“የአፋር ህዘብ ስልታዊ አሰፋፈር በቀይ ባህር ጠረፍ አካባቢ በአረብ ባሕረ ስላጤ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በአፍሪካ-ውስጥ መካከል የንግድ በሮች ጠባቂዎችና ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ወደቦቻቸው የወርቅ፣ የዝሆን ጥርስና ሌሎች ውድ ዕቃዎች መለዋወጫና ማስተላለፊያ ሆኑ፣ ይህም በአካባቢው ያላቸውን ተፅዕኖ አጠናክሮላቸዋል።”
መግቢያ
አፋር የዛሬው ኢትዮጵያ፤ ኤረትራ እና ጁቡቲ ሳይፈጠር ከሳውኪን ወደብ (Arab-Peninsula) እሰከ አዱላስ ወደብ ከባቡል መንደብ እስከ ዘይላዕ ወደብ በባለቤትነትና በብቸኝነት ለብዙ ሺ አመታት (Immemorial years) የቆየና የኖኑ ህዝብ ነው።
የዛሬው የኢትዮጵያን፣ የጅቡቲን እና የኤርትራን ክፍሎች የሚያጠቃልለው የአፋር ትሪያንግል ቀደምት ተወላጅ የሆነው የአፋር ህዝብ በቀይ ባህር አካባቢ ታሪካዊ የንግድ ትስስር ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በጥንካሬያቸው እና በባህል ሃብታቸው የሚታወቁት አፋርዎች ቀኝ ገዥዎችና ወራሪዎች በመምጣታቸው በፊት ከጥንት ገዜ ጀምሮ በዚህ ስትራቴጂካዊ ጉልህ ስፍራ በበላይነትና በስኬት የኖረና የመራ ህዝብ ነው።
በአፍሪካ ፣ በአረብ ባሕረ-ገብ መሬት እና በህንድ ንዑስ አህጉር መካከል የሸቀጦች እና የባህል ልምዶች ልውውጥ ውስጥ ወሳኝ አማካኝና አገናኝ በመሆን ለብዙ አመታት አገልግለዋል። በባህር ንግድ መስመሮች ውስጥ በተለይም ከአንደኛ – ሰባተኛውው ክፍለ-ዘመን #የአክሱም ግዛት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት በባህር ንግድና ኢኮኖሚ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ እንደ ቅመማ-ቅመም፣ ጨርቃጨርቅ እና የከበሩ ድንጋዮች የሸቀጦች ግብይት ዋና ተዋናዮች የነበሩና ይህም በክልላዊም (regional) ሆነ በአለምአቀፍ ሁኔታዎች ውስጥ የነበራቸው ጠቀሜታና አስፈላጊነታቸው አጠናክሯል።
የአፋር ህዘብ ከአክሱም ዘመነ መንግሰት ጋር ቅርብ ግንኙነት ስለነበረው በዘመኑ የአክሱም ግዛተ መንግሥት መሳካትና መጠናከር ዉስጥ የአፋር ሚና በጣም ጉልህ (ሀ):- የአፋር ህዝብ እና የቀይባህር ቁረኝነት በአለም አቀፍ ከታሪክ ፀሀፊያን አንደበት:-
የአፋር ህዝብ ለዘመናት በአፍሪካ ቀንድ
የባህር ላይ ታሪክ ውስጥ በጥልቅ የተካተተ የቀይ ባህር ጠረፍ አካባቢዎች የማይደራደር ጠባቂ ህዝብ ነው ።የአፋር ህዝብ በዚህ ወሳኝ የንግድ እና የፍልሰት ኮሪደር ላይ የበላይነታቸው የጀመረው በቀኝ ገዥዎች የተፈጠሩት እንደ ኤርትራ እና ጅቡቲ እንድሁም አሁን ያለችው ኢትዮጵያና ሌሎች ዘመናዊ ሀገራት ከመፈጠሩ በፊት ከብዙ ሺህ አመታት በፊት እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
