ከእውነቱ በለጠ
በፕሪቶሪያ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በተደረገው ድርድር፣ ህውሃትን በመወከል ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ተደራዳሪዎች አቶ ጌታቸው ረዳ እና ጄነራል ፃድቃን ገብረ ትንሳይ መሆናቸው ይታወሳል። እነዚህን ወኪሎቹን እና ተደራዳሪዎቹን የገፋው እና አይናቸው ላፈር ያለው የህወሃት ክንፍ፣ የድርድሩን ሂደት እና የድርድሩ ውጤት የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ባግባቡ የመረዳት ችግር ይታይበታል።
ቀድሞውንም የራሱን ተደራዳሪዎች የምፈልገውን አይነት ስምምነት አይደለም የተፈራረማችሁት በሚል በተደጋጋሚ ሲወቅስ እና ሲኮንን የከረመው የህውሃት ክንፍ፣ በገሃዱ አለም የተደረገውን፣ አለም ያወቀውን ስምምነት ሳይሆን፣ በምናቡ እና በምኞቱ ያለውን ስምምነት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ብሎ በመጥቀስ ራሱም ተወናብዶ፣ ሌሎችንም የሚያወናብድ አካሄድ ይከተላል።

በዚህ አካሄድ የሚከሰተውን ውዥንብር ለማጥራት የሚከተሉትን ነጥቦች እና እውነታዎች መገንዘብ ጠቃሚ ነው፤
o የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ የፖለቲካ ስምምነት እና ቃል ኪዳን፣ በሁለት ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረገ የዘላቂ ተኩስ ማቆም እና የሰላም ስምምነት ነው። ስምምነቱ፣ የአለም አቀፍ ስምምነት( treaty) አይደለም፣ ህግ አይደለም፣ የኢፌድሪ ሕገ መንግስትን እና የሃገሪቱን ህጎች የሚተካ አይደለም።
o ይልቁኑም ስምምነቱ፣ ባስቀመጣቸው ግቦች፣ መርሆዎች እና ግዴታዎች ህጋዊነት እና ሕገ መንግስታዊነትን ትልቅ ስፍራ ሰጥቶዋቸዋል። የስምምነቱ አንድ መርህ ሆኖ የተቀመጠው፣ “Legality and respect for constitutional norms and principles enshrined in the FDRE Constitution” ህጋዊነት፣ የኢፌድሪ ህገ መንግስት ውስጥ የተካተቱ ድንጋጌዎችን እና መርሆዎቹን ማክበር ነው።
o በተጨማሪም፣ በስምምነቱ አንቀጽ 7 ውስጥ የህወሃትን ግዴታዎች አስመልክቶ በግልጽ እንደተመላከተው፣ ህወሃት የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፤

Respect the constitutional authority of the Federal Government, all constitutional bodies and organs of the Federal Government [ የፌደራል መንግስቱን፣ የሁሉንም ሕገ መንግስታዊ አካላት እና የፌደራል መንግስቱን አካላት ሕገ መንግስታዊ ስልጣን ማክበር]

Cease all attempts of bringing about an unconstitutional change of government [ ሁሉንም ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የሚደረግ የመንግስት ለውጥ ሙከራዎች ማቆም]
o ስለዚህ የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ የሃገሪቱ ህጎች እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ሊከበር እንደሚገባው አፅንኦት የሚሰጥ፣ ይህንንም በተመለከተ በተለይም ህወሃት ላይ ግልጽ የሆኑ ግዴታዎችን ያስቀመጠ ነው።

ስለዚህ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት የጊዜያዊ አስተዳደር፣ በሁለቱ ወገኖች ምክክር ሊቋቋም ይገባል ሲል፣ የጊዜያዊ አስተዳደርን አስመልክቶ ባለው የሃገሪቱ የህግ ስርዓት እና አግባብ መሰረት መሆኑ ግልጽ ነው። ምክንያቱም፣ ከላይ እንደተመላክተው፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ህጋዊነትን መልሶ ለማስፈን የተደረገ እንጂ ህጋዊነትን ለመገርሰስ የተደረገ ስምምነት አይደለም። የፖለቲካ ስምምነት፣ ወደ ህጋዊ ቅርጽ ሳይለወጥ እና የህግ መሰረት እንዲይዝ ማድረግ ሳይቻል፣ የጊዚያዊ አስተዳደር ሊኖር አይችልም። የፌደራል መንግስት በጀት ሊመድብለት የሚችል፣ አብሮት ሊሰራ የሚችል ጊዚያዊ አስተዳደር የግድ ህጋዊ መሰረት ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ደግሞ በክልል ደረጃ የሚኖር ጊዜያዊ አስተዳደርን በተመለከተ ብቸኛው እና አግባብነት ያለው የሕግ ማዕቀፍ በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 62(9) ላይ ተተመረኮዘው በፕሪቶሪያ ስምምነትም ታሳቢ የተደረገው የፌደራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 ነው።

በነገራችን ላይ፣ ይህ አዋጅ የወጣው በ1995 አመተ ምሕረት ህወሃት በፌደራል መንግስቱ ቁልፍ እና ሁነኛ ተዋናይ በነበረበት ወቅት ነው። ይህ አዋጅ፣ ከሰሞኑ ወይም ከለውጡ በኋላ የወጣ ህግ አይደለም፡፡ ግልጽ የሆነ ሕገ መንግስታዊ መሰረት ያለው አዋጅ ነው። ጊዜያዊ አስተዳደርን የተመለከትው የሃገራችን የሕግ ማቀፍም ይህ አዋጅ ነው።

ይህ አዋጅ ለፌደራል መንግስት እና ለመራሄ መንግስቱ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰፊ ስልጣን እና ሃላፊነት የሰጠ ቢሆንም፣ ይህን ስልጣን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት የፌደራል መንግስቱ ህወሃትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገው ምክክር እና የሚሰበስበው ግብዓት ጠቃሚ እና እጅግ አስፈላጊ ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር አካታች መሆን እንዳለበት ይገልፃል። ስለዚህ የፌደራል መንግስት የጊዜያዊ አስተዳደሩን አካታችነት እና ቅቡልና ለማሳደግ ከህዝብ አስተያየት እና ጥቆማ መሰብሰቡ ተገቢ ነው።