.1) የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ: በኢዜማ መተዳደርያ ደንብ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ከፍተኛ የሥልጣን አካል ሲሆን የሥልጣን ዘመኑም 3 ዓመት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ይህ ጉባኤ የሥልጣን ዘመኑ ሊገባደድ ጥቂት ወራት የቀረው መሆኑን ከግንዛቤ በመውሰድ ሥራ አስፈጻሚው በድርጅታዊ መተዳደሪያ ደንቡ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መሠረት ጉባኤውን ለማካሄድ ወደ ዝግጅት እንዲገባ ውሳኔ አስተላልፏል።
1.2) የፓርቲ መዋቅሮችን ማጠናከር፡ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ከተካሔደው 6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በፍጥነት ተለዋዋጭ የሆነው የቀጠናው እና የሀገሪቱ ፖለቲካ እና የጸጥታ ችግር እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ተዳምረው ባለፉት ዓመታት የድርጅታችንን መዋቅሮች እና አባላት የታለመለትን ያህል የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ተግዳሮት ገጥሞን ቆይቷል። በመሆኑም ይህንን ችግር በሚያርቅ መልኩ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው የድርጅት መዋቅር ግንባታ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይደር የሚባል ተግባር እንዳልሆነ በመገንዘብ በዲጂታል ሥርዓት ማጠናከርን ጨምሮ ዘመኑ በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።
1.3) የኢዜማ አካዳሚ እና ተከታታይ አቅም ማጎልበቻ ውይይቶች፡ ኢዜማ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀዳሚ ተግባር ማኅበረሰብን ወደተሻለ ቦታ የሚያደርስ የጠራ አስተሳሰብ መያዝ፣ ይህን አስተሳሰብ መሬት ላይ ማውረድ የሚችል ዘመን ተሻጋሪ ድርጅታዊ መዋቅር መገንባት እንዲሁም በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆኑ ሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ስልታዊ በሆኑ ዘላቂ ግብ ላይ ተመስርተው እየተነተኑ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የሚችሉ አመራሮችን ማፍራት መቻል ትክክለኛ የሆነው መንገድ ከመሆኑም ባሻገር ዘላቂ የሆነ የሕዝብ ይሁንታን ያስገኛል ብሎ የሚያምን ፓርቲ ነው። ይህንን ሕልም በሀገራችን እውን ማድረግ ግን እንደሚታሰበው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በቅጡ ይረዳል፤ ረዥም ጊዜ እንደሚያስፈልገውም ይገነዘባል፡፡ በተለይ ልኂቃን የሚባሉት የሀገሪቱ ዜጎች በፖለቲካው ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት ደካማ መሆን እና በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ሥልጣን በሃሳብ የበላይነት ሳይሆን በጡንቻ መፈርጠም ላይ የተመሠረተ መሆኑን የተቀበለ የአስተሳሰብ ውቅር የበላይነት መያዙ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ፖለቲካ ላይ የዳር ተመልካች እንዲሆኑ ከመግፋቱም በላይ አምባገነን የሆኑ ሥርዓቶችም በሥልጣን ኮረቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት ምቹ ሁኔታ አድረገው እንዲወስዱት አድርጓል።
ይህንን አስተሳሰብም ሆነ አሠራር በሂደት ሊያርቅ በሚችል መልኩ የፖለቲካ አመራሮችን ማብቃት እንደ ተቀዳሚ ሥራ መውሰድ ይገባል። በዚህ ረገድ ኢዜማ አባላቱንም ሆነ ፍላጎቱ ያላቸውን ሀገር ወዳድ ዜጎች ለማሰልጠን ዝግጁ የሆነ አካዳሚ ገንብቶ መጨረሱን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞችን ወደ አካዳሚው ለማስገባት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተመዘገቡ አባላት በመመልመል ላይ ይገኛል። ከአካዳሚው ዘላቂ የአቅም ግንባታ ሥራ ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም ሲያደርገው ከነበረው የፖለቲካ ውይይቶች በተለየ ትኩረት ለአመራርነት እና ለጠራ ግንዛቤ አስተዋጽኦ ባላቸው የተመረጡ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የውይይት መድረኮች በተለያዩ አማራጮች እንዲካሄድ ወስኗል።
2) ሀገራዊ ጉዳዮች
2.1) ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፡ በውይይቱ በልዩ ትኩረት ከታዩት አጀንዳዎች መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንዱ ሲሆን ውስጣዊ የጸጥታ ችግሮች፣ የኑሮ ውድነት እና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮችን በየፈርጁ ተመልክቶ አሁናዊ ሀገራዊ ፖለቲካችን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ እየተለወጠ መምጣቱን ፓርቲው ተገንዝቧል። ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በኋላም ቢሆን በዘውግ ማንነት ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ሂደት የሀገራችንን እድገት እና ዴሞክራሲ ወደኋላ በማስቀረት ዛሬም እልባት ስላላገኘ ለዜጎቻችን መፈናቀል፣ ሞት እና ሰላም ማጣት መንስኤ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ በእንደዚህ አይነት ሃገራዊ ሁኔታና በሚለዋወጡ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክንያት ሀገር ወዴት እየሄደች ነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ባለመቻሉ ህዝባችን በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ መሆኑን እና ማህበረሰባችንን ከዚህ ግራ መጋባት በማውጣት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚኖርባትን ሀገር ለመፍጠር የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት ለመዘርጋት ይቻል ዘንድ ፓርቲያችን ይህን ተለዋዋጭ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት በተረዳ መልኩ ለህዝቡ ጠንካራ የፖለቲካ አማራጭ ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ወቅቱን የሚመጥን የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አሠራር ማስፈን ይረዳ ዘንድ የአጭር እና የረዥም ጊዜ ተግባራት የለየ ሲሆን ይህንንም አስመልክቶ በቅርቡ የተብራራ ሰነድ ይፋ እንደሚያደረግ ያሳውቃል።
ፓርቲያችን ኢዜማ ከድርጅታዊ መርኆዎቹ ቀዳሚው የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ሁሌም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። የፖለቲካ ፓርቲ (የቡድኖች) ጥቅም ከሀገር በታች የሆነ ፍላጎት መሆኑን በመገንዘብ የሀገርን ጥቅም ጉዳይ በምንም መልኩ በሁለተኛ ደረጃ የሚያየው እንዳልሆነ ዛሬም በድጋሚ ለማረጋገጥ ይፈልጋል። ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በተለይ በዘውግ ማንነት ላይ የተንጠለጠለው የፖለቲካ አስተሳሰብ እና መዋቅር እስካሁን ሀገራዊ አንድነታችን በማላላትም ሆነ ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅማችን ስጋት የሆኑ አያሌ ችግሮችን ያጋለጠን መሆኑ ሳያንስ በዚህ ስሁት አስተሳሰብ የተለከፉ ኃይሎች ከባእዳን ጋር ሳይቀር በመሰለፍ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎቻቸውን በጥንቃቄ እየተከታተላቸው ይገኛል። በኢትዮጵያ ወስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከት እና ፍላጎቶች እንዳሉን ብናምንም የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚፈታተኑ እና የሕዝብን ሰላም የሚነሱ ጉዳዮች ሲከሰቱ ግን ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኃይሎች ጋር በጋራ የምንቆም መሆኑን በድጋሚ ለማረጋገጥ ይወዳል።
2.2) ሀገር አቀፍ ምርጫ፡ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን በበርካታ ውስጣዊ እና ውጪያዊ ችግሮች የተከበብን ቢሆንም የፖለቲካ ሥልጣን ማግኛው ብቸኛ መንገድ በሃሳብ ፉክክር ላይ የተመሠረተ ነጻ እና ገለልተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መሆኑ ላይ አቋማችን የማይናወጽ ነው። በሀገራችን ወደ ሥልጣን መውጫ መንገድ ምርጫና ምርጫ ብቻ እንዲሆንም አብክሮ ይሰራል፡፡በዚህም መሠረት አሁናዊ ሀገራዊ ፖለቲካ ላይ ፓርቲው እንደ አንድ ዋነኛ ባለድርሻ የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና ለመጫወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደረጉ ከሚገባቸው ፖለቲካዊ ተሳትፎዎች መካከል በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ አንዱ ነው። ይህንንም ማሳካት እንዲያስችለው በቅርቡ በፓርቲው መሪ የሚመራ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰይሞ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን ያሣውቃል።
2.3) ሀገራዊ ምክክር፡ ሀገራችን ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ኋላቀርነት ምክንያቶች አንዱ እስካሁንም ያልተጠናቀቀው የዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች መሆናቸውን ግልፅ ነው። ከእነዚህ ችግሮች ጋር የተያያዙ የተለያዩ የታሪክ ዕይታዎችና ቁርሾዎች የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ከድጡ ወደማጡ እንዲዘፈቅ በማድረግ ፍትሕ፣ ነጻነት እና እኩልነት የሰፈነባትን የተረጋጋች ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። ከዚህ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነትን ለድርድር ሳያቀርብ ቢያንስ መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የተለያየ እምነት እና ፍላጎት አለን የሚሉ ኃይሎችን ወደ ጋራ ሥምምነት የሚያደርስ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ፓርቲያችን ቀደም ሲል ባጸደቃቸው ድርጅታዊ ሰነዶቹም ሆነ የአቋም መግለጫዎቹ ሲያስገነዝብ ቆይቷል፡፡
ሀገራችንም ለዚህ ጥሩ መደላድል የመፍጠር እድል ያለው የሀገራዊ ምክክር ከሦስት ዓመታት በፊት መጀመሯ ይታወሳል። ሀገራዊ ምክክሩ የሚመራበትን ሕግ በመደንገግም ሆነ ኮሚሽነሮቹን በመሰየሙ ሂደት በርካታ እክሎች የነበሩበት ቢሆንም እንኳን ጉድለቶቹ እንዲስተካከሉ ግፊት እያደረጉ በምክክሩ ሂደት መሳተፍ የተሻለው አማራጭ መሆኑን በማመን ኢዜማ ለሀገር አንድነት፣ ለሕዝብ ሰላም እና እድገት ይበጃል የሚላቸውን ምክረ ሃሳቦች የያዘ ሰነድ አዘጋጅቶ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በሙሉ ልብ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ገዢው ፓርቲ በአንድ አንድ አካባቢዎች እንደተስተዋለው የተለያዩ ጣልቃ ገብነቶችን በመፈጸም አመኔታውን ከመሸርሸር እንዲቆጠብ ለማሳሰብ እንወዳለን። ከዚህ ባለፈ ከፍተኛ ሀገራዊ ሀብት ፈስሶበት የሚደረግ እና በስንት አንድ ጊዜ የሚገኝን ሀገራዊ ምክክርን የመሰለ እድል ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚመጡ ጣልቃ ገብነቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባም እናሳስባለን።
ሀገራዊ ምክክሩ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዲሆን በተለያዩ አከባቢዎች ነፍጥ አንስተው የሚፋለሙ ኃይሎች ተሳታፊ መሆን እጅጉን አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት ከመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ባለፈ የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በድርድር፣ በሽምግልና ብሎም በሌሎች ሰላም ማምጣት በሚችሉ ማናቸውም አማራጭ መንገዶችን ተጠቅሞ ግጭቶቹ የሚቆሙበት ሁኔታን እንዲያመቻች እንደወትሮው ሁሉ ዛሬም በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን። የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት በምንም ምክንያት ይሁን ነፍጥ አንስተው ጫካ የገቡ ኃይሎች ሊያስታውሱት የሚገባው ዋና ቁምነገር ያለፉትን ሁለት ትውልዶች የአመጽ መንገድ ልብ ካልን ከብዙ ሕይወት እና ንብረት ውድመት በኋላ ምናልባት የመንግሥት ለውጥ ማምጣት ይቻል እንደሆነ እንጂ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓትም ሆነ የተሻለ ማኅበረሰብ የሚፈጥር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን እንደማይቻል መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ ነፍጥ ያነሳችሁ ኃይሎች እንታገልለታለን ለምትሉት ማኅበረሰብም ሆነ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ጦርነት ጥፋት እንጂ አንዳች እርባና እንደማያመጣ በመገንዘብ ለሰላም ድርድር በራችሁን ክፍት እንድታደርጉ እና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በድጋሚ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለሀገራዊ የጋራ ጥቅሞቻችን በጋራ እንድንቆም በውስጣዊ ችግሮቻችን ሳቢያ በምንም ሁኔታ ቢሆን ለውጭ ኃይሎች በር እንዳንከፍት ሀገራዊ ጥሪ ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
የካቲት 25/2017 ዓ.ም.
TIPS
The Wars We Still Can Stop
Ethiopia: Israel Foreign Minister Says His Country Wants to Be Part of Ethiopia’s Success
A Nation Silenced: How the 1993 Referendum Stripped All Ethiopians of Their Sea
The 1976 TPLF Manifesto: TPLF’s “Republic of Greater Tigray”
Away from the global spotlight, Eritreans are trapped in a garrison state
Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s
Ethiopia-Eritrea Tension: A Volatile History that Never Truly Ended – Could Assab Become Africa’s Crimea?
“As an outlier among the five tplf leaders, I wasn’t part of the armed struggle tradition”
Former Tigray fighters say no to war
Don’t Risk Your Future: The United States Cracks Down on Illegal Immigration
Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation
Ethiopia and Eritrea Slide Closer to War amid Tigray Upheaval
Sea Outlet Serious and Unabated Agenda for Ethiopia: Retired Lieutenant General Yohannes
Israel’s Peace With Egypt Is Starting to Crack
Egyptian, Eritrean FMs reject involvement of non-bordering countries[Ethiopia] in Red Sea security
Ethiopia, Creditors Agree on $8.4 Billion Debt Restructuring