የሃገር መከላከያ ሰራዊት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ምክንያት የፋኖ ሃይሎች ዘመቻዎች እና ብ/ጀነራል ምግበይ ሃይለ ግንኝነት እንዳላቸው በመጥቀሱ ምክንያት አጀንዳው ከፍተኛ ትኩረት አግንቷል ። ይህ የመከላከያ ሰራዊት መግለጫ ምን ያህል እውነትነት አለው የሚለውን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ፋኖ ከትግራይ ሃይሎች በተለይም የእነ ደብረፂዮን ህወሓት ጋር በመጣመር ፌደራል መንግስት ለመጣል ቢስማሙ ወይም ለመስማማት ዕቅድ ካላቸው ፖለቲካዊ እንድምታው ምን ማለት እንደሆነ ግና መታወቅ ያለበት ይመስለኛል።
1ኛ) የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፅዮን ህወሓት ጋር መጣመሩ ወይም ለመጣመር ዕቅድ አለው ማለት በዋነኛነት የፋኖ ሃይሎች ለትጥቅ ትግል የዳረጋቸው ምክንያት የህልውና ሳይሆን የስልጣን መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል የሚያስብል ይሆናል ። ይህ ለማለት የቻልኩት ምክንያቱም የአማራ ህዝብ ችግሮች ህገ መንግስታዊ እና መዋቅራዊ ናቸው የሚል በአማራ ክልል ፖለቲካዊ ሃይሎች የተደረሰ ስምምነት መኖሩን ስለማቅ ነው ። በሌላ አማርኛ የአማራ ህዝብ ችግሮች የሚመነጩት አሁን ካለው የፌደራል ህገ መንግስት መሆኑን ብዙዎቹ የአማራ ፖለቲከኞች የሚስማሙበት እና በትግል ሂደታቸው የትግል አጀንዳቸው መሆኑን የሚታወቅ ሃቅ ነው። ከዚ ነጥብ አንፃር የአማራ ህዝብ ለእልቂት የዳረገው ህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በመትከል፡ ለዚህም ደጋፊ የሚሆን ትርክት በመንዛት፡ በማስፈፀም እና ዘብ በመቆም የእነ ደብረፂዮን ህወሓት( core Tplf) ዋነኛ ፖለቲካዊ ሃይል በመሆኑ የፋኖ ሃይሎች ከዚህ ሃይል ጋር የሚያደጉት መጣመር ትግላቸው የህልውና ሳይሆን የስልጣን ለዛውም ከአማራ ህዝብ ግፍ ፈፃሚ ሃይል ጋር የሚደረግ መርህ አልባ ጥምረት እንደሆነ ያሳያል የሚል እምነት አለኝ።
2ኛ) የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፂዮን ህወሓት ጋር ጥምረት መፋጠር እንደ አዲስ የትግል ሃይሎች በሂደት የቅቡልነት ችግር ይፈጥርባቸዋል የሚል እምነት አለኝ። የእነ ደብረፂዮን ህወሓት በረዥም ግዜ የስልጣን ቆይታ ምክንያት ሰፊ የሚባል ሰብአዊ መብት ጥሰቶች፡ የሙስ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች በመፈፀማቸው ምክንያት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ቡድኖች ናቸው። በመሆኑም በዚህ ልክ እና መጠን በወንጀል የሚፈግ አካል ጋር የትግል ጥምረት የሚፈፀም አካል የፍትህ፡ የዴሞክራሲ እና የህግ ልዕልና አካል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም ከወዲሁ የስልጣን ሃይል እና ስልጣኑን ተፃረው የቆሙት አካላት በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ በማስተናገድ ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት ፡ ሙስና የሚፈፅም፡ ፍትህ የሚያጓድል እና ለህግ ልዕልና ቀናኢ ያልሆነ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም የፋኖ ሃይሎች አዲስ እንቅስቃሴ ቢሆንም ቅቡልነቱ አሉታ ከሆነው የእነ ደብረፂዮን ሃይል የትግል ጥምረት ካደረገ ቅቡልነቱ በዛ ልክ የወረደ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