አንጋፋው የፋራንሳይ የቋንቋና የታሪክ ተመራማሪ ዲዲየር ሞሪን (2012)፡ “Dictionnaire historique des Afar (1285-1982) በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፋቸው በአርኪኦሎጂ ግኝታቸው የአፋርን ህዝብ ቀደምትነት ከቀይ ባህር ጋር የተቆራኘ መሆኑን ቀጥሎ ባለው መልኩ ገልፀውልናል :- ”አፋሮች በቀይ ባህር ተወላጆችና ቀደምት ባለቤቶች በመሆናቸው ባህላዊ እና ግዛታዊ ቀጣይነት ከጥንት ጀምሮ አስጠበቋል። በዳንካሊያ አካባቢ የሚገኙት የቃል-ታሪካቸውና የአርኪኦሎጂ ቅርሶች የአፋር ህዝብ ከቀይ ባህር ሥነ-ምህዳርና ንግድ ጋር የቆየና የተሳሰረ ሥልጣኔ መኖሩን ያረጋግጣል።” በማለት አትተዋል
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ላይ ያተኮረው ጣሊያናዊው አርኪዮሎጂስት እና የታሪክ ምሁር ሮዶልፎ ፋቶቪች ይህንን በሰፊው በተጠቀሰው: የጥንታዊ መንግስታት በሰሜን አፍሪካ ቀንድ (1999) በተሰኘው ፅሑፋቸው ላይ ዳስሷል። እንዲህ በማለት በመፅሀፋቸው ያስረግጣል።
“የአፋሮች የአክሱማዊት ግዛትን (kingdom of Aksumite) ከሰፊው የአፍሮ-ኢውራሺያ
(Afro-Eurasian) የንግድ ሥርዓት ጋር በማገናኘት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።የአፋር ህዝብ በቀይ ባህር ወደቦች ላይ የነበራቸው ቁጥጥር የአክሱም ግዛት :- የሮማንና ቤዛንታይን ኤምፓየሮች ፣ የፋርስ (Persian) እና የህንድ ገበያዎችን በቀጥታ በቀይ-ባህር አፋሮች አማካኝነት እንዲያገኝ አስችሎታል፣ ይህም ዕድል የአክሱም ግዛት እንደ ኃያል ኢምፓየር ወይም ግዛት ሆኖ እንዲያድግ አስችሎታል”።
በተመሳሳይ፣ አንጋፋው የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ The Ethiopian Borderlands በሚል ርዕሰ በ(1997)፣ በፃፈው መፅሀፋቸው በአፋር የበላይነት የተያዘው የአዱሊስ ወደብ (Adulis Port) ያለውን ወሳኝ ሚና ዘርዝሯል። “የአዱሊስ ወደብ በአፋር ተጽእኖ ስር የቀይ ባህር ንግድ ዋና ማዕከል በመሆን ሸቀጦቹን በአፍሪካ፣ በሜዲትራኒያን እና በእስያ መካከል እንዲዘዋወሩ አድርጓል። ያለዚህ መዳረሻና መገናኛ ፣ የአክሱም ግዛት ወደ ሃያልና የስልጣኔ ኤምፓየር ማደጉ በእጅጉ ይገደብ ነበር። በማለት የአክሱም መንግስት ሃያልነት እና ስልጣኔ ትልቅ መንሰኤ በአፋሮች የሚተዳደረው የአዱሊስ ወደብ መሆኑን በመግለፅ የአፋር ህዝብ በአክሱም መንግሥት ስልጣኔ እና ዕድገት ላይ የነበረው ሚናን በአፅንኦት አብራርቷል።
የአፋር የኢኮኖሚ የበላይነት ከአክሱም ውድቀት በኋላም እስከ 20ኛው ክፍለዘመን ድረስ ከቀይ ባህር እስከ ዳናኪል ዲፕሬሽን (Danakil depression) ቀጥሏል። የቀይ ባህር እና የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁር የሆኑት መርዶክዮስ አቢር ይህንን:- በኢትዮጵያ እና በቀይ ባህር (1980) በሚል ስራቸው ሲዳሰሱት የአፋርን የጨው ንግድ (አሞሌ ጨው) ቅልጥፍና ሲገልጹ፡- ” አፋር ከደናኪል ዲፕሬሽን)(Danakil Depression ) ወደ ኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች እና ከዚያም በላይ በማጓጓዝ ለአፍሪቃ ቀንድ የጨው ንግድ የደም ስር በመሆን አገልግሏል ። የንግድ ተጓዦቻቸው (Caravans) የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ከመምጣታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የአገር ውስጥ ኢኮኖሚን አስጠብቆ ቆይቷል።”
እንድሁም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባደረጉት ሰፊ ጥናትና ምርምር የሚታወቁት ታዋቂው እንግሊዛዊው አንትሮፖሎጂስት አይ.ኤም.ሊዊስ ” ይህንን ስር የሰደደ ታሪክ :People’s of the Horn of Africa (1998) በተባለው መጽሃፋቸው እንዲህ ሲሉ ገልፀውታል።
”ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ውስጥ ጣልቃ ከመግባታቸው ከረጅም ጊዜ በፊት የአፋሮች ቁልፍ የቀይ ባህር ወደቦች እና የባህር መስመሮችን/መንገዶችን በመቆጣጠር በቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ዘላቂ ህልውናን ጠብቀዋል” ።
ይህ ታሪካዊ እውነታ የአፋርን ግዛት ሉዓላዊነት ብቻ ሳይሆን የረዥም ጊዜ ሚናቸውን እንደ ባህር መርከበኞች፣ ነጋዴዎች እና የባህል አስተዋይነታቸው የሚያሳይ ነው ።
አፋሮች በአፍሪቃ ቀንደ ከመገኘታቸውም/ከመኖሪያቸው ባለፈ የአፋር ህዝብ ከቀይ ባህር ጋር ያለው ግንኙነት በቋንቋ፣በባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን የሚያተቱ ጥናቶች የአፋርን ቀደምትነት በጉልህ የሚያሳይ ነው ። ታኀዋቂዎቹ አፍሪካውያን የታሪክ ተመራማሪዎች ቦኒ ሆልኮምብ እና ሲሳይ ኢብሳ፣ The Invention of Ethiopia (1990) በሚል ርዕስ ያበረከቱት ተፅዕኖ ፈጣሪ ስራቸው : የአፋርን ህዝብ ከቀይ ባህር ጋር ያላቸው ግንኙነት ከባህላቸው እና ከቋንቋቸው ጥልቀት አንጻር አፅንዖት ሰጥተውበታል።
“የኩሽቲክ ቤተሰብ(Cushitic Family) ቅርንጫፍ የሆነው የአፋርኛ ቋንቋ በአንድ ወቅት የቀይ ባህር የንግድ መረቦችን ይቆጣጠሩ ከነበሩት ነዋሪዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸው እንድሁም የቋንቋ ውርሻቸው፣ በባህር ላይ ማጥመድ፣ ዓሣን ማጥመድ እና በንግዱ ላይ ካላቸው እውቀትና ክህሎት ጋር ተዳምሮ በአፍሪካ ቀንድ (ክልል) ቀደምት የባህር ዳርቻ ነዋሪዎች እንደ ነበሩ ሚናቸውንና በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ህያው ምስክር ናቸው ። በማለት ገልፆታል። የተመራማሪዎቹ ምልከታዎችና ማስረጃዎች የአፋር ህዝብ በአከባቢው የሚገኙ ወይም የሚኖሩ ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በኢኮኖሚና በባህል ልውውጡ ንቁ መሃንዲሶች ነበሩ የሚለውን ታሪክና ሃሳብ ያጠናክራሉ፣ ይህም የአፋርን የቀይ ባህርን ሚና በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በከዚያም በላይ ወሳኝ ትስስር በመፍጠር የተጠናከረ ነበር ።
ከዚህ በተጨማሪ የአፋር ህዝብ በቀይ ባህር ላይ ያለው ፋይዳ የጎላ ነጋዴ በመሆናቸውም ጎልቶ የሚያሳይ እንደ ትሪሚንግሃም በእስልምና እና በአፍሪካ ታሪክ ላይ የተካነ ታዋቂው እንግሊዛዊ ምሁር ”Islam in Ethiiopia (እስላም በኢትዮጵያ)” (1952) በተሰኘው መፅሃፋቸው ላይ ስለ አፋር ህዝቦች በቀይ ባህር ላይ የነበራቸው የኢኮኖሚያዊ የበላይነትን በተመለከተ ተጨማሪ ግንዛቤን በማጠናከር እንድህ በማለት ይገልፃል። “የአፋር ህዘብ ስልታዊ አሰፋፈር በቀይ ባህር ጠረፍ አካባቢ በአረብ ባሕረ ስላጤ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በአፍሪካ-ውስጥ መካከል የንግድ በሮች ጠባቂዎችና ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ወደቦቻቸው የወርቅ፣ የዝሆን ጥርስና ሌሎች ውድ ዕቃዎች መለዋወጫና ማስተላለፊያ ሆኑ፣ ይህም በአካባቢው ያላቸውን ተፅዕኖ አጠናክሮላቸዋል።” በማለት የኣፋር ህዝብን የቀይ ባህር እስትራቴጂክ እና ስልታዊ አሰፋፈርን እንድሁም በኢኮኖሚና ንግድ ላይ የነበራቸው የበላይነት አመላክቷል።
………………………………………………………..
(ለ):- የአፋርን የጂኦፖለቲካል አሰፋፈር እና ፈተናዎች
ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የአፋርን የቀይ ባህር ጠረፎች እና የኢኮኖሚን ቁጥጥር ዝምብሎ ያለ ፈተና የመጣ አልነበረም ። የአፋርን ራስ በራስ ማስተዳደርን እና የአፍሪቃ ቀንድ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል የቅኝ ግዛት እና ኢምፔሪያል ምኞቶች በተከታታይ ለብዙ አመታት በተለያዩ መንገዶች የመጡ ቢሆንም፣ የአፋር ህዝብ በተከታታይ የሚመጣ የውጭ የበላይነትን በትጋት በመከላከል በፅኑ ተቋቁሟል። ይህንን ሀሳብ የሚያጠናክረው ታዋቂው የታሪክ ምሁር #ጆናታን ሚራን በRed Sea Citizens: Cosmopolitan Society and Cultural Change in Massawa (2009)” በተሰኘው ስራው የአፋርን ፀረ-ቅኝ ገዥዎች ተጋድሎ እንድህ ብሎ ዘግቧል፡-
“አፋሮች የኦቶማንን (የቱርክ) ፣ የግብፅን እና በኋላም የአውሮፓ ወረራዎችን በባህር ዳር ግዛቶቻቸው ላይ በመቃወም በፀረ-ቅኝ ግዛት ተቃውሞ ግንባር ቀደም ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ1875 የግብፅን ወረራ በመቃወም ያደረጉት ሕዝባዊ አመጽ ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነበር።
ይህ ተቃውሞ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ እንኳን እንደ #ሱልጣን ያሲን ሃይሳማ እና የአፋር ናሽናልስትና መሪ የነበሩት ያሲን ሞሃሞዳና በመሳሰሉት ሰዎች የሚመሩ ንቅናቄዎች የአፋርን ህዝብ በማበረታታት የአንድነት እና የራስን እድል በራስ የመወሰን ትልቅ እስከ ዛሬ ድረስ ዘርግተዋል።
የአፋር ህዝብ በታሪካቸው በርካታ የውጭ ተግዳሮቶች ገጥሟቸዋል፣ ከነዚህም መካከል በአጎራባች ጎሳዎች እና ኢምፓየሮች ግዛታቸውን ለመቆጣጠር ሙከራ አድርገዋል። እነዚህ ጫናዎች ቢያጋጥሟቸውም እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ የራስ ገዝ አስተዳደርን ጠብቀው ቆይተዋል፣ ይህም ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዥ ኃይሎች እና ከኢትዮጵያ ገዥዎች ጋር በተደረጉ ፍልሚያዎች እና ግጭቶች በንቃት በመፋለም የውጭውን ሀይሎች የበላይነት በመቃወምና በመጋፈጥ ከፍተኛ ተቃውሞ አሳይተዋል። ይህን ተቃውሞ ከሚያጎሉ ታሪካዊ ክስተቶች መካከል በ1875 በስዊዘርላንድ ጀብዱ ቨርነር #ሙንዚንገር የሚመራው የግብፅ ወራሪ ላይ በአፋር አውሳ አካባቢ በተለምዶ ”ጋማሪ” የሚባል (በአሁኑ የአፋር ክልል በአውሲ ረሱ አፋምቦ ወረዳ አካባቢ) በሱልጣን መሀመድ ሃንፍሬ (ኢላልታ) የሚመራው የአፋር ተዋጊዎች ከእነ ጦር መሪያቸው #ሙንዚንገርን ጨምሮ አንድ ሳይወጣ የተደመሰሰበት ክስተት የአፋርን ነፃነታቸውን እና ማንነታቸውን ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት በግልጽ የሚያሳይ ታሪካዊ ክስተት ነው ።
በሌላው ታሪካዊ ክስተት ለ30 አመታት ያህል የቀጠለው የጣሊያን ወረራ ታቃውሞ የአፋር በጊሪፎ ሱልጣን (ቢዱ ሱልጣን )፣ በሱልጣን ሃይስማ አሃው እና በልጆቻቸው ሱልጣን መሀመድ ሃይሳማ እስከ ሱልጣን ያሲን ሃይሳማ ዘመን ድረስ የተደረገው የረጅም ጊዜ መከላከል እና ዉጊያ ነበር ። የአፋር የፀረ-ቅኝ ግዛት ስሜት እና የአፋር ህዝብ በፋሽስት-ኢጣሊያኖች ላይ ለ30 አመታት ባደረገው ተጋድሎ በሺህ የሚቆጠሩ የአፋር ተወላጆች ህይወታቸውን ያጡ ቢሆንም በሙሶሎኒ የሚመራው የጣልያን ሃይሎች በአፋር እልህ አስጨራሽ ጦርነትና መስእዋትነት በአፋር በኩል/ወደ መሀል አገር እና ግዛቶች ማለትም ወደ መሀል ኢትዮጵያ እንዳይገቡ አድርጓል። በዚሁ እልህ አስጨራሽ የማንነት እና ክብርን። አሳልፎ ያለመስጠት ተጋድሎ #ወጣቱ_ሱልጣን_ያሲን_ሃይስማ ከሙሶሎኒ ሀይሎች ጋር ለብዙ አመታት ባደረገው ከባድ ጦርነት በ1931 ቢዱ በተባለች ቦታ በ39 አመቱ ተሰውተዋል ።
……………………………………………………………..
(ሐ):- የአሁኑ የኣፋር ህዝብ ሁናቴ እና የቀይ ባህር ውጥረት
በዘመናችን የአፋር ህዝብ ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር እየተጋፈጠ እና እየተባባሰ የመጣውን የፖለቲካ ተለዋዋጭነት እና ውጫዊ ጫናዎች ተባብሶበታል ። በንግድ በተለይም በቀይ ባህር ጠረፍ እና በጨው ምርት ላይ የነበራቸው የበላይነት በተከታታይ በማሽቆልቆል የብዙ ሺ አመታት የአፍሪቃ ቀንድንና እና የቀይ ባህር ጠረፎችን በባለቤትነት እና በበላይነት ይመሩ የነበረው የአፋር ህዝብ ዛሬ በቀኝ ገዥዎች የተፈጠሩት የአፍሪቃ ቀንድ አገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣ በኤርትሪያ እና በጁቡቲ መንግስታት ያለፍላጐታቸው ተከፋፍለውና ተገልለው ይገኛል። በምስራቅ አፍሪቃ እና በቀይ ባህር አካባቢ ከእነ አካተው እንድጠፉ የተደረገውን የውጭ እና የውስጥ ወረራን ተቋቋመው እስካሁን ድረስ በታሪክ ከነበሩበት አካባቢዎች ፈንክች ሳይል፣ ባህላቸው ፣ ቋንቋቸው፣ እና ማህበራዊ ማስተጋብራቸው ጠብቀው አይበገሬነቱን አስረግጠዋል።
የአፋር ህዝብ በአካል በሶስቱም በአርተፊሻል መስመር የተከለሉ አገሮች የሚገኝ ቢሆንም በመንፈሳቸው የተለያዩ አገር ሰዎች ነን ብሎ አስቦ አያውቅም። አፋሮች በሶስት አገራት ስገኙ ሁሉም በደንበሮች የሚገናኙና በመካከላቸው ሌላ ባዕድ የሆነ አካል ስለላስገቡ እስካሁን ድረስ ማህበራዊ ግንኙነታቸው ማስቀጠል ችሏል።
የአፋር ህዝብ በጦርነት እና በሀይል መርታት እንዳማይቻል የተረዳው ገዢዎች በተለይም የኢትዮጵያ ገዥ ነግስታት አፋርን በጦርነት አለመንካትና ወደ ዘመናዊነት እንዳይቀላቀሉ ፣እንዳይማሩ፣ በኢኮኖሚው እንዳያድጉ ፣ እንዳይነቁ ተብለው በሪጅናል ደረጃም ከዕድገት ፖሊሲዎችና እና ስትራቴጂዎችም ጭምር እንድገለሉ ተደረገው በአሁን ጊዜ በሶስቱም አገሮች በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ይገኛል። የአፋር ህዝብ በሶስቱም አገሮች የሚገኘው የአፋር ህዝብ ከፖለቲካዊ ፣ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ተገለለውና ምንም አይነት ሚና እንዳይኖረው ተደርጓል።
በኤርትራ አፋር ታሪካዊ እርስት የሆኑ አካባቢዎች ላይ ዲሞግራፍን እስከመቀየር እና የአፋር ህዝብ ለዘመናት በጦርነት እንኳን ያልተፈናቀለበትን የባህር ጠረፎችን ለቀው እንድሄዱ በሲስተማቲክ አስገዳጅነት እየተፈናቀሉ ይገኛሉ ። ከኤርትራ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአፋር ቤተሰቦች ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ የመን፣ ወደ ሱዳን ወደ ጅቡቲና ሌሎች አገሮች ተሰደዋል፣ እየተሰደዱም ይገኛል ። ይህንን በመቃወም የቀይ ባህር ነፃ አውጪ ተጋድሎዎች ማለቲም የRed Sea Afar Democratic organization(RSADO), እና Eritrean Afar National Congress (EANC) ትግሎች ከተጀመረ ብዙ አመጣጥ አስቆጥሯል።
በጅቡቲ እንደዚሁ ትልቁን የመሬት ቆዳና የቀደሙ ነዋሪዎች የሆኑት የአፋር ህዝብ ለፈረንሣይ ስላልተጎባደደ ብቻ የጅቡቲን ዲሞግራፊ በመቀየር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት በአካባቢው ታሪካዊ ይዞታዎች ያልነበራቸው የኢሳ-ሶማሌ ጎሳ አባላት እንድይዙ ተደረገው የአፋር ህዝብ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ረገድ ያላቸው ሚና በጣም ደካሜ ሆነዋል።
ይህንን የተቃወመው የጅቡቲ ህዝብ ግዲያ፤ እስር እና መሳደድ ደርሶባቸዋል። ይህንን ጭቆናን በመቃወም (Front for Restoration of Unity and Democracy (FRUD) ወደ የትጥቅ ትግል ገብቶ መታገል ከጀመረ ብዙ አመታት አስቆጥሯል። የአፋር ህዝብ ለብዙ ዘመናት የኖሩበት የቀይ ባህር ዳርቻዎችና ወደቦች ከፍተኛ ጂኦፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው አካባቢዎች ናቸው ።
በታሪክ የአፋር ህዝብ በዛሬይቱ ኤርትረና ጅቡቲ በባህር ዳርቻዎች ሰፍኖ የኖሩበት በመሆኑ በእነዚህ ወደቦችና አካባቢዎች ላይ የሚነሱ ማናቸውም የይገባኛል ጥያቄዎች ለዘመናት የመሬቱ ተቆርቋሪና ነዋሪ ሆኖ የቆየውን የአፋር ህዝብን መብትና ታሪካዊ ህልውና ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።
የአፋር ማህበረሰብን ያላሳተፈ ማንኛውም በቀይ ባህር ወደቦች እና አካባቢዎች የሚደረጉ የይገባኛልም ሆኔ ለሎች ስምምነቶች ቀጥታ የአፋርን ህዝብ ህልውና የሚነካ በመሆኑ አፋርን ቀጥታ የሚያሳትፍ መሆን አለበት።በነዚህ ወደቦች ላይ ፍላጎት ያለው ማንኛውም መንግስት ወይም አካል ከአፋር የፖለቲካ መሪዎች እና ተወካዮች ጋር በመነጋገር ድምጻቸው እንዲሰማ እና እንዲከበር ማድረግ አለበት።
በነዚህ ወደቦች ላይ ፍላጎት ያለው ማንኛውም መንግስት ወይም አካል ከአፋር የፖለቲካ መሪዎች እና ተወካዮች ጋር በመነጋገር ድምጻቸው እንዲሰማ እና እንዲከበር ማድረግ አለበት። ወደቦች የኢኮኖሚ መናኸሪያ ብቻ ሳይሆኑ የአፋር ህዝብ የማንነት እና የአኗኗር ዘይቤ አካል ናቸው። በውሳኔ ሰጪነትና ተጠቃሚነታቸው ሚና ችላ ማለትና መንፈግ የኢ-ፍትሃዊና ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ በአካባቢው ሳላምና መረጋጋትና ተጨማሪ ውጥረቶች እንዳይፈጠሩ እነዚህ ወደቦች በተመለከተ የሚደረጉ ማንኛውም ስምምነቶች እና ፖሊሲዎች ሁሉን አቀፍ ውይይቶች በማድረግ የአፋር ተወላጆች ፍቃድና ተሳትፎ እንዲደረጉ ከአፋር ፖለቲከኞች እና የማህበረሰብ መሪዎች ጋር ምክክር እና ድርድር ተደርጎ መሆን አለበት ።
በመላው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ጅቡቲ የተስፋፋው የአፋር ህዝብ ከእነዚህ የባህር ዳርቻ አካባቢዎች ጋር የባህል፣ የኢኮኖሚ እና የታሪክ ግኑኝነት በመጋራት በማንኛውም በዚህ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች ላይ መሳተፍ ለድርድር የማይቀርብ ያደርገዋል ።
የቀይ ባህር ጠረፍ ወይም ወደቦች የኢኮኖሚ መናኸሪያ ብቻ ሳይሆኑ የአፋር ህዝብ የማንነት እና የአኗኗር ዘይቤ አካል ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም የክልል መንግስታትን (Red Sea Region) እና የኢኮኖሚ አጋሮችን ጨምሮ አለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት የአፋርን ውክልና ከወደብ ጋር በተገናኘ አፋርን የድርድር አካል ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ሊገነዘቡ ይገባል።
የአፋርን ህዝብ ጥቅም ችላ ማለት አሁን ያለውን ውጥረት ከማባባስ እና ለበለጠ መፈናቀል እና መብት መጓደል አስተዋጽኦ ያደርጋል። ፍትሃዊ አካሄድ ዘላቂና ፍትሃዊ መፍትሄ ለመፍጠር ከአፋር ተወካዮች ጋር የኢኮኖሚ ጥቅማጥቅሞችን፣ የአስተዳደር መዋቅሮችን እና የሀብት ክፍፍል ዘዴዎችን መወያየትን ያካትታል። የአፋር ህዝብ ለአያት ቅድመ አያቶቹ ያላቸውን ህጋዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እውቅና መሰጠቱ መረጋጋትን ከማስፈን ባለፈ ለክልላዊ ትብብርና ልማት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
To be continu
Via አፋር ትሪያንግል