ደብረጽዮን የሚመሩት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሕዝብ መሪውን እንዲመርጥ ያቀረቡትን ጥሪ አወገዘ፤ ግንባሩ ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚነንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) የትግራይ ህዝብ ለቀጣይ አንድ ዓመት ስልጣኑ የሚራዘመውን የጊዚያዊ አስተዳደሩን የሚመራ ፕሬዜዳንት እንዲጠቁም ያቀረቡትን ጥሪ “የተናጠል ውሳኔና ተግባር” ሲል ነው የተቃወመው።
” የፕሪቶሪያ ሥምምነት ከተፈረመ ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖታል ” ያለው የደብረፅዮን ትህነግ ” ስምምነቱ በሙሉነት ተተግብሮ ትግራይ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሊኖራት ይገባ ነበር ” ብሏል። ይህ እንዳይሆን በግንባር ቀደምትነት የጊዜያዊ አስተዳደሩን እግር ሲጎትትና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የእነ ደብጽዮን አንጃ እንቅፋት እንደሆነ አቶ ጌታቸው መናገራቸው አይዘነጋም።
” የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉነት ያልተተገበረው የፌደራል መንግስት በስምምነቱ አፈፃፀምና አተገባበር በተከተለው የተሳሳተ አካሄድና ፓለቲካዊ ቀውስ እንዲፈጠር በመስራቱ ነው ” ሲልም ክስ አሰምቷል።
” በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንቀፅ 3 መሰረት ተዋዋይ ወገን ሌላውን በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ በፕሮፓጋንዳ ማጥቃት ይከለክላል ይሁን እንጂ ይህንኑ የስምምነቱ አካል በፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነው ” ብሏል።
” የፌደራል መንግስት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መንፈስና ይዘት በወጣ አካሄድ አግባብነት በሌላቸው 359/1995፤ ደንብ 533/2015 ህግና አዋጆች እንዳሻው እየወሰነ ይገኛል ” የሚል ወቀሳም አቅርቧል።
” የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንቀፅ 10 የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግስት መግባባት እንዲቋቋም ያዛል ” ያለው የደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ” የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ውሳኔ መወሰን አይችልም ” ብሏል።
” ህወሓት ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ ከስልጣን ማስነሳቱ ተከትሎ ፤ ጀነራል ታደሰ ወረደ ፕረዚደንት እንዲሆኑ ማእከላዊ ኮሚቴ ወስኖ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀብሎታል” ካለ በሁዋላ “ይህንን ወደ ጎን በመተው በጠቅላይ ሚንስትሩ የተናጠል ውሳኔ በሚያስመስል መልኩ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የሚጥስ አካሄድ ተቀባይነት የለውም ” ሲል ገልጿል።
” የፌደራል መንግስት ህዝብን ከሚጎዱ ግልፅ ተግባራት በመቆጠብ ዘላቂ ጥቅምና የጋራ ሰላም በሚያረጋግጡ ተግባራት እንዲያተኩር ጥሪ እናቀርባለን ” ያለው የደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ” የተናጠል ውሳኔዎች እንዲቆሙ ” ብሏል።
በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት አዲስ በሚዋቀረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ፌደራል መንግስት ሃምሳ ከመቶ ድርሻ እንዳለውና በክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ያዛል። የክልሉን መሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሰይሙ በግልጽ ተቀምጧል። ደንቡ ይህ ሆኖ ሳለ ትህነግ ምኑን ነቅሶ እንድተቃወም ለአብዛኞች ግልጽ አልሆነም። ይልቁኑም “ውሳኔው የትግራይን ህዝብ ትዕግስት የሚፈታተን ነው” ተብሎ የተገለጸው በርካቶችን ግራ አጋብቷል። ሕዝብ የሚፈልገውን ቢመርጥ ትህነግ ለምን እንደሚቃወም ሕዝብ ጥያቄ እንደሚያቀርብ ከወዲሁ እየተሰማ ነው።
በጦርነቱ ወቅት ግፋ በለው ሲሉ የነበሩና ተቀማጭነታቸው ውጭ አገር የሆኑ የትግራይ ብሄርተኛ ሚዲያዎች “ጥሪው የትግራይን ህዝብ መናቅ ነው” ሲሉ ተድምጠዋል።
ትርጉም ቲክቫህ