ዛሬ ጠዋት ወደ ምስራቃዊ ዞን የሰላምና የፀጥታ ሃላፊ ደውሎ ” ከቀበሌ የተወጣጡ ጥቂት ደጋፊዎች በሰራዊት በመታገዘ ጊዚያዊ አስተዳደሩ የሾማቸው ከንቲባ ሲገለገሉት የነበረው ፅሕፈት ቤት በመስበር በደብረፅዮኑ ትህነግ ለተመረጡት ከንቲባ አስረክበዋል
ለወራት የቆየው በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ባለፉት ወራት በደብረፂዮን (ዶ/ር) የሚመራው ወገን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።
በአቶ ጌታቸው የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ይህ ሙከራ በክልሉ አለመረጋጋት በማስፈን ያለውን ችግር እንደሚያባብስ በመግለጽ ቢያስጠነቅቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቱ እየተባባሰ ይገኛል።
ባለፉት ቀናት በክልሉ ያሉት ታጣቂ ኃይሎች አመራሮች ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የደብረፂዮን ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ተቋማትን በኃይል የመቆጣጠር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑ እየተገለጸ ነው።
ይህ ሁኔታም በክልሉ ዳግም ግጭት ሊያስከትል ይችላል በሚል ነዋሪዎች ላይ ከባድ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ አቅም ያላቸው ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያቀኑ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተለይ በአቶ ጌታቸው የሚመራው አስተዳደር የትግራይ ኃይልን ከሚመሩት ወታደራዊ አዛዦች መካከል ዋነኛ የሚባሉትን ሦስት መኮንኖች ማገዱን ካስታወቀ በኋላ ውጥረቱ አይሏል። ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ በምሥራቃዊ ዞን የጊዜያዊ አስተዳደሩን የተቃወሙ የሠራዊት አመራሮች ከመሩት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የአዲግራት ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ታውቋል።
ይህንን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች እና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወይም የደረሰ ጉዳት እንዳለ አልተገለፀም። ትናንት ሰኞ የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለአራት ሰዓታት በዶ/ር ደብረፂዮን በሚደግፉ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው ነበር። የአዲግራቱን ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ህወሓት በፌስ ቡክ ገፁ አረጋግጧል።
“የአዲግራት ከተማ ከንቲባ ሆኖ በምክር ቤት የተሾመው ረዳኢ ገብረ እግዚአብሔር በምስለኔ ግለሰቦች በተሾሙ ሰዎች ምክንያት ጽህፈት ቤቱን ተረክቦ አገልግሎት እንዳይሰጥ አደርጎ ቆይቷል” በማለት ጽህፈት ቤቱን መልሰው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ አመራሮች በወረዳ እና በዞን ደረጃ በሚደረጉ የሹም ሽር ጉዳዮች ፖለቲካዊ እሰጥ አገባ ውስጥ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህ በክልሉ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው አለመግባባት ያስከተለው የፀጥታ ስጋት ደግሞ ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረውን ሁኔታ አንደሚያስታውሳቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በሁለት ቡድን ተከፋፍለው በክህደት እና በመንግሥት ግልበጣ የሚወናጀሉት የህወሓት አመራሮች ሁኔታ በሕዝቡ መካከል ስጋት ወደ ፈጠረ አለመግባባት ገብተዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ መጋቢት 1/2017 ዓ.ም. አለመረጋጋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው ያሏቸውን ሦስት የትግራይ ኃይሎች አዛዦችን አግዷል። በደብረፂዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳን “የቀድሞ ፕሬዝዳንት” አንደሆኑ በመግለጽ ይህ ዕግድ ሕጋዊነት የሌለው እና ተግባራዊ የማይሆን ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል።
በተመሳሳይ የክልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ እርምጃው “የተቋሙን አሠራር ያልተከተለ፣ ያልሾመውን የሚያወርድ የግለሰብ እርምጃ ነው በማለት” ቅቡል አይደለም ብሏል።
ይህ መግለጫ ኃላፊነት የጎደው ነው ያለው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በበኩሉ መግለጫው የአንጃው መግለጫ ግልባጭ ነው፤ ይህም ሕጋዊ፣ ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ ተቀባይነት የሌለው ስለሆነ በአስቸኳይ መታረም እንዳለበት አዟል። ይህ ካልሆነ ግን “ይህንን ተከትሎ ለሚመጡ ነገሮች ሙሉ ኃላፊነት የሚወስደው በቢሮው ስም መግለጫ ያወጣው ከፍተኛ የቢሮ አመራር ነው” በማለት አስጠንቅቋል። https://www.bbc.com/amharic/articles/c9wp714r17zo