3ኛ) የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደረብፅዮን ቡድን ጋር መጣመሩ ሊያስከትለው የሚችል ሌላው ፖለቲካዊ አደጋ ከትግራይ አዲስ ትውልድ ጋር ሊገጥመው የሚችል ስልታዊ ተቃርኖ ነው። አሁን አሁን በትግራይ ክልል እየታየ እንዳለው ፖለቲካዊ ዕድገት አዲሱ የትግራይ ትውልድ ፀረ ህወሓት በአጠቃላይ የደብረፅዮን ቡድን በልዩ ሁኔታ ከፍተኛ ተቋውሞ ከማሰማት አልፎ የትጥቅ ትግል የማድረግ ምልክትቶች እየታዩ ነው። በዚህ ሂደት የአዲሱን ትውልድ ፀረ እነ ደብረፂዮን ህወሓት የሚደረግ ትግል የክልሉ ዋነኛ ሃይል ለመሆን እና እየሆነ ሲመጣ በሚያደርገው ትግል የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፂዮን ቡድን በሚቀርብለት ጥያቄ ሊያደርገው የሚችል ማናቸውም ድጋፍ ከትግራይ አዲሱ ትውልድ ጋር ግጭት መግባት ሊኖር ይችላላ። ይሄ ደግሞ የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፂዮን ቡድን ከሚያገኙት ጥቅም በላይ ከትግራይ አዲሱ ትውልድ የሚገጥማቸው ተፃብኦ በብዙ እጥፍ ይጎዳቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
4ኛ) የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፂዮን ቡድን ጋር መጣመር ከፈጠሩ ሌላው ሊያስከትለው የሚችል አደገኛ ውጤት ከትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተደዳር ሊኖር የሚችል ከፌደራል መንግስት ወታደራዊ ጥምረት መፍጥር ነው። እንደሚታወቀው የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ምንም እንኳን ዝቅ ያለ ወታደራዊ ድጋፍ ቢኖረውም ከፍተኛ የሚባል የህዝብ በተለይም የወጥቶች ድጋፍ ያለው አካል ነው። ግዚያዊ አስተዳደሩ በማናቸው የጦርነት ፕሮጀክቶች የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ሲገልፅ ይሰማል። ለዚህም ይመስለኛል የፌደራል መንግስት የዛሬ ሁለት አመት በአማራ ክልል ጦርነት ሲያውጅ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ከሌሎች ክልል መንግስታት በተለየ ሁኔታ ለፌደራል መንግስት የድጋፍ መግለጫ ያላወጣው። ሆኖም ይህ የግዚያዊ አስተዳደሩ የገለልተኝነት አቋም ሊቀየርበት የሚችል በጣም ጠባብ ዕድል የለም ማለት አይደለም። የፋኖ ሃይሎች እና የነ ደብረፂዮን ህወሓት መጣመራቸው እውን ሆኖ ውጤት እያመጣ ከታየ የግዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮቹም ስልጣናቸው ከእነ ደብረፂዮን ቡድን ከመነጠቅ ለማዳን ያችን ጠባብ ዕድል በመጠቀም ከፌደራል መንግስት ጋር በመጣመር ፀረ ፋኖ -ደብረፂዮን ቡድን የጥምረት እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይችላሉ።
በአጠቃላይ የፋኖ ሃይሎች ከእነ ደብረፂዮን ቡድን ጋር መጣመራቸው ማስረጃ ይሁን መረጃ የሌለ ቢሆንም ፍላጎት ግን የለም ማለት አይቻልም። ይህ ጥምረት ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች ውጤት አልባ የተሳሳተ ጥምረት ( wrong match) ነው የሚል እምነት አለኝ።
Abera Nigus ( opinion